የፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የሳምንቱ ዓበይት ጉዳዮች ቅኝታችንን ቀጥለን ሌሎች ሊነሱ የሚገባቸው የሳምንቱ ጉዳዮችን እንዲህ ተመልክተኛቸዋል።

👉ዳኞቻችን እና የአዲሱ የጨዋታ ህግ ትውውቅ

የዓለምአቀፉ የእግርኳስ ማኅበራት ቦርድ (IFAB) የእግርኳስ ጨዋታ የሚመራባቸው ህግጋትን የመከለስና የማሻሻያ ስራዎች በተለያዩ ጊዜያት ሲከውን ይስተዋላል። በዚህም መሠረት ባሳለፍነው የፈረንጆች አቆጣጠር ጁን አንድ ጀምሮ በተወሰኑ የጨዋታ ህጎች ላይ ማሻሻያ ማድረጉ ይታወሳል። ከአስራ ሰባቱ የጨዋታ ህጎች ላይ ወደ ስምንት በሚጠጉት ላይ ማሻሻያዎች ሲያደርግ በዚህም መሠረት ከዚህ ቀደም ከጨዋታ ውጭ የሆነን ኳስ ዳግም ወደ ጨዋታ በመልስ ምት ሲጀምር የኳሱ ባለቤት ቡድን ተጫዋቾች ከአስራ ስድስት ከሃምሳ ውጭ ሆነው ኳስን እንዲቀበሉ ያስገድድ የነበረው የጨዋታ ህግ ማሻሻያ ተደርጎበት የኳሱ ባለቤት ቡድን ተጫዋቾች የገዛ ሳጥናቸው ውስጥ ገብተው ኳስን መቀበል እንደሚችሉ መደንገጉ ይታወቃል።

በተያያዘም የተቃራኒ ቡድን ተጫዋች ኳሱ ተነክቶ ወደ እንቅስቃሴ እስካልገባ ድረስ ወደ ሳጥን ውስጥ መግባት ስለመከልከላቸው ይደነግጋል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ቡና ከስሑል ሽረ ጋር ባደረጉት ጨዋታ 70ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ተክለማርያም ሻንቆ በሳጥኑ ውስጥ ለሚገኙት ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ተጠቅሞ ኳሱን ከማስጀመሩ በፊት የስሁል ሽረው የመስመር አጥቂ ዲዲየ ለብሪ ኳሱ ወደ እንቅስቃሴ ባልገባበት ሁኔታ በኢትዮጵያ ቡና ሳጥን ውስጥ ገብቶ ኳሱን ለማቋረጥ በተጠንቀቀ በተገኘበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ዳኛው የሽረውን ተጫዋቾች ከሳጥን እንዲያስወጣው በመንገር ኳሱን ለመጀመር በማቅማማቱ በዕለቱ አልቢትር የቢጫ ካርድ ሰለባ መሆኑ መነጋገርያ የነበር ክስተት ነበር።

ይህ ሒደት በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ኢትዮጵያ ቡና ከወልዋሎ በነበራቸው የምድብ ጨዋታ ላይ በተመሳሳይ መሰል የህግ አተረጓገም ክፍተቶች እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። በመሆኑም የሚመለከተው አካል በተሻሻሉት የጨዋታ ህጎች ዙርያ ለዳኞች ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎች ከማዘጋጀት አልፎ ለስፖርት ቤተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ላይ መሥራት ይኖርበታል።

👉አዳማ ከተማ በስተመጨረሻም አዲስ ማልያ ተጠቅሟል

ላለፉት ጥቂት ዓመታት በተለመደው ቀይ በጥቁር እንዲሁም ነጭ መለያ ይታወቁ የነበሩት አዳማ ከተማዎች ከረጅም ጊዜያት በኋላ በዚህኛው ሳምንት ቡድኑ ከፋሲል ከተማ ጋር በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ ላይ ሎሚ ከለር በጥቁር በሆነ አዲስ ትጥቅ ብቅ ብለዋል።

በፋይናንስ እጥረት ክፉኛ ሲሰቃይ የከረመው ቡድኑ ከዩናይትድ ቢቨሬጅ ኩባንያ ጋር የስፓንሰር ሺፕ ውል በይፋ ለመፈራረም ቀናትን እየተጠባባቀ የሚገኝ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ጅማሮ በቡድኑ አባላት ከፍተኛ ቅሬታ ይነሳበት የነበረውን የትጥቅ ችግር በተወሰነ መልኩ የተፈታ ይመስላል።

ይህ በመጪው ሀመስ ይፈረማል ተብሎ የሚጠበቀው የስፖንሰር ሺፕ ውል ስምምነት ፈርጀ ብዙ የክለቡን ችግሮች ለመፍታት የሚኖረው ሚና ላቅ ያለ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በተመሳሳይ በትጥቅ ችግር የደጋፊዎች መለያ ላይ ፕላስተር እየለጠፉ ሲገለገሉ የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች በተመሳሳይ በሁለተኛው ዙር በአዲስ መለያ ብቅ ብለዋል።

👉የሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ክስተቶች …

በዚህ ሳምንት ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ በሀዋሳ ስታዲየም ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 5ለ3 ሲያሸንፍ የሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ከሚችለው አቅም በላይ ተገኝተው የተከታተሉ ሲሆን በርካታ የሚባሉ ደግሞ ቦታ አጥተው ጨዋታውን ሳይመለከቱ በጊዜ ወደ የመጡበት ተመልሰዋል፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይ ትኩረት ከሳቡ ነገሮች መካከል የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ቅሬታ ይነሳል። በጨዋታው ላይ ክብር ትሪቡኑ ግማሹ ለኛ ሲገባን የናንተን ደጋፊዎች ብቻ አስቀምጣችዋል በማለት ከጨዋታው መጀመር ቀደም ብሎ ቅሬታቸውን ያሰሙ ሲሆን ቦታውንም ማግኘት ሳይችሉ የቀሩበት መንገድም አብዛኛዎቹን ያስከፋ ነበር፡፡ 

ሌላው በዚህ ውጥረት በነገሰበት ጨዋታ ላይ በተወሰነ መልኩ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ተስተውሏል፡፡ ጨዋታው እንደተጀመረ አዲስ ግደይ በሰከንዶች መሀል ጎል ካስቆጠረ በኃላ  የድንጋይ  መወራወሮች የታዩ ሲሆን የፀጥታ አካላት በፍጥነት ተቆጣጥረው ወደ ሰላም መልሰውታል፡፡

በዚህኛው ጨዋታ ላይ ሌላው የታዘብነው ጉዳይ  በአጥር ሽቦ ውስጥ ከዳኞች እና ከጋዜጠኞች እንዲሁም ከሚመለከታቸው ውጪ በርካታ ደጋፊዎች ገብተው መታየታቸው የወላይታ ድቻ ተጠባባቂ ስፍራ ላይ ተቀምጠው የነበሩ በተለይ የቡድን መሪው ወደ ዕለቱ ኮሚሽነር በመሄድ እንዲወጡ ካልሆነ በዚህ ሒደት መጫወት እንደማይችሉ በመግለፅ ስሞታን ቢያሰሙም ተቀባይነት ሳያገኙ ጨዋታው ተጀምሯል፡፡

👉የባህርዳር ከተማ መልካም ተሞክሮ

የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ማኅበር የቡድኑን ባለውለታዎች እውቅና በመስጠት ረገድ ከየትኛውም ደጋፊ ማኅበር በተሻለ በዘንድሮው የውድድር ዘመን እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

በዚህኛው ሳምንት ቡድኑ በሜዳው ጅማ አባጅፋርን አስተናግዶ ከረታበት ጨዋታ ጅማሮ በፊት ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ በማሳደግ እና ዓምና በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን ላስቻሉት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው የማስታወሻ ስጦታ ሲያበረክቱ በተመሳሳይ ለቀድሞው የቡድኑ ተጫዋቾች ለነበሩት እና በአሁኑ ሰዓት በጅማ አባ ጅፋር እየተጫወቱ ለሚገኙት ኤልያስ አህመድ፣ አሌክስ አሙዙ፣ ከድር ኸይረዲን እና ሀብታሙ ንጉሴ እንዲሁ የምስጋና እውቅና ሰጥተዋል።

መሰል ሒደቶች ዘንድሮ በተደጋጋሚ በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም በክለቡ የደጋፊ ማኅበር አመራሮች ሲደረጉ የተመለከትን ሲሆን ይህን በእግርኳሳችን ያልተለመደውን የመመሰጋገን ልምዳችን ለማሻሻል ተምሳሌታዊ ተግባር በመሆኑ ሊበረታቱ ይገባል።

መቐለ 70 እንደርታ፣ ፋሲል ከነማ፣ አትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሌሎች ይህን ተግባር ሲፈፅሙ የሚታዩ ክለቦች ናቸው።

👉የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች ተቃውሞ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት መርሃግብር ከሁለት ተከታታይ የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን በቅጣት ምክንያት ከሜዳቸው ውጪ በሀዋሳ አከናውነው የተመለሱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሜዳቸው በመቐለ 70 እንደርታ ሽንፈት አስተናግደዋል።

በ35ኛው ደቂቃ ሆሳዕናዎች “የመቀለ ተጫዋች ኳስ በእጅ ነክቷል፤ የፍፁም ቅጣት ምት ይገባናል” በሚል ጨዋታውን የመሩት አልቢትር ላይ ከፍ ያለ ተቃውሟቸው በተለያዩ መንገዶች አሰምተው ጨዋታው ከተወሰኑ ግርግሮች በኃላ ቢቀጥልም በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ሀዲያዎች ከቅጣት ምት የተሻማችውን ኳስ ገጭተው በማስቆጠር ደስታቸውን እየገለፁ ባለበት ወቅት ረዳት ዳኛው ኳሷን የገጫት ተጫዋች ከጨዋታ ውጭ ነው በሚል ግቧን በመሻራቸው የተከፉት የሆሳዕና ደጋፊዎች የተለያዩ ቁሶችን ወደ ሜዳ በመወርወራቸው የተነሳ ጨዋታው ለአምስት ያክል ደቂቃዎች ተቋርጧል። በዚህም የመቐለው የህክምና ባለሙያ ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ደርሶበት የህክምና እርዳታ ሊደረግለት ችሏል።

መሰል ክስተቶች በአቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ሲከሰቱ የመጀመሪያ ባይሆንም የክለቡ ደጋፊዎች የቀደሙት ድርጊቶቻቸው ካስከተለው መዘዝ ግን አሁንም መማር ይገባቸዋል።

ቡድናቸው በወራጅ ቀጠና ውስጥ በመዘፈቁ ቅር የተሰኙት የክለቡ ደጋፊዎች መሰል ድርጊቶች ክለቡን ለቅጣት ከመዳረግ በዘለለ ክለቡ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ላይ ከኃላ ሆነው ብርታት መስጠት የሚገባቸውን የደጋፊዎቹን ጥቅም በገለልተኛ ሜዳ በመጫወት እንዳያገኝ ከማድረግ ውጭ የሚፈይደው ነገር ባለመኖሩ በሰከነ መንገድ የክለባቸውን እጣ ፈንታ ለማቃናት ከክለቡ አመራሮች እና ተጫዋቾች ጋር በጋራ ሆነው መስራት ይኖርባቸዋል።

👉የዓባይ ግድብ እና የዓድዋ ተጓዥ ደጋፊዎች

ከሰሞኑ በሀገሪቱ ከፍተኛ መነጋገርያ የሆነው የዓባይ ግድብ ጉዳይ በተለያዩ የሊጉ ጨዋታዎች ላይ በደጋፊዎች ዘንድ ተንፀባርቋል። በተለይም በድሬዳዋ ስታዲየም እና አዲስ አበባ ስታዲየም ደጋፊዎች ስለ ጉዳዩ የሚገልፁ የተለያዩ ፅሁፉች የታዩ ሲሆን በተጨማሪም የተለያዩ ከጉዳዮ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ዜማዎች በስታዲየም ውስጥ ተደምጠዋል።

ሌላኛው ደግሞ በቅርቡ በተከበረው የዓድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ በጉዞ ዓድዋ ላይ የተሳተፉ ሁለት እንስት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ክለባቸውን ስላስተዋወቁ የክለቡ የበላይ ጠባቂ አቶ አብነት ገ/መስቀል የምስጋና እና የእውቅና ሽልማት በትናንቱ ጨዋታ ላይ አበርክተውላቸዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ