ቅድመ ዳሰሳ| ስሑል ሽረ ከ ሲዳማ ቡና

ስሑል ሽረዎች ከወራት ቆይታ በኃላ ወደ ሽረ ተመልሰው ሲዳማ ቡናን የሚያስተናግዱበት ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ከውጤታማው የአሸናፊነት መንገድ ከወጡ በኋላ ሦስት ነጥብ ለማግኘት የተቸገሩት ሽረዎች ከወራት በኋላ ወደ ሜዳቸው ተመልሰው በሚያደርጉት ጨዋታ ወደ አሸናፊነት መመለስ የግድ ይላቸዋል።

የስሑል ሽረ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ ተሸነፈ አቻ አቻ አሸነፈ

ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ የመጀመርያ ዙር ውጤታማ ስብስባቸው በተለያዩ ምክንያቶች ያላገኙት ስሑል ሽረዎች ያስፈረሟቸው አዳዲስ ተጫዋቾች ለጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ለቡድኑ ጥሩ ዜና ቢሆንም ወሳኙ ተጫዋቻቸው ነፃነት ገብረመድኅን በቅጣት ማጣታቸው ግን ለአዲሱ አሰልጣኝ መጥፎ ዜና ነው።

በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው የሚታወቁት ስሑል ሽረዎች በአዲሱ አሰልጣኝ ስር የሚከተሉት አጨዋወት ለመገመት ቢከብድም በመጀመርያው ጨዋታዎች ለየት ያለ አቀራረብ ለመከተል ይደፍራሉ ተብሎ አይገመትም። ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት በመጀመርያው ዙር በአጨዋወታቸው ወሳኝ ተጫዋች የነበረው ዓብዱለጢፍ መሐመድ በቅጣት ምክንያት ያላሰለፉት ሽረዎች ተጫዋቹ ከቅጣት መልስ ማግኘታቸው ተከትሎ አስፈሪው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ለመመለስ የሰፋ ዕድል አላቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች በማጥቃቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች በነገው ጨዋታ በተጋጣሚ የመስመር አጨዋወት ላለመጋለጥ የተገደበ እንቅስቃሴ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው ሳምንት የቡድኑ የማጥቃት ክፍል የመራው ብሩክ ሐድሽ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። አማካዩ ነፃነት ገብረመድኅንም በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም። በዚህም አዲስ ፈራሚው ራሂም ኦስማኑ ጨዋታውን በቋሚነት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

የሲዳማ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

አስፈሪ ማጥቃት ጥምረት መገንባት የቻሉት እና ባለፉት አራት ጨዋታዎች በርካታ ግቦች አስቆጥረው ያሸነፉት ሲዳማዎች ግስጋሴያቸውን ለማስቀጠል ወደ ሽረ እንዳስላሴ አምርተዋል።

በፈጣን አጥቂዎቻቸው መሰረት ያደረገ ስል የማጥቃት አቀራረብ ያላቸው ሲዳማዎች በአመዛኙ ዓመቱን ሙሉ ከተከተሉት የተለመደ አጨዋወት ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ አይገመትም። በዚህም ቡድኑ ከፈጣሪ አማካዮቻቸው በሚነሱ የመሬት ለመሬት ኳሶች (Through pass) የግብ ዕድሎች ይፈጥራል ተብሎ ሲገመት በቅርብ ጨዋታዎች እምብዛም ያልተጠቀሙበት የመስመር አጨዋወትም የቡድኑ ሁለተኛ አማራጭ አጨዋወት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ቡድኑ ምንም እንኳ በርካታ የማጥቅያ አማራጮች ቢኖሩትም በመከላከል ላይ ያለው ክፍተት እና መልሶ ማጥቃቶች የመግታት ያለው ደካማ አቅም በነገው ጨዋታ ፈቶ ማግባት ይጠበቅበታል። በርካታ ግቦች አስቆጥረው ባሸነፉባቸው ጨዋታዎች ሳይቀር በቁጥር ቀላል የማይባሉ ግቦች ያስተናገዱት ሲዳማዎች በነገው ጨዋታ የመስመር ተከላካዮቻቸው የማጥቃት ተሳትፎ ይገድባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሲዳማ ቡናዎች በነገው ጨዋታ ዮሴፍ ዮሐንስ እና አዲሱ ቱላ በጉዳት አያሰልፉም በአንፃሩ ጊት ጋትኮችን ከጉዳት፣ ግርማ በቀለን ከቅጣት መልስ አግኝተዋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ ሦስት ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ሲዳማ ሁለቱን ሲያሸንፍ በአንዱ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ ስምንት ሲያስቆጥር ሽረ ደግሞ አራት ማስቆጠር ችሏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ምንተስኖት አሎ

ዐወት ገብረሚካኤል – ዮናስ ግርማይ – አዳማ ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ

ሀብታሙ ሽዋለም – አክሊሉ ዋለልኝ

ዲዲዬ ለብሪ – ያሳር ሙገርዋ – ዓብዱለጢፍ መሐመድ

ራሂም አስማኑ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

አማኑኤል እንዳለ – ግርማ በቀለ – ጊትጋት ኮች – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ – ብርሀኑ አሻሞ – አበባየው ዮሐንስ

አዲስ ግደይ – ይገዙ ቦጋለ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

©ሶከር ኢትዮጵያ