“የ2013 ውድድር ስጋት ላይ ነው” መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ

የ2012 የፕሪምየር ሊግ ውድድሮችን ሙሉ በሙሉ የሠረዘው የሊግ ኩባንያ የ2013 ውድድሮችን ለማድረግ ስጋት ላይ እንዳለበት እየተናገረ ይገኛል።

በኮሮና ወረርሺን ምክንያት የተቋረጡ የሊግ ውድድሮች ቀጣይ እጣ ፋንታ ላይ ውይይት ያደረገው የሊግ ኩባንያው በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት ሀገራችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ስለምትገኝ እና ወረርሽኙ እንደ ሀገር መቆጣጠር እንደሚቻል ማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ የ2012 የሊግ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ተሰርዘዋል። በዚህም መሠረት በየትኛውም ሊግ ሻምፒዮን እንዲሁም ወራጅ የሌለ በመሆኑ ቀጣይ ዓመት በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴርሽን ካፕ ኢትዮጵያን የሚወክል ክለብ አይኖርም በማለት ማሳወቁ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ የተለያዩ አውንታዊም አሉታዊም ሀሳቦች እየተንፀባረቁ ይገኛል። ይህን አስመልክቶ ትናንት በፌዴሬሽኑ ፅፈት ቤት አዳራሽ የሊግ ኩባንያው ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ካነሷቸው በርካታ ሀሳቦች መካከል የ2013 ውድድርን ስጋት ውስጥ የሚከት አስተያየት ሰጥተዋል።

“የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በዝርዝር በሰጠን መነሻ ሀሳብ መሠረት ሰኔ፣ ሐምሌ እና ነሐሴ የችግሩ ቁልፍ ወራቶች ናቸው። ስለዚህ መስከረም እና ጥቅምት ይህ ችግር ይቃለላል ብሎ ከወዲሁ መገመት ትክክል አይደለም። ይሁን እንጂ ዛሬ የምንነሳው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚያልቀው ነሐሴ ቢሆንም መንግስት ሁኔታውን አይቶ ሐምሌ ወይም ነሐሴ ሊያራዝመው ስለሚችል ከተራዘመ የመንግስትን ፖሊሲ ተቀብለን እናስፈፅማለን። ስለሆነም የ2012 ብቻ ሳይሆን የ2013 የውድድር ዘመን እንደከዚህ ቀደሙ በሁለት ዙር ላይካሄድ ይችላል። ያኔ ተጨባጩ ሁኔታ እንደሚፈቅደው በአንድ ዙር ሆኖ አንድ ዙሩም በጥሎ ማለፍ መልክ አድርገን ክለቦች አስቀድመው አውቀውት ተስማምተንበት በአንድ ዙር ቻምፒዮኑ፣ ወራጁ ይኑር ከተባለና ከተስማማን ወደ ፊት የሚሆነውን ለመነጋገር አስበናል። አሁን ያየነው እስከ ነሀሴ ድረስ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድረስ ነው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ