አምስት ተጫዋቾችን በጨዋታ መቀየር የሚያስችለው ህግ ዛሬ ተቀባይነት አገኘ

ከቀናት በፊት በፊፋ አማካኝነት የቀረበው “የአምስት ተጫዋቾች በጨዋታ ይቀየሩ” ሃሳብን አይ ኤፍ ኤ ቢ (IFAB) ዛሬ መቀበሉን አስታወቀ።

በኮቪድ-19 ምክንያት በዓለም ላይ የሚደረጉ እግርኳሳዊ ውድድሮች ከተቋረጡ ሰንበትበት ብሏል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሃገራት በወረርሽኙ ምክንያት ያቋረጡትን የሊግ ውድድር ለመጀመር እያጤኑ አልፎም የሚጀምሩበትን ቀን እያሳወቁ ይገኛሉ። ይህንን ተከትሎ የዓለም አቀፉ የእግርኳስ የበላይ አካል የሆነው ፊፋ ውድድሮች የሚመለሱ ከሆነ በጨዋታ የሚቀየሩ ተጫዋቾች ቁጥር ከ3 ወደ 5 ይደግ ብሎ ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው ዓለምአቀፍ እግርኳስ ማኅበር ቦርድ [IFAB] ያስገባው ጥያቄ ዛሬ ከሰዓት ምላሽ አግኝቷል። በዚህም የጨዋታ ህጎችን የሚያወጣው አካል ውድድሮችን ለመጀመር ለወሰኑ እንዲሁም ሊጎቻቸውን ዳግም ለማስቀጠል እያሰቡ ላሉ ሃገራት የጨዋታ ህጉን በጊዜያዊነት ማሻሻሉን ገልጿል።

በመሆኑም እስከ ዲሴምበር 31 (ታኅሣሥ 2013) ድረስ ውድድሮቻቸውን ለማጠናቀቅ እቅድ ላወጡ ሃገራት በህግ 3 ላይ የተቀመጠውን “በጨዋታ የሚቻለው 3 ተጨዋቾችን ብቻ መቀየር ነው” የሚለውን ሕግ ማሻሻሉን አስታውቋል። ስለዚህ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ ብቻ ውድድሮቻቸውን ለማጠናቀቅ ያሰቡ ሃገራት ከዚህ በኋላ 5 ተጨዋቾችን በጨዋታ በመቀየር ተጨዋቾች ላይ ሊደርስ ይችላል ተብሎ ሲሰጋ የነበረውን አካላዊ እና አዕምሯዊ ጫና መከላከል እንዲችሉ አድርጓል። ውሳኔው የቫይረሱ ተፅዕኖ መርዘም እና ማጠርን ከግምት ውስጥ በማስገባት ምናልባትም የጊዜ ገደቡ ላይ ማሻሻያ ሊደረግ ይችላል ተብሏል።

ነገር ግን በጨዋታ ላይ ቡድኖች 5 ተጨዋቾችን የመቀየር ፍቃድ ቢያገኙም የጨዋታው ፍሰት ቶሎ ቶሎ እንዳይቋረጥ እና ጨዋታው በየጊዜው እንዳይረበሽ አንድ ቡድን በጨዋታ የተጫዋች ለውጦች የሚደረገው በሦስት አጋጣሚ ብቻ (በእረፍት ጊዜም ይቻላል) ነው ተብሏል። ምናልባት ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ጊዜ ተጨዋች ከቀየሩ ሁለቱም በተመሳሳይ ያላቸውን እድል እንደተጠቀሙ ይቆጠራል ተብሏል። ከዚሁ ከተጨዋች ቅያሪ ጋር በተያያዘ ጨዋታው ወደ ጭማሪ 30 ደቂቃ የሚያመራ ከሆነም ቡድኖቹ ያላቸውን 3 የተጨዋች ቅያሪ እድል መጠቀም እንደሚችሉ (በሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ካልተጠቀሙበት) ተጠቁሟል። ነገርግን ሃገራት በጭማሪ 30 ደቂቃ ተጨማሪ የተጫዋች ለውጦችን የሚፈቅዱ ከሆነ ጭማሪ 30 ደቂቃው ከመጀመሩ በፊት ወይም ከእረፍት መልስ ጨዋታው ሳይጀመር ብቻ ቅያሪውን ሊያደርጉት እንደሚገባ አሳስቧል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ