ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ወልዋሎ

የጦና ንቦች በሜዳቸው ቢጫ ለባሾቹን የሚያስተናግዱበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከደካማው ጉዞ ወጥተው ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ ደረጃቸውን ያሻሻሉት የጦና ንቦች በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ጥለው ከደረጃቸው ላለመውረድ ከዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት ይጠበቅባቸዋል።

የወላይታ ድቻ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ

በሜዳቸው ጥሩ ክብረ ወሰን ያላቸው የጦና ንቦች በሜዳቸው በብዛት እንደሚከተሉት የመስመር ተጫዋቾች በዋነኛነት የሚያሳትፈው የማጥቃት አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ቢገመትም ተጋጣያቸያው ወልዋሎ አፈግፍጎ ይጫወታል ተብሎ ስለሚታመን በጨዋታው ሒደት አጨዋወቱን የሚቀይሩበት ዕድል እንዳለ ይታመናል።

በዚህም ቡድኑ ከባለፉት የሜዳው ጨዋታዎች በተለየ አጨዋወቱን ከመስመር ወደ መሀል ለመሀል የሚደረግ የማጥቃት አጨዋወት ይቀይራል ተብሎ ሲገመት ባለፈው ሳምንት የሲዳማ ቡናን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ለመቋቋም የተቸገው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ግን አሰልጣኙ በልበ ሙሉነት የሚያጠቃ አቀራረብ ይዘው እንዳይገቡ ሊያደርጋቸው ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ በመጀመርያው ዙር ለተከላካዮች ሽፋን በመስጠት የተዋጣለት ተስፋዬ አለባቸው ለሀዲያ ሆሳዕና አሳልፎ የሰጠው ቡድኑ የተጫዋቹን ሚና የሚተካ ሁነኛ አማካይ ካልተካ ከላይ የተጠቀሰው አጨዋወት በጥሩ መንገድ ለመተግበር መቸገሩ አይቀርም። ቡድኑ ያፈገፈገው ተጋጣሚ ለማስከፈት ፈጣሪ አማካዮች ማካተት የግድ ስለሚለው ከአማካዮቹ ጀርባ የቡድኑ ሚዛን የሚጠብቅ ተከላካይ አማካይ ያለው ወሳኝነት የታወቀ ነው።

የጦና ንቦች በነገው ጨዋታ ውብሸት አለማዮን በጉዳት ምክንያት አያገኙም። በአንፃሩ አዲስ ፈራሚዎቹ አበባው ቡታቆ፣ ሚካኤል ለማ እና አማኑኤል ተሾመ ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። ጉዳት ላይ የነበረው ደጉ ደበበም ተመልሷል።

የወልዋሎ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ

በሰባተኛው ሳምንት ድሬዳዋን ካሸነፉ በኃላ ሦስት ነጥብ ለማግኘት የተቸገሩት ወልዋሎዎች ከተከታታይ ሽንፈት እና የአቻ ውጤቶች በኃላ ወደ ድል ለመመለስ አቅደው ወደ ሶዶ አምርተዋል።

በጫና ውስጥ ያሉት እና ከጨዋታው የግድ ነጥብ ፍለጋ ወደ ሶዶ ያመራሉ ተብለው የሚጠበቁት ወልዋሎዎች በጨዋታው ጥንቃቄ የተሞላበት እና አፈግፍጎ በመልሶ ማጥቃት የሚጫወት አቀራረብ ይዘው ይቀርባሉ ተብሎ ሲገመት በአጨዋወቱ ንፁህ የግብ ዕድል ለመፍጠር ግን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱን ከመቼውም ግዜ በላይ የሰመረ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ባለፈው ጨዋታ የ4-1-4-1 አደራደር የነበራቸው ቢጫ ለባሾቹ በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ አደራደር ይኖራቸዋል ተብሎ ሲገመት ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በትኩረት ማጣት እና በተጫዋቾች የግል ስህተት ምክንያት በቀላሉ ግብ ሲያስተናግድ የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸውም በርካታ ለውጦች ይሻል።

በተለይም በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በርካታ ግቦች ያስተናገደው እና በሁለተኛው አጋማሽ የአካል ብቃት ችግሮች የሚታይበት ቡድኑ የተጠቀሱት ችግሮች መቅረፍ ዋነኛ የቤት ስራው መሆን እንዳለበት ይታመናል።

ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሶዶ ይዘዋቸው ካልሄዱት ተጫዋቾች ውጭ በጉዳትም በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም።

የእርስ በርስ ግነኙነት

– ቡድኖቹ በሊጉ አምስት ጊዜ ተገናኝተው አራቱን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ ወልዋሎ አንድ አሸንፏል።

-በሁለቱ ግንኙነት ወልዋሎ አምስት፤ ድቻ አራት ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

መክብብ ደገፉ

ፀጋዬ አበራ- ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ- ያሬድ ዳዊት

በረከት ወልዴ – ተመስገን ታምራት – እድሪስ ስዒድ

እዮብ ዓለማዮህ – ባዬ ገዛኸኝ – ቸርነት ጉግሳ

ወልዋሎ (4-1-4-1)

ዓብዱልዓዚዝ ኬይታ

ገናናው ረጋሳ – ዳዊት ወርቁ – አቼምፖንግ አሞስ – ሳሙኤል ዮሐንስ

ዮናስ በርታ

ኢታሙና ኬይሙኔ – አመለ ሚልክያስ – ያሬድ ብርሀኑ – ራምኬል ሎክ

ጁንያስ ናንጂቡ

© ሶከር ኢትዮጵያ