ሪፖርት | አዳማ ከተማ ወልቂጤን አሸንፏል

17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በቅጣት ምክንያት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ አዳማ ከተማን ያስተናገዱት ወልቂጤ ከተማዎች እጅግ ደካማን እንቅስቃሴ ባሳዩበት ጨዋታ በአዳማ ከተማ የ2ለ0 ሽንፈት ደርሶባቸዋል።

ባለሜዳዎቹ ወልቂጤዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን ከረታው ስብስብ ውስጥ ሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ በዚህም ዐወል ከድር፣ ፍፁም ተፈሪ እና እዩኤል ሳሙኤል በዛሬው ጨዋታ በመጀመሪያው አሰላለፍ ሲካተቱ በአዳማዎች በኩል በፋሲል ከተማ ከተሸነፈው ቡድን ውስጥ ተመሳሳይ የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ሱሌይማን መሐመድ፣ ተስፋዬ ነጋሽ እና ብሩክ ቃልቦሬ በመጀመሪያ አሰላለፍ ዳግም የተካተቱ ተጫዋቾች ናቸው።

እጅግ የተቀዛቀዘ መልክ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም በኩል ደካማ እንቅስቃሴን አስተውለናል። የጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የተደረገው በ5ኛው ደቂቃ ነበር። የወልቂጤው አህመድ ሁሴን ያሳለፈለትን ኳስ ጫላ ተሺታ ወደ ግብ ቢልክም ኳሱን ጃኮ ፔንዜ ያዳነበት ሙከራ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር።

በ7ኛው ደቂቃ ግን አዳማ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የተገኘውን ኳስ ከነዓን ማርክነህ ከወልቂጤዎች ሳጥን ግራ ጠርዝ ላይ የይድነቃቸው ኪዳኔን አቋቋም ስህተት ተመልክቶ በግሩም ሁኔታ መቶ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

አልፎ አልፎም ቢሆን አዳማ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት የተሻለ ጥረትን ሲያደርጉ በተስተዋሉበት የመጀመሪያ አጋማሽ ወልቂጤ ከተማዎች በመከላከልም ሆነ በማጥቃት የጨዋታ ሂደቶች እጅግ ተዳክመው ተመልክተናል። በ19ኛው ደቂቃ ፉአድ ፈረጃ ከእጅ ውርወራ የተገኘውን ኳስ የይድነቃቸውን ጎሉን መልቀቅ ተመልክቶ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ወደ ግብ የላካት ኳስ የግቡን ቋሚ ለትማ ልትመለስ ችላለች። በተመሳሳይ በወልቂጤ ከተማዎች በኩል በ26ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን ከእጅ ውርወራ የደረሰውን ኳስ በቮሊ የሞከራት ኳስ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ሊወጣበት ችሏል። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ሙከራዎችን ሳያስመለከት በአዳማ የ1ለ0 መሪነት ሊጠናቀቅ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሸ ጅማሮ ወልቂጤ ከተማዎች የጨዋታውን ውጤት ለመቀልበስ በማሰብ አማካዮቹን ኤፍሬም ዘካርያስ እና አብዱልከሪም ወርቁን በማስገባት የተሻለ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም ኳስን ከማንሸራሸር በዘለለ ወደፊት ሄዶ አደጋ በመፍጠር ረገድ ቡድኑ ያን ያህል አስፈሪ አልነበረም። በ49ኛው ደቂቃ ጫላ ተሺታ በግንባሩ ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ አህመድ ሁሴን ከጃኮ ከፔንዜ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ጃኮ በቀላሉ ካመከነበት እጅግ አስቆጭ አጋጣሚ በቀርም የጠራ የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በአንፃሩ አዳማዎች ግን አልፎ አልፎም ቢሆን ወደፊት በሄዱባቸው አጋጣሚዎች እጅግ አስፈሪ ነበሩ። በ56ኛው ደቂቃ የወልቂጤ ተጫዋቾች ከጨዋታ ውጭ በሚል የተዘናጉትን ኳስ ቡልቻ ሹራ ተፈትልኮ በመግባት ከይድነቃቸው ኪዳኔ ጋር ተገናኝቶ አንጠልጥሎ ለማስቆጠር የሞከረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወደ ውጭ የወጣበት ፤ በ69ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው በረከት ደስታ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የላከው ቅጣት ምት ይድነቃቸው ኪዳኔ ያዳነበት አጋጣሚ እንዲሁ ተጠቃሽ ነበር።

አዳማዎች ይህ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ85ኛው ደቂቃ የወልቂጤ ተጫዋቾች ትኩረት መሉ ለሙሉ በማጥቃቱ ላይ በነበረበት የጨዋታ ቅፅበት የከተበታተነው ወልቂጤ ተከላካይ ጀርባ አዲስ ህንፃ ያሳለፈለትን ኳስ በረከት ደሰታ በግሩም አጨራረስ የቡድኑን 2ለ0 አሸናፊነት ያረጋገጠች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በዚህም ውጤት መሰረት አዳማ ከተማ ደረጃውን ወደ ስድስተኛ ከፍ ሲያደርጉ ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ ወደ ሰባተኛ ደረጃ ሊንሸራተቱ ችለዋል።

©ሶከር ኢትዮጵያ