በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ የእግርኳሱ አካላት በጎ ተግባር ሊከውኑ ነው

በሀዋሳ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦች እና ከከተማዋ የፈሩ የእግር ኳስ ታዋቂ ተጫዋቾች አሰልጣኞች እና ደጋፊዎች ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ ለአረጋውያን ገቢ የማሰባሰብ ስራን በይፋ ይጀምራሉ፡፡

በእግር ኳሱ ዙሪያ ያሉ ክለቦች፣ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች እና አመራሮች በወረርሺኙ ዙርያ የነቃ ተሳትፎን እያደረጉ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ ውስጥ የሚገኙ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ የክለብ ደጋፊዎች እና በእግር ኳሱ ላይ እየሰሩ ያሉት በሙሉ አሳታፊ ያደረገ አረጋውያንን የመርዳት ዘመቻ ከፊታችን ቅዳሜ ማለዳ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል። በኮሚቴ ደረጃ የተቋቋመው ስብስብ አባል የስፖርት ጋዜጠኛ ሰለሞን አባቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አቅመ ደካማ የሆኑ ማኅበረሰብን በግንባር ቀደምትነት ታሳቢ ያደረገ ፕሮግራም እንደሆነ ገልፆል፡፡

“ቅዳሜ በከተማው ከንቲባ እውቅና ያገኘ ለአረጋውያን እርዳታ ማሰባሰብን አላማ ያደረገ ፕሮግራም ይደረጋል። በዚህ ገቢ ማሰባሰብ ላይ የሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች የራሳቸውንን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከቁሳቀስ እስከ ገንዘብ ማሰባሰብ ድረስ ይሰራል። የሀዋሳ ከተማ እና የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ማኅበርም በዚህ ላይ ጉልህ ተሳትፎን ያደረጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሀዋሳ ውስጥ የሚገኙ የጤና እግር ኳስ ቡድኖች በዚህ በጎ ተግባር ላይ የራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ይደረጋል።” ብሏል፡፡

ከዋናው ፕሮግራም ውጪ ከነገ ጀምሮ የቅስቀሳ ተግባራት እና ስለ ኮሮና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራን በተለይ ታዋቂ በሆኑ የሀገራችን እና የከተማዋ ስፖርተኞች ይሰራል ሲል ጋዜጠኛው የገለፀ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የደም ልገሳ፣ እጅ ማስታጠብ በሜዳ ላይ አዝናኝ የሆኑ ፕሮግራሞች ለማድመቂያነት ታስቧል ብሏል። ሁሉም የዚህን መልካም ተግባር ለመደገፍ የራሱን ድርሻ መወጣትም አለበት ሲልም ሀሳቡን ቋጭቷል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ