ሪፖርት | የጣናው ሞገድ ጅማን በሜዳው አሸንፏል

የ2ኛ ቀን የ16ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ባህር ዳር ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን በሜዳው ጋብዞ 1-0 አሸንፏል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የቀድሞ የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ማኅበር አመራሮች እንዲሁም የአሁኑ አመራሮች በተናጥል ለቀድሞ ተጨዋቾቻቸው እና አሰልጣኛቸው (ጳውሎስ ጌታቸው) ስጦታዎችን አበርክተዋል።

ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች በ15ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ስሑል ሽረን ጋብዘው አንድ ለምንም ከረቱበት ቋሚ 11 ፍቃዱ ወርቁን በሚኪያስ ግርማ ብቻ ቀይረው ወደ ሜዳ ሲገቡ ተጋባዦቹ ጅማዎች ደግሞ በሊጉ አጋማሽ ጨዋታ ከተተቱበት የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ መሀመድ ሙንታሪ እና መላኩ ወልዴን በሰዒድ ሀብታሙ እና ወንድማገኝ ማርቆስ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በሁለቱም በኩል በነበረ ፈጣን እንቅስቃሴ ታጅቦ የጀመረው ይህ ጨዋታ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር አስመልክቷል። ገና እንደተጀመረም የባህር ዳር ከተማ የቀኝ መስመር ተከላካይ ሚኪያስ ግርማ ከርቀት አክርሮ ወደ ጎል በመታው ኳስ የመጀመሪያ ሙከራ ተስተናግዷል። ከደቂቃ በኋላም ጀሚል ያዕቆብ በእንግዳዎቹ በኩል ጥሩ ኳስ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መትቶ ሙከራ አድርጓል። ጅማዎች ከዚህ ሙከራ በተጨመሰሪ በ6ኛው ደቂቃም በአጥቂያቸው ብዙዓየው እንደሻው አማካኝነት ጥቃት ሰንዝረው ነበር።

በእኩል የጨዋታ ሚዛን የጀመረው ጨዋታው ቀስ በቀስ የባለሜዳዎቹ ሃያልነት ተስተውሎበታል። በዚህም ባህር ዳሮች ኳስን በትዕግስት በመቀባበል ጥቃቶችን መሰንዘር ይዘዋል። በተለይ በ11ኛው እና በ14ኛው ደቂቃ በተገኙ የቅጣት እና የመዓዘን ምቶች ቡድኑ እጅግ ለግብ ቀርቦ ነበር። በተቃራኒው የሚዋልል እንቅስቃሴ በማሳየት ጨዋታውን የቀጠሉት ጅማዎች በ20ኛው ደቂቃ መልካም አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በዚህ ደቂቃ ኤሊያስ በግል ጥረቱ ያገኘውን ኳስ ለብዙዓየሁ አቀብሎት ብዙዓየሁ ስቶታል።

የጅማን የግብ ክልል መፈተሽ የቀጠሉት የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ተጨዋቾች በ23ኛው ደቂቃ በአስፈሪ ሁኔታ ወደ ግብ ደርሰው አላማቸውን የግቡ አግዳሚ አምክኖባቸዋል። በዚህ ደቂቃ ፍፁም ከአጋሮቹ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ወደ ጎል የሞከረው ኳስ መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል። ከዚህ በተጨማሪም ስንታየሁ በጅማ ተጨዋቾች የቅብብል ስህተት ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ መትቶ የግቡ ቋሚ መልሶበታል። ቋሚው የመለሰውንም ኳስ ፈጣኑ የመስመር ተጨዋች ግርማ አግኝቶት ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በሚያገኙዋቸው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ብቻ ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል መድረስ የቀጠሉት ጅማዎች በ33ኛው ደቂቃ በተሞከረ የተመስገን ጥሩ ኳስ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት መዘናጋቶች ያስመለከቱት ጅማዎች ግብ አስተናግደው መመራት ጀምረዋል። በ40ኛው ደቂቃም ከግራ መስመር የተሻገረን ኳስ ፍፁም ዓለሙ ወደ ግብነት ቀይሮ ባህር ዳሮች መሪ ሆነዋል። ጎሉ ከተቆጠር ከደቂቃ በኋላም ቁመተ መለሎው አጥቂ ስንታየሁ 2 ወርቃማ እድሎችን አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። እንደ አጀማመራቸው የጨዋታውን አጋማሽ ያላገባደዱት ጅማዎች ስህተታቸውን የሚያርሙበት እድል በጭማሪው ደቂቃ አግኝተው የግቡ ቋሚ መልሶባቸዋል። አጋማሹም በባህር ዳር መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የጣሩት ጅማዎች ገና ከጅምሩ ጥቃቶችን መሰንዘር ተያይዘዋል። በዚህም በ46ኛው ደቂቃ ኤሊያስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ የባለሜዳዎቹን መረብ ለመፈተሽ ጥረዋል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም ጅማዎች በ48ኛው ደቂቃ በተገኘ የቅጣት ምት ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል።

በተቃራኒው በተቀዛቀዘ አጨዋወት ወደ ሜዳ የገቡት ባህር ዳሮች የመጀመሪያ የጠራ ሙከራ ለማድረግ 20 ደቂቃዎች ወስደውባቸዋል። በዚህም በ65ኛው ደቂቃ የቡድኑን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው ፍፁም ከሳላምልክ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብለው ለስንታየሁ ያደረሱትን ኳስ ስንታየሁ በአስቆጪ ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ለዚህ ጥቃት ወዲያው ምላሽ የሰጡት ጅማዎች በበኩላቸው ከ2 ደቂቃዎች በኋላ ብዙዓየሁ በሞከረው ጥብቅ ኳስ አቻ ለመሆን ጥረዋል።

ባለሜዳዎቹ ባህር ዳሮች በጥሩ አቀራረብ ይህንን አጋማሽ አይጫወቱ እንጂ በፈጣን ሽግግሮች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ታትረዋል። በዚህም በ70ኛው ደቂቃ ሳሙኤል በግራ መስመር ያገኘውን ኳስ ሰብሮ በመግባት የሞከረው ሙከራ ሰዒድ አምክኖታል። በተጨማሪም በ80ኛው ደቂቃ ሳላምላክ በተቃራኒ መስመር ያገኘውን ኳስ በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ጥሮ ሳይሳካለት ቀርቷል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ቡድኑ ከመዓዘን በተሻገረ ኳስ ጥሩ ጥቃት ሰንዝሮ የግቡ አግዳሚ መልሶታል።

በአንፃራዊነት በዚህ አጋማሽ ተሽለው የተጫወቱት ጅማዎች በእንቅስቃሴ ደረጃ ሻል ያለ ነገር ቢያስመለክቱም የላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ በሚፈጥሩት የውሳኔ እና የቅብብል ስህተት ፍሬያማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃዎች ሲቀሩትን የቡድኑ የአማካይ መስመር ተጨዋች ንጋቱ ከርቀት በተመታ የቅጣት ምት ቡድኑን አቻ ለማድረግ ጥሯል። ጨዋታው ተጠናቆ በተጨመረው የጭማሪ ደቂቃ ወደ ጅማ የግብ ክልል በፈጣን ሽግግር ያመሩት ባህር ዳሮች በፍፁም አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ጥረው መክኖባቸዋል። ጨዋታውም በባህር ዳር ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ