ሀዲያ ሆሳዕና ስታዲየሙን ሊያድስ ነው

ቅሬታን ሲያስተናግድ የከረመው የሀዲያ ሆሳዕናው አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታድየም ሙሉ በሙሉ የማሻሻያ ግንባታ ሊደረግበት ነው፡፡

በፕሪምየር ሊጉ በተደጋጋሚ በክለቦች ቅሬታ ከሚቀርብባቸው ሜዳዎች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ስታዲየም በተለይ አመቺ ያልሆነው የመጫወቻ ሳሩ በዋናነት ክለቦች አቤቱታ ሲያሰሙበት የነበረ ሲሆን ለተመልካቾች ምቹ መቀመጫ በበቂ ሁኔታ አለመገንባቱ የቅሬታ መነሻ ጉዳዮች እንደነበሩ በዚህ ዓመት በተደጋጋሚ ሲነሱ ተመልክተናል፡፡ በሊጉ ደካማ የውድድር ዓመትን ሲያሳልፍ የነበረው ክለቡ ሊጉ በኮሮና ቫይረስ መቋረጥን ተከትሎ ከመውረድ ስጋት በመትረፉ በቀጣዩ ዓመት ምቹ ስታዲየምን ለውድድር ለማቅረብ ከአሁኑ ወደ ስራ ለመግባት መዘጋጀቱን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ማዶሮ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ስራ አስኪያጁ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቁመዋል፡፡ “የዞኑ መንግሥት እና የክለቡ ቦርድ በጀት እንዲለቅ ጠይቀናል። ለዚህም በቂ ምላሽን አግኝተናል። በአዲስ መልክ በተለይ ትኩረት ሰጥተን የመጫወቻ ሳሩን የበፊቱን አንስተን በአዲስ መልክ ለመስራት ዝግጅት አጠናቀናል። የስታዲየሙ አጥር ግንባታም ተጀምሯል። የክልሉን መንግስት ወደ 8 ሚሊዮን ብር የጠየቅን ሲሆን ይህም ገንዘብ ገቢ ሲሆን ለትሪቡን ማስፋፊያ ግንባታ እንዲውል አስበናል።” ብለዋል።

በተያያዘ የደመወዝ ክፍያ ቅሬታ በተጫዋቾቹ የሚነሳበት ክለቡ በቅርቡ በድጎማ ከሚመጣ ገንዘብ ወርሀዊ የቡድኑን አባላት ደመወዝ ለመሸፈን ጥረት ላይ እንደሆኑም ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ