ወልዋሎዎች እስካሁን ወደ ዓዲግራት መመለስ አልቻሉም

ቢጫ ለባሾቹ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባጋጠመው አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ወደ ከተማቸው ማምራት አልቻሉም።

ከምስራቅ አፍሪካ አጎራባች ሀገራት በተነሳው የምድረ በዳ አውሎ ንፋስ ምክንያት ላለፉት ቀናት ሰሜናዊ የኢትዮጵያ ክፍል ከባቢ አየር በአቧራ ተሸፍኗል። በዚህ ምክንያትም በርካታ የአየር በረራዎች ሲሰረዙ ሁለት የፕሪምየር ሊጉ ክለቦችም በሁኔታው ተስተጓጉለዋል። በትናንትናው ዕለት ሲዳማ ቡና በተፈጠረው ሁኔታ መስተጓጎላቸውን መግለፃችን ሲታወስ ዛሬም ባለፈው ዓርብ ወደ ሶዶ አምርተው ከወላይታ ድቻ ጋር የተጫወቱት ወልዋሎዎች በተፈጠረው ሁኔታ እስካሁን ወደ ዓዲግራት ማምራት እንዳልቻሉ ለማወቅ ተችሏል። ቡድኑ ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ድረስ በአዲስ አበባ እንደሚቆይም ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በቀጣይ ቀናት ሁኔታዎቹ በቶሎ የማይስተካከሉ ከሆነም ቡድኑ በቀጣይ ሳምንት ቅዳሜ በሜዳው ከስሑል ሽረ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ሊራዘም ይችላል ተብሏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ