ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ስሑል ሽረ ላይ የግብ ናዳ በማውረድ ዙሩን በድል ከፍቷል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ዛሬ ጅማሮውን ሲያደርግ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ስሑል ሽረን የገጠመው ኢትዮጵያ ቡና በአቡበከር ናስር ሐት-ትሪክ እና ሀብታሙ ታደሰ ሁለት ጎሎት በመታገዝ ስሑል ሽረን 6-1 በመረምረም ሁለተኛው ዙር በአስደናቂ ውጤት ጀምሯል።

ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ከተጠቀሙት ስብስብ ውስጥ የቀኝ መስመር ተከላካዩ አህመድ ረሺድን በኃይሌ ገ/ተንሳይ ብቻ ቀይረው ወደ ሜዳ ሲገቡ በአንፃሩ ስሑል ሽረዎች ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው የሆኑት አብዱለጢፍ መሐመድ እና ያስር ሙገርዋን ሳይዙ ወደ ዛሬው ጨዋታ ገብተዋል። በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ክለቡን የተቀላቀለው ዮናታን ከበደ ደግሞ በተጠባባቂነት ጨዋታውን ጀምሯል።

በትናንትናው ዕለት ዋና አሰልጣኝ በመሆን ሽረን የተረከቡት አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃ ምንም እንኳን ቡድኑ መምራት ባይችሉም ከጨዋታው መጀመር በፊት በነበረው የቡድን ውይይት መርተው ጨዋታውን ከተመልካች ጋር ሆነው መከታተል ችለዋል።

ገና ከጅምሩ ጫና መፍጠር የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ገና በማለዳ ነበር ወደ ሽረ የግብ ክልል መድረስ የጀመሩት። በ2ኛው ደቂቃ አቡበከር ናስር አስቀድሞ ሀብታሙ ታደሰ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ተቆጣጥሮ በድጋሚ ወደ ግብ የላካትን ኳስ የሽረው ግብጠባቂ ምንተስኖት አሎ ሊያድንበት ችሏል።

ስሑል ሽረዎች በተወሰኑ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች በግራ መስመር የተሰለፈው መድሀኔ ብርሃኔ በግል ጥረቱ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል ከሚያደርገው ጥረት በዘለለ ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ ባልቻሉበት የመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች ጨዋታውን በመቆጣጠር ረገድ የተሻሉ ነበሩ።

ጫና ከጅምሩ መፍጠር የጀመሩት ቡናዎች
በ7ኛው ደቂቃ አስራት ቱንጆ ከግራ መስመር ያቀበለውን ኳስ አቡበከር ከሳጥን ጠርዝ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ምንተስኖት ሲመልስ በድጋሚ ሀብታሙ ቢያገኛትም መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። ነገርግን በ8ኛው ደቂቄ ፈቱዲን ጀማል ከመሀል ሜዳ አካባቢ ከሽረ ተከላካዮች ጀርባ ለቡድኑ አጋሮቹ ያቀበለውን ኳስ ምንተስኖት አሎ ወደ ሳጥኑ ጠርዝ ፈጥኖ በመድረስ ቀድሞ ቢቆጣጠርም ኳሱን ለማፍጠን በሚያነጥርበት ወቅት የተሳሳተውን ኳስ አቡበከር ናስር አግኝቶ በቀላሉ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ወደ መሐል ሜዳ ተጠግቶ ለመከላከል ከሚጥረው የሽረ ተጫዋቾች ጀርባ የሚፈጠረውን ክፍት ቦታን መጠቀም ተቀዳሚ እቅዱ የነበረው ቡና ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ ተስተውሏል። በ32ኛው ደቂቃም በሽረ ሳጥን ጠርዝ አካባቢ አቡበከር ናስር ታግሎ ያሾለከለትን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከገባ በኃላ ወደ ግብ የላከው ኳስ በምንተስኖት አሎ ስህተት ታግዞ ከመረብ በማዋሀድ ልዩነት ያሰፉበትን ግብ አስቆጥሯል።

በ43ኛው ደቂቃ ደግሞ ነፃነት ገ/መድህን ሀብታሙ ታደሰ ከሽረ ሳጥን ውስጥ ለማሻማት የሞከረውን ኳስ በእጁ በመንካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር ናስር በማስቆጠር ቡድኑ በ3-0 እየመራ ወደ መልበሻ ቤት እንዲያመራ አስችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች ከፍ ባለ ፍላጎት የግብ ልዩነቱን ለማጥበብ ኢትዮጵያ ቡናዎች ላይ ጫና በማሳደር የጀመሩት ሽረዎች ገና በ48ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ አካባቢ በረጅሙ ያሻሙትን የቅጣት ምት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ለማውጣት ባደረጉት ጥረት ኃይሌ ገ/ተንሳይ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ልማደኛው ሀብታሙ ሸዋለም በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ጨዋታ የመመለስ ተስፋ ሰጥቶ ነበር።


ነገርግን የሽረዎች ተነሳሽነት ከ55 ደቂቃ በኃላ መዝለቅ አልቻለም ነበር። በተጨማሪም በመጀመሪያ አጋማሽ ከተከላካይ ጀርባ በሚተዋቸው ክፍት ቦታዎች አደጋ ሲጋብዙ የነበሩት ሽረዎች በተመሳሳይ መንገድ በሁለተኛው አጋማሽ መቀጠላቸው በመከላከል ሽግግር ወቅት በተጋጣሚ ሜዳ ክፍል በርካታ ተጫዋቾች ከመቅረታቸው ጋር ተዳምሮ በሁለተኛው አጋማሽ በኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች የግብ ክልላቸው በቀላሉ ሲጎበኝ ውሏል።
በ57ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ከተከላካይ ጀርባ ለሚኪያስ መኮንን ያሳለፉለትን ኳስ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሽረ ሳጥን ውስጥ በቁጥር በዝተው በመገኘት ታፈሰ ሰለሞን ወደ ግብ የላከው ኳስ በሽረ ተጫዋቾች ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው አቡበከር ናስር ደገፍ አድርጎ በማስቆጠር በሽረዎች መነቃቃት ላይ ውሃ ቸልሷል። በግሉም ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል።

አሁንም ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ቡናዎች በ68ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ታደሰ ላይ ክብሮም ገ/ህይወት በሰራው ጥፋት ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሚኪያስ መኮንን አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ አምስት ከፍ ማድረግ ችሏል።

ቡናዎች በተቆጠሩት ግቦች ይበልጡኑ እየተነቃቁ የመጡ ሲሆን በ86ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አዲስ ፍሰሀ ከራሳቸው ሜዳ ክፍል በግሩም ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ከተከላካዮች ጀርባ አፈትልኮ የገባው ሀብታሙ ታደሰ ከሳጥን ጠርዝ ምንተስኖት አሎ ኳሷን ለማዳን በፍጥነት ወደ እሱ መምጣቱን ተመልክቶ አንጠልጥሎ የማሳረጊያዋን ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 6-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ