ሪፖርት | የዓመቱ ፈጣን ጎል በተቆጠረበት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻን ረቷል

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ባስተናገደው የሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ በሀብታሙ ገዛኸኝ ሐት-ትሪክ ታግዘው 5-3 በማሸነፍ ተከታታይ የድል ጉዟቸውን ቀጥለዋል።

ሲዳማ ቡናዎች በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ሰበታን በሜዳቸው ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት ቡድን ውስጥ ፍቅሩ ወዴሳ ፣ ግርማ በቀለ እና ብርሀኑ አሻሞን በመሳይ አያኖ ፣ ሰንደይ ሙቱክ እና ዳዊት ተፈራ በመተካት ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል። ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ስታድየም በኢትዮጵያ ቡና አስደንጋጭ ሽንፈት የቀመሰው ወላይታ ድቻ ደግሞ በጉዳት ባጣው ውብሸት አለማየሁ ምትክ ሙባረክ ሽኩርን ለሀድያ ሆሳዕና አሳልፎ በሰጠው ተስፋዬ አለባቸው ቦታ ተመስገን ታምራትን በመለወጥ ወደ ሜዳ ገብቷል።

ከጨዋታው መጀመር ቀደም ብሎ የሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ በርካታ የሁለቱን ክለቦች ደጋፊዎችን ለማስተናገድ በመገደዱ ምክንያት እጅግ ብዙ ደጋፊዎች ቦታ በማጣታቸው ምክንያት ጨዋታውን መከታተል ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በሌላ በኩል ከዚህ በፊት ከሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ጋር ሰጣገባ ውስጥ ገብቶ የነበረው የወላይታ ድቻው አምበል እና አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ የሲዳማ ቡናን ደጋፊዎች ይቅርታ በመጠየቅ የአበባ ስጦታ አበርክቶላቸዋል።

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ ፊሽካቸውን ባሰሙበት ቅፅበት ሲዳማ ቡናዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት ግብ አስቆጥረዋል፡፡ 44ኛው ሰከንድ ላይ ዳዊት ተፈራ ከመሀል የደረሰውን ኳስ በግራ በኩል በዛው ቅፅበት ወደ ግብ ክልል በፍጥነት በአየር ላይ ሲያሻማ የወላይታ ድቻ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ ዝንጉነት ታክሎበት አምበሉ አዲስ ግደይ በፍጥነት ደርሶ በጭንቅላቱ በማስቆጠር ሲዳማ ቡናን መሪ አድርጓል፡፡ ይህች ግብ ከወራት በፊት የወላይታ ድቻው የመስመር አጥቂ እዮብ ዓለማየሁ በ48ኛው ሰከንድ ካስቆጠራት ግብ የቀደመች በመሆኗ የዓመቱ ፈጣን ግብ ሆና በዕለቱ ዳኛ ተመዝግባለች፡፡

ግቧ ከተቆጠረች በኋላ ጨዋታው ለሁለት ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር። የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ቦታ አላገኘንም በማለት ከጅምሩ ቅሬታን ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን በዚህም የተነሳ የድንጋይ መወራወሮች ከታዩ በኋላ በፀጥታ ኃይሎች ፈጣን እርምጃ ለመቆጣጠር በመቻሉ በድጋሚ ጨዋታው ጀምሯል፡፡ የሲዳማ ቡና የመሀል ሜዳ ብልጫን እንዲሁም የሰላ የአጥቂ ስፍራ በተመለከንበት በዚህ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ በተለይ ከመሀል ሜዳ በሚመሠረቱ ቅብብሎች በመታገዝ በወላይታ ድቻ ላይ ጫናን በተደጋጋሚ አሳድረዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የአበባየው ዮሐንስ እና ዳዊት ተፈራ አስደናቂ ጥምረት ለአዲስ ግደይ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ እንደጉድ መፈንጨት የመሀል ሜዳውን በሚገባ ተቆጣጥሮ ኳስን በማድረስ የተዋጣለት ነበር፡፡ የሲዳማ ቡናን የበሰለ የፊት መስመር መቋቋም ያቃተው የድቻ የመከላከል አደረጃጀት ለተቆጠሩት ግቦች ዋጋን ያስከፈላቸው ሲሆን በመልሶ ማጥቃት በሲዳማ ቡና ላይ የሚፈጥሩት እንቅስቃሴ ግን አስፈሪ ነበር፡፡ በተለይ መሀል ሜዳ ላይ የተሰለፈው እድሪስ ሰዒድ ከባዬ ገዛኸኝ ጋር በቅንጅት አልፎ አልፎም ቢሆን ለጦና ንቦቹ መነቃቃት ሲፈጥሩ አይተናል፡፡

ለዚህም ማሳያ እድሪስ ሰዒድ ወደ ቀኝ አድልቶ በረጅሙ የሰጠውን ባዬ ገዛኸኝ ተቆጣጥሮ ሁለት ጊዜ ገፋ አድርጎ ከርቀት ሲመታ መሳይ አያኖ በግሩም ሁኔታ ያወጣበት ሙከራ ይነሳል፡፡ ከዚህ ሙከራ በኃላ በፍጥነት ወደ ድቻ ግብ ክልል የደረሱት ባለሜዳዎቹ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በፈጠረው ስህተት አዲስ ግደይ አግኝቶ ለዳዊት ሰጥቶት አማካዩ በቀጥታ ሲመታ ለጥቂት የወጣችበት ሌላኛዋ የሲዳማ ሙከራ ነበረች፡፡ ባለፉት ጨዋታዎች የቸርነት ጉግሳን እና እዮብ አለማየሁን የግራ እና ቀኝ ቦታን ለመጠቀም ቢያስቡም ያልተሳካላቸው እንግዶቹ በሌላኛው አማራጭ ባደረጉት ከመሀል ሜዳ በሚነሳ ቀጥተኛ ኳስ ግብ አስቆጥረዋል፡፡ በ19ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ የነበረው እድሪስ ሰዒድ የመሀል ሜዳ ጨረሩ ላይ ከቆመበት ቦታ ትንሽ ኳሷን ገፋ በማድረግ የመሳይ አያኖን አቋቋም ስህተት አይቶ እጅግ ግሩም ግብ ከመረብ አሳርፎ ድቻን አቻ አድርጓል፡፡

ግብ ካስተናገዱ በኃላ ወደ ጨዋታው የተመለሱት ሲዳማ ቡናዎች በድቻ ላይ ብልጫን ወስደዋል፡፡ በይበልጥ በቅብብል ስኬታማ የነበሩት ሲዳማዎች መሪ ያደረጋቸውን ግብ አግኝተዋል፡፡ በ25ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ የተነሳችሁን ኳስ አዲስ ግደይ እና ዳዊት ተፈራ እየተቀባበሉ ወደ ሳጥን ከተጠጉ በኃላ አዲስ በቶሎ ለዳዊት ሰጥቶት ዳዊትም ከመረብ አሳርፎ ሲዳማን ወደ 2-1 መሪነት አሸጋግሯል፡፡ ወላይታ ድቻዎች በእድሪስ ሰዒድ እና ባዬ ገዛኸኝ ጥረት ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ዕድል ቢያገኙም ከመረብ ማዋሀድ ግን ተስኗቸዋል፡፡ በተለይ ባዬ ገዛኸኝ በፈጠረው መልካም አጋጣሚ ቸርነት ጉግሳ አግኝቶ በመቻኮል ያመከናት የምታስቆጭ ነበረች፡፡

ከዕረፍት መልስ ሲዳማ ቡና አሁንም ልክ በመጀመሪያው አጋማሽ የተጠቀመውን የማጥቂያ መንገድ በደንብ ያስቀጠለበት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ግብ ሲቆጠርባቸው ብቻ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ለማድረግ የሚታትሩበት ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ መዳከሞች ታይተውበት የነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ ከአዲስ ግደይ በነበረው ተግባቦት አስደናቂ አቋሙን ያሳየበት ነበር፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ አራት ያህል ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ በቀኝ የወላይታ የግብ ክልል የተገኘን የቅጣት ምት ለሲዳማ የመሀል ሜዳ ጨዋታ ማማር አስተዋፅኦው የጎላ የነበረው አበባየው ዮሀንስ በረጅሙ ወደ ግብ ሲያሻማ ሀብታሙ ገዛኸኝ የወላይታ ድቻን የተከላካይ መስመር አጠባበቅ ስህተት በሚገባ ተጠቅሞ በግንባር በመግጨት የሲዳማን ሦስተኛ ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡

ሲዳማ ቡናዎች ምንም እንኳን ከፊት አስፈሪ መሆናቸውን ብናይም ኃላ ላይ ግን በሚፈጠሩ ጥቃቅን ስህተቶች ለወላይታ ድቻ የመልሶ ማጥቃት ተጋልጠዋል፡፡ በተለይ ባዬ ገዛኸኝ ከመሀል አልያም ከቀኝ እየተነሳ ሲሞክራቸው የነበሩት እና እድሪስ ሰዒድ ከግብ ጠባቂው መሳይ ጋር አንድ ለአንድ አገናኝቶት ባዬ ገዛኸኝ አስቆጠረ ሲባል ያሳቀፋት ክስተት ለድቻ እጅግ የምታስቆጭ ሆና ስታልፍ ቡድኑም ተደጋጋሚ የአጨራረስ ድክመቱ ዋጋ አስከፍሎታል። በ66ኛው ደቂቃ መሀል ሜዳ ላይ አበባየው ዮሀንስ ኳስን መስርቶ ከአዲስ ግደይ ጋር በፈጠረው ሂደት አዲስም ነፃ ቦታ ለነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ ሰጥቶት ሀብትሙ በድንቅ አጨራረስ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ግብ አግብቷል፡፡ ከወትሮው በተለየ መልኩ በእድሪስ እና ባዬ ላይ ጥገኛ የመሰሉት ወላይታ ድቻዎች 77ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ፀጋዬ ብርሀኑ ከቀኝ በኩል መሬት ለመሬት ሲያሳልፍ ባዬ ገዛኸኝ ነካ ብቻ በማድረግ ከኃላው ለነበረው እድሪስ ሰይድ ለቆለት አማካዩም ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አክሎ ልዩነቱን 4-2 እንዲሆን አስችሏል፡፡

የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች ተጠቅመው ግብ ለማስቆጠር ትግል ውስጥ የገቡት ወላይታ ድቻዎች በፀጋዬ አበራ እና ነጋሽ ታደሰ አማካኝነት እጅጉን ለግብ ቀርበው የነበረ ቢሆንም አንዱን በግብ ጠባቂው መሳይ ሲመለስባቸው አንደኛዋ የላይኛውን የግብ ብረት ገጭታ ወጥታለች፡፡ ሆኖም የመከላከል አደረጃጀታቸው ተዳክሞ የታየው ድቻዎች አምስተኛ ግባቸውን አስተናግደዋል፡፡ 83ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ ግደይ አቀብሎት ሀብታሙ ገዛኸኝ ለሲዳማ ቡና የማሳረጊያ አምስተኛ

ዋን ግብ ሲያስቆጥር ለራሱ ደግሞ ሐት-ትሪክ ሰርቷል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በጭማሪ አራት ደቂቃ ውስጥ የሲዳማ ቡናው ተከላካይ ክፍሌ ኪአ በእድሪስ ላይ በሳጥን ውስጥ የሰራውን ጥፋት ተከትሎም የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ባዬ ገዛኸኝ ወደ ግብነት ለውጧት ጨዋታው በሲዳማ ቡና 5-3 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

©ሶከር ኢትዮጵያ