ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ ዘጠኝ – ክፍል አንድ

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ማቅረባችንን ቀጥለን በዛሬው መሠናዶ ምዕራፍ ዘጠኝን ወደ እናንተ ማድረስ እንጀምራለን።


አዲስ የእግርኳስ አጨዋወት ጅምር

አብዛኞቹ የዚህ ዘመን እግርኳስ ተንታኞች የዘርፉን ቀደምት ባለሙያዎች ስጋት በማስተጋባቱ ረገድ ተወቃሾች ሳይሆኑ አይቀርም፡፡ የሚከተሉትን ሁለት ምሳሌዎች እናጢን፦

” ጥድፈት ከልክ ያለፈ እንክብካቤ ይቸረዋል፤ ፈጣንነትም የጥሩ ብቃት መለኪያ- አልፎም ልቆ የመገኘት መገለጫ ተደርጎ ተወስዷል፡፡” – ዊሊ ሜይዝል በ1957 የጻፈው

” ኳስን በፍጥነት ከግብ ክልል ማራቅ…፣ የፍርሃት  መንፈስ ያረበበበት ጨዋታ…፣ የውድቀት ስጋት …፣ ኳስን በቁጥጥር ሥር የማድረግና የመረጋጋት አቅም ማጣት…፣ የተጫዋቾቹን በቆራጥነት የመፋለም ወኔ የማያበርድ፥ የቴክኒክና የፈጠራ አቅማቸውንም የማያዳክም ከፍተኛ ድምጽ የሚሰማበት የድጋፍ ጩኸት…፣…” – ማርቲን ሳሙኤል በ2007 በዘ-ታይምስ ጋዜጣ ላይ የጻፈው

(ይህ ጽሁፍ ከመውጣቱ ሁለት ቀናት በፊት እንግሊዝ በክሮኤሺያ 3-2 ተሸንፋ በ2008ቱ የኦስትሪያና ፖላንድ የአውሮፓ ሃገራት ዋንጫ ውድድር ላይ መካፈል ሳትችል መቅረቷን ልብ ይሏል፡፡)

በእርግጥ ሁለቱም አስተያየቶች በእንግሊዝ እግርኳስ የሚስተዋሉትን መሰረታዊ ጉድለቶች አጉልተው ከማሳየት አኳያ ትክክለኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሃገሪቱ አንድ የአጨዋወት ሥልት ፍሬ-አልባ የመሆን ዕጣ ከገጠመው የችግሩ መንስኤ ለቴክኒካዊ ክህሎት ትኩረት ካለመቸር ጋር ይያያዛል፡፡ ይህ ሃሳብ ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊትም ተነስቶ ነበር፥ ይኸው አሁንም ይነሳል፥ በእነዚህ የዘመናት ጠርዝ መካከል በነበሩት ዓመታትም እንዲሁ ሲያከራክር ኖሯል።

ከፍጥነት ጋር በተያያዘ ግን ቅሬታ የሚያቀርቡት ወገኖች እምብዛም ናቸው፡፡ በሜይዝል እይታ በ1950ዎቹ አጋማሽ የነበረው የእንግሊዝ እግርኳስ እጅግ ፈጣን ከነበረ “በሶስተኛው ሚሊኒየም የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በፕሪምየር ሊጉ የታየውን የፍጥነት ደረጃ ምን ይለው ይሆን?” ያስብላል፡፡ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ የነበረውን እግርኳስ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ስንመለከት ከዘመናዊ የእግርኳስ ጨዋታ አንጻር በዝግታ እንቅስቃሴ የሚካሄድ ጨዋታ መምሰሉን እንረዳለን፡፡ አሁን በዘመናችን ያለው ደግሞ በተለየ ሁኔታ እየፈጠነ እንደሆነም እንገነዘባለን፡፡ የ1950ዎቹን ሃንጋሪዎች አልያም የ1960ዎቹን ብራዚሎች ስንመለከት ተጫዋቾች ኳስን ይዘው ለብዙ ደቂቃዎች መቆየታቸውን እናስተውላለን፡፡ ታዲያ ይህ የሆነው በተጫዋቾቹ የቴክኒክ ብቃት ብቻ አይደለም፡፡ ያንን ቅጽበታዊ የኳስ ቁጥጥር የሚከውኑት በአቅራቢያቸው የሚገኝ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ባለመኖሩ ነው፡፡ ኳስ እግሩ ሥር የያዘ ተጫዋች የመቀባበያ አማራጮችን የሚያጤንበት በቂ ጊዜ አለው፡፡ የጋሪንቻ ወይም የስታንሊ ማቲውስ የድሪብሊንግ ችሎታ በአሁኑ ዘመን የማይታይበት ምክንያት ተጫዋቾች ተሰጥዖው ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም፥ ይልቁንም እነዚህኞቹ ባለክህሎት ተጫዋቾች አብዶዎቻቸው ወይም ድሪብሎቻቸው ውጤታማ እንዲሆን የግድ የሚሹት ሦስት ወይም አራት ሜትር የሚደርስ ርቀት አለ፤ በዚህ ዘመን ይህን የመሮጫ ቦታ የትኛውም ተቃራኒ ቡድን አይሰጣቸውም፡፡ ስለ እውነት ከሆነ “እነ ማቲውስና ጋሪንቻን የመሳሰሉ የቀድሞ ድንቅ ተጫዋቾች በአሁኑ ዘመን እግርኳስ ታላላቅ ተጫዋቾች ሊሆኑ ይችሉ ነበርን?” ተብለን ብንጠየቅ መልሳችን ምናልባት “አዎ!” ሊሆን ይችላል፡፡ ነገርግን እነርሱ ይከውኑ ከነበሩት የድሪብሊንግ ቴክኒክ በተለየ መንገድ ድሪብል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ተጫዋቾች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ቦታ ማነስ፣ የጨዋታው አጠቃላይ ተለዋዋጭ ቅርጽ መጥበብና ተጭኖ የመጫወት ዘይቤ ዘመናዊ እግርኳስን ከጥንቱ የሚለዩ ባህርያት ናቸው፡፡ ለምሳሌ፦ በሆነ ወቅት አንድ ቡድን በተለየ አቀራረብ ከመጣና ስኬታማ ሆኖ ከተገኘ ሌሎችም የዚህን ቡድን መንገድ ይከተላሉ ተብሎ መጠበቁ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ይህ በጣም ተገማች ሐሳብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የተጭኖ መጫወት ዘዴ (Pressing) መስፋፋት ከተለመደው ወጣ ያለና የተለየ አመጣጥ አለው፡፡ ይህ የጨዋታ ሥልት በጀርመን የተተገበረው በቅርቡ 1990ዎቹ ላይ ነው፡፡ አሪጎ ሳኪ በ1980ዎቹ በኤሲ.ሚላን ሲተገብሩት በአዲስ ግኝትነት ሃገሪቱ ጉድ አለች፡፡ ነገርግን <ፕሬሲንግ>ን ሪኑስ ሚሼልስ በአያክስ፣ ቫለሪ ሌቫኖቭስኪ በዳይናሞ ኪዬቭ እንዲሁም ግራሃም ቴይለር በዋትፎርድ ለዓመታት ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡ በ1960ዎቹ መጨረሻ የአርጀንቲናው ክለብ ኢስቱዲያንቴስ ዴ ላ ፕላታ በኦዝቫልዶ ዙቤልዲያ እየተመራ ውጤታማ ጊዜ ሲያሳልፍ <ፕሬሲንግ> የቡድኑ ዋነኛ የአጨዋወት ዘዴ ነበር፡፡ ያም ሆኖ <ፕሬሲንግ> ዩክሬይን ውስጥ በሰራ ሩሲያዊ የእግርኳስ ሊቅ፣ በቀድሞዎቹ የተባበሩት የሶቭየት ህብረት አባል ሃገራት ውስጥ ካልሆነ በቀር በሌላው ዓለም  እምብዛም ስሙ በማይነሳ ታላቅ አሰልጣኝ አማካኝነት የተፈጠረ የእግርኳስ ታክቲካዊ ግኝት ነው፡፡ እስካሁንም ድረስ የእግርኳስ ዝግመታዊ ለውጥ ወጥ ሒደት አላሳየም፡፡ ለጨዋታው እድገት የራሳቸውን ድርሻ  የተወጡ በርካቶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ “የዘመናዊ እግርኳስ አባት” የሚለው ማዕረግ ለአንድ ሰው ብቻ ይሰጥ ከተባለ ከቪክቶር ማስሎቭ በላይ ሊጠቀስ የሚችል ሰው አይኖርም፡፡

ቪክቶር ማስሎቭ በእግርኳስ አጨዋወት አብዮት ያስነሳል ብሎ ማንም አልገመተም፡፡ ያኔ እርሱ በድንገቴ ለውጥ አምጭ አሰልጣኝነት ወይም በሩቅ አሳቢነት የሚፈረጅ አልነበረም፡፡ ይልቁኑ ለእግርኳስ ባለው ጥልቅና የጋለ ስሜት የሚታወቅ ነበር፡፡

” ማስሎቭ ‘አያቴ’ እየተባለ መጠራቱ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ አብዛኞቹ በሥሩ ያለፉ ተጫዋቾችን ሊያደርስ ይችል ይሆናል፡፡ ነገርግን የእነርሱ አያት የመሆን እድሜ ላይ በጭራሽ አልደረሰም ነበር፡፡ ቅጽል ስሙን ያገኘው ኪዬቭ ከመምጣቱ በፊት ይመስለኛል፡፡ በጭራሽ ከእድሜው ጋር በተያያዘ እንዳልተሰጠው ግን አምናለሁ፡፡ ምናልባት መልኩ የአያት ገጽታ አላብሶት ይሆናል፡፡ ደልደል ያለ ሰውነት ያለው፣ ራሰ በራ የሆነ እና ቅንድበ ሙሉ መልክ ነበረው፡፡ የተቀጽላው መሰረታዊ ምክንያት ግን ከገዘፈ ጠቢብነቱ፣ ሰብዓዊ ርህራሄውና ደግነቱ ጋር ሳይያያዝ እንደማይቀር ይገመታል፡፡” ይላል በ1950ዎቹ የዳይናሞ ኪዬቭ ምርጥ አጥቂ የነበረው ሚክሃይሎ ኮማን፡፡

በ1910 በሞስኮው የተወለደው ማስሎቭ የሶቭየትን ሊግ በተጫዋችነት ከቆረቆሩት ወጣቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ በወቅቱ ጠንካራና እምነት የሚጣልበት አማካይ ከመሆኑም በላይ አስገራሚ ቅብብሎችን የመከወን ችሎታም የታደለ ነበር፡፡ ማስሎቭ በ1934 እና 1935 በሞስኮው ሻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃ አግኝቶ በጨረሰው የቶርፒዶ ክለብ አባል ሆኖ አሳልፏል፡፡ በ1936 እና 1939 መካከል በነበሩት ዓመታትም ቡድኑን በአምበልነት መርቷል፡፡ በ1938 በፈረንሳይ በተዘጋጀው አለም አቀፍ የእግርኳስ ውድድር ላይም ቶርፒዶ ዋንጫ እንዲያነሳ አስችሏል፡፡ በ1942 የተጫዋችነት ዘመንኑ ካገባደደ በኋላ የቶርፒዶ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ፡፡ በ1962 ወደ ሮስቶቭ-ና-ዶኑ ከማቅናቱ በፊት ለአራት ጊዜያት ያህል በቶርፒዶ መቆየት ችሏል፡፡ ከእነዚህ ቆይታዎቹ የመጨረሻ በነበረውና በ1957 በጀመረው የአሰልጣኝነት ጊዜው በክለቡ  እጅግ ስኬታማ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በሶቭየት ሊግ ለሁለት ጊዜያት ያህል ቡድኑ ሁለተኛ ሆኖ እንዲጨርስ ከማስቻሉም በላይ በ1960 ቶርፒዶ የመጀመሪያ የሊግ ድል እንዲጎናጸፍ አድርጓል፡፡ በ1964 ወደ ዳይናሞ ኪዬቭ ካመራ በኋላ ደግሞ ሃሳቦቹን በነጻነት ወደ ተግባር የሚመነዝርበትን የአሰልጣኝነት እድል አገኘ፡፡ በዚህም ሳቢያ የሶቭየት እግርኳስ ማዕከልነትን ከሞስኮው ነጥቆ ወደ ዩክሬናውያኑ ዋና ከተማ አሻገረ፡፡

ቪክቶር ማስሎቭ ገራገር ባህርይ የነበረው ቢሆንም ያን አይነት ጀብዱ ለመፈጸም ከፍተኛ የስብዕና ጥንካሬ እንዲሁም በእግርኳሱ ውስጥ የሰፈነውን ፓለቲካዊ ሽኩቻ የመቋቋም አቅም ነበረው፡፡ ለአብነት ያህል እንኳ የያኔውን የዩክሬይን ኮሚዩኒስት ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ የርዕዮተ ዓለም ክፍል ተጠሪ ከነበረው ቮሎድሚር ሼርብስኪ ጋር ለመወዳጀት ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ (ቫለሪ ሌቫኖቭስኪም ለእግርኳስ ሲል ሼርብስኪ በዩክሬን የፓርቲው ሊቀመንበር ከሆነ በኋላ ጥብቅ ቁርኝት ፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡) ዳይናሞዎች ተጫዋች ለመመልመል በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ይጓጓዙ ነበር፡፡ ለምሳሌ፦ በ1950ዎቹ አብዛኞቹ የክለቡ አባላት ከዛካርፓቲያ ግዛት የመጡ ነበሩ፡፡ ነገርግን በማስሎቭ ዘመን አብዛኞቹ የሃገሪቱ ምርጥ ተጫዋቾች ወደ ዳይናሞ መጉረፍ ጀመሩ፡፡ ክለቡ ለተጫዋቾች የሚያቀርበው በኪዬቭ የተሰሩ ዘመናዊ መኖሪያ አፓርትመንቶች ብዙዎችን የማማለል ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ጥቅማጥቅሞችና የመሳሰሉት መደለያዎች የሚቀርቡት በፓርቲው አመራሮች ይሁንታ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ማስሎቭ ነጻነቱን አሳልፎ ላለመሥጠት ጠንካራ አቅምና ጽኑ አቋም ነበረው፡፡ በኪዬቭ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያለው ቪክቶር በሆነ አጋጣሚ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ረዳት በመሆን የሚያገለግል ሰው ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ ላሳየው ደካማ ብቃት ግሳጼ ለማቅረብ በዕረፍት ሰዓት ወደ መልበሻ ክፍል ይመጣል፡፡ አሰልጣኙ የመልበሻ ክፍሉ በር ላይ ቆሞ ሰውዬው ወደ ውስጥ እንዳይገባ እየከለከለው ” በነገው ዕለት ነጻ ነኝ፤ ብዙም ሥራ አይበዛብኝም፡፡ እዚያው መጥቼ አለቃህን አገኘዋለሁ፤ ለጥያቄዎቹ በሙሉ ምላሽ እሰጠዋለሁ፡፡ እናም እባክህ አሁን በሩን ለቀህ በመጣህበት ልትመለስልኝ ትችላለህን?” በማለት ሸኘው፡፡ ምናልባት የተረኩ እርግጠኝነት አጠያያቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ገጠመኝ በየትኛው ጨዋታ እንደተከሰተ አስማሚ መረጃ የለም፤ በነገሩ የትኛው የፓርቲ ሰው እንደተሳተፈም በቂ ማስረጃ አልቀረበም፡፡ ነገርግን የትርክቱ በተደጋጋሚ መነገር ከጀርባ የተደበቀ እውነታ ስለመኖሩ ማሳያ ይሆናል፡፡

” አያታችንን (ማስሎቭን መሆኑ ነው፡፡) መጀመሪያ በመልካም ስብዕናው አደነቅነው፤ ከዚያ ደግሞ በአሰልጣኝነቱ ማረከን፡፡” ይላል ከ1964-1967 ድረስ ዳይናሞ ኪዬቭን በአምበልነት የመራው አንድሪይ ቢባ፡፡ ሲቀጥልም ” እርሱ በቀዳሚነት እኛን የሚመለከተው ከጠንካራና ደካማ ጎናችን ጋር እንደ ሰው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እንደ እግርኳስ ተጫዋች ያየናል፡፡ ከተጫዋቾቹ ጋር ግንኙነት የሚመሰርተው በዚህ መልኩ ነው፡፡ በጣም ስለሚታመንልን እርሱ ላይ ምንም አይነት መጥፎ ስሜት ተሰምቶን አያውቅም፡፡ ማስሎቭ እኛን ያምነናል፤ እኛም እንዲሁ ለእርሱ ከልባችን እንታመናለን፡፡” በማለት አሰልጣኙ ለተጫዋቾቹ ያለውን አመለካከት ያስረዳል፡፡

አንድሪይ ቢባ ስለ ቪክቶር ማስሎቭ የተናገረው የመተማመን ግንኙነት የሚሰራው የአሰልጣኙን ፈለግ በሚከተሉት ተጫዋቾች ዙሪያ ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በ1958 በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ወደ ወኅኒ ቤት ከመውረዱ በፊት በማስሎቭ ሥር የታላቁ ቶርፒዶ ቡድን አባል የነበረው ኤድዋርድ ስትሬልዞቭ የሚያስታውሰው ሌላኛውን የአሰልጣኙ ባህርይ ነው፡፡ ” ማስሎቭ ማንኛውንም ተጫዋች ካልወደደ ጥላቻውን ለመደበቅ ሲጥር አይታይም፡፡” ይላል፡፡

በሁለቱም ገጽታዎቹ አብረውት ለሰሩ ሁሉ ማስሎቭ የተከበረና የተምሳሌታዊ ስብዕና ባለቤት መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ” የቅድመ ጨዋታ ትዕዛዛቱ ከአምስት ደቂቃዎች በላይ አይፈጁም፤ ብዙ ነገሮችን በአግባቡ የማስታወስ ችግር ነበረበት፡፡ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ስሞች ሳይቀር ይምታቱበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሁሌም እጥር ምጥን ባለ ገለጻ የተቃራኒ ቡድን ጠንካራ ጎንን በምን መልኩ እንደምንመክት ያብራራልናል፡፡ ልባችንን ለመንካት አዘወትሮ የሚያነሳት አባባል አለችው፡፡

‘ ዛሬ ልክ እንደ አንበሳ ብርቱ፣ እንደ አጋዘን ፈጣን፣ እንደ ግስላ ንቁና ቀልጣፋ መሆን አለባችሁ፡፡’ እኛም የምንችለውን ያህል ምርጥ ሆነን ለመገኘት መትጋት የዘወትር ተግባራችን ነበር፡፡” ሲል ቢባ ስለአሰልጣኙ ማስሎቭ ያወጋል፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡