ታሪካዊው ከበደ መታፈርያ ሲታወሱ

ባለፈው ሳምንት በጀመርነውና በሕይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን የምንዘክርበት አምድ በዛሬ ዝግጅቱ ከቀደምት የእግርኳስ ተጫዋቾቻችን መካከል የሚጠቀሱትና የዘመናቸው ታላቅ ተጫዋች የነበሩት ከበደ መታፈርያን እንዘክራለን።

ከበደ መታፈርያ በ1940ዎቹ እና ሀምሳዎቹ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደሙ የነበሩ ሲሆን በኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና ኢትዮጵያ ዋንጫ በርካታ ዋንጫዎችን ያነሳውና ወቅቱ ከፍተኛ ተወዳጅነት የነበረው የጦር ሠራዊት (ኋላ ላይ መቻል) ወሳኝ የአጥቂ ስፍራ ተሰላፊ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል የነበሩት ከበደ መታፈርያ ለመጀመርያ ጊዜ የተከናወነው የ1957 (በኢትዮጵያ 1949) አፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ ታሪካዊ ተጫዋቾች አንዱ የነበሩ ሲሆን ለብሔራዊ ቡድን በርካታ ጨዋታ ካደረጉ ተጫዋቾችም አንዱ ናቸው። በመቻል ቆይታቸውም 6 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና 6 የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ማሳካት ችለዋል።

ከመቻል በመቀጠል ለበራሪ ኮከብ ለጥቂት ጊዜያት የተጫወቱትና ኋላ ላይ መቻልን ያሰለጠኑት ጋሽ ከበደ ከእሳቸው ቀጥሎ ለመጣው የእግርኳስ ትውልድ ፈር በመቅደድ እና ስፖርቱ በኢትዮጵያ ትኩረት እንዲያገኝ ከፍተኛ ሚና በመጫወት በታሪክ መዝገብ ሲታወሱ ይኖራሉ።

ጋሽ ከበደ በወቅቱ በችሎታቸው በርካታ አድናቂ እንደነበራቸው ለማሳየት በቅርቡ ለሕትመት የበቃው “ከሰንጋ ተራ እስከ አምስተርዳም : ከታኅሣሥ ግርግር በፊት የተወለደ ያዲሳባ ልጅ ግለ ታሪክ” የመላኩ ተገኝ መፅሐፍ ላይ ስለ ከበደ መታፈርያ ይህን አስፍሮ ነበር።

“ካምቦሎጆ የነበረበት ሰፈር (የዛሬው አዲስ አበባ ስታዲየም) ያኔም ቢኾን ከከተማ ውጭ የሚባል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ወደ ደብረዘይት መንገድም በርካታ ሰፈሮች ነበሩ። መድፈኛና እና አራተኛ ክፍለ ጦር፤ እንዲሁም ንፋስ ስልክ ከካምቦሎጆ በኋላ ያሉ ሰፈሮች ነበሩ። ከካምቦሎጆ በስተግራ በኩል ከግዮን ሆቴል በኋላ እስከ አዋሬ ድረስ ግን ጫካ ነበር። ወደ ቦሌም በኩል ጫካ ይበዛው ነበር።

“እንግዲህ ወደ ኳስ ዓለም የገባነው እንዲህ እንዲህ እያልን ነበር ለማለት ነው።

“እንደማስታውሰው ከኾነ ያኔ እኔ ትንሽም ስለነበርኩ፣ ገመምተኛ ቢጤም ስለነበርኩ ካምቦሎጆ የሚሄዱት ወንድሜና ይስሐቅ ብቻ ነበሩ፡፡ ከካምቦሎጆ ሲመለሱ ታዲያ ወሬያቸው ስለተጫዋቾች ነበር። ሁለቱም የመቻል ደጋፊዎች ስለነበሩ ስለ ከበደ መታፈሪያ ሲያወሩ አፌን ከፍቼ ነበር የማዳምጣቸው። መቻል ያኔ ጦር ሠራዊት የሚባለው ጦር ቡድን ነበር። የመቻል ደጋፊዎች የጦር ሠራዊት አባላት ቢሆኑም እንደነ ከበደ መታፈሪያ ያሉ ድንቅ ተጫዋቾች ስለነበሩት ከሲቪሉም ደጋፊዎች ነበሩት። እኔና ወንድሜ ለምሳሌ የመቻል ደጋፊ ነበርን። ያኔ ታዲያ ኳስ ተጫዋቾች ከጣሊያኖች የተወሰደ ልማድ ነበራቸው። ይኸውም መሐረብ አናታቸው ላይ ሸብ አድርጎ ማሰር ነው። ታዲያ አንድ ጊዜ መቻልና መኩሪያ ሲጫወቱ ይስሐቅና ወንድሜ እንደምንም አግባብተው ወሰዱኝ። እኔ ከጨዋታው ይልቅ ተመልካቹን ነበር የማየው።

“ጨዋታው ሲያልቅ ተመልካቹ ሜዳውን መውረሩ የተለመደ ስለነበር መጀመሪያ ብርር ብለው የሚገቡት ልጆች ነበሩ። በዚያ ዘመን ሜዳውን ከተመልካች የሚለይ አጥር አልነበረም። ያን ዕለት ከመቻልና ከመኩሪያ ማን እንዳሸነፈ ትዝ አይለኝም። ብቻ ጨዋታው ሲያልቅ ይስሐቅ እጄን ይዞ ወደ ሜዳው በረርን። በቀጥታ ወደ ከቤ (ከበደ መታፈሪያ) ሄድን። ይስሐቅ ከቤ ላይ ተጠመጠመበት። ከቤም ጭንቅላቱ ላይ ያሰረውን መሐረብ ከሰው ተውሶ ኖሮ ያዋሰው ደግሞ ይስሐቅ መስሎት ‹‹እንቺ..ጎበዝ!›› ብሎ መሐረቡን ሰጠው፡፡ ይስሐቅም ያላሰበው ሲሳይ ሲያጋጥመው ደነዘዘ፡፡ ከቤም ከወረረው ኩታራና መቻል ደጋፊ ጋር ወደ መድፈኛ አቅጣጫ ሄደ።

” ያኔ የመቻል፣ የጊዮርጊስና የመኩሪያ ቡድን ተጫዋቾችን ዝርዝር በቃላችን ነበር የምንወጣው። አሁንም ድረስ ከማስታውሳቸው የመቻል ተጫዋቾች ግብ ጠባቂው ሽታ፣ስጦታው፣ ዮናስ ፣ አየለ ጅቦ፣ አዳሙ፣ አሰግድ፣ ከቤ፣ ጣሰውና አመለወርቅ፤ ከጊዮርጊስ ደግሞ አሼ ብረቱ (አሸናፊ)፣ ነፀረ፣ ቸሬ፣ ዘውዴ፣ ይድነቃቸው፣ ፑሽካሽ፣ ያየህይራድ ሲሆኑ ከመኩሪያ ደግሞ ታደሰ፣ ኃይሉ፣ ትርፌ፣ ብርሃኔ ኩሩሩ ነበሩ። ከኦሜድላ ተካና ግብ ጠባቂው ብርሃኔ ይታወሱኛል፡፡ ከዚያ በኋላ በኳስ አበድን፡፡ የጨርቅ ኳስ ተሰፋና ግቢያችን ውስጥ ‹‹እኔ ከቤ፣ አንተ ብርሃንን እየተባባልን መጫወት ጀመርን። “

ከ12 ዓመታት በፊት መስከረም 18 ቀን 2000 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ጋሽ ከበደ መታፈርያን የሚያወሱ ፅሁፎች ማግኘት አዳጋች ቢሆንም በሚያዚያ ወር 2000 ለህትመት የበቃውና በፋንታሁን ኃይሌ፣ ኃይማኖት ቃኘው እና ተዘራ አለነ አማካኝነት የተዘጋጀው “ይድረስ ለባለንብረቱ” የተሰኘ መፅሐፍ የታላቁን ተጫዋች የህይወት ጉዞ በጥሩ ሁኔታ አቅርበዋል። እኛም ከመፅሐፉ ላይ ያገኘነውን ፅሁፍ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

(ከዚህ በታች ያለው ፅሁፍ ሙሉ ለሙሉ ከመፅሐፉተወሰደ ነው)


የውቤ በረሃ የሙቀት መጠን ጣሪያ በነካባቸው ዓመታት በአንደኛው ዘመን ከወዳደቁ ጨርቆች የሠሯትን ኳስ ከወዲያ ወዲህ እያንከባለሉ የሚጫወቱ አንድ ልጅ እናስብ፡፡ የዘመኑ ታላላቅ ሰዎች በሚያዘወትሩት የመዝናኛ ስፍራ በእጃቸው የሠሯትን ኳስ በእግራቸው እያንከባለሉ ራሳቸውን በራሳቸው መንገድ ያዝናኑ ነበር፡፡

ዕድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ የእግር ኳስ ተጫዋችነትን እና ውትድርናን ቀዳሚ ምርጫቸው እንደሚያደርጉ ተተንብዮላቸዋል፡፡ የቀለም ትምህርታቸው ነገር ብዙም የሚያዋጣ ባለመሆኑ እየተረሳ ሄዷል። የጀግናው ከበደ መታፈሪያ የሕይወት መዘውር ከውትድርናው ይልቅ ለእግር ኳስ ጨዋታ አዳላችና በሙሉ ልብና ወኔ ኡደቱን አስተናገደች፡፡ በውቤ በረሃ መንገድ የእግር ኳስ ጨዋታ የገጠሙት አብሮ አደጎቻቸው በተለያየ መስክ ሲሰማሩ «ጋሽ ከቤ» የመቻል ክለብንና የብሔራዊ ቡድን ማልያን የሙጥኝ አሉ፡፡ ለማልያው ፍቅርና ለስፖርቱ በነበራቸው ጥልቅ ፍላጎት የሚያደርጉትን ጨዋታ ለመመልከት ሜዳ ሲመጡ በሩቅ ከመተያየት በስተቀር ከአብሮ አደግ ጓደኞቻቸው የተሰነባበቱት ቀደም ብሎ ነበረ::

የተወለዱበትን ዓመተ-ምህረት በነጠላ ማንሳት ከዘመኑ መግፋት ጋር ተያይዞ አልተሳካም። በ1999 ዓ.ም. መገባደጃ ሰሞን ይሄን መረጃ ከአንደበታቸው ማግኘት ወሳኝ በመሆኑ እንጂ ፤ የጋሽ ከቤ የማስታወስና የመናገር አቅም ከባድ ፈተና ገጥሞት ነበረ፡፡ የከቤ ቁመትና ትከሻ አልጋ ላይ በመዋሉ የዘወትር ግርማ ሞገሳቸውን አጥተው ይታያሉ፡፡ የብርቅዬ ተጫዋቹን ጋሽ ከበደ መታፈሪያ ገድሎች በወጉ ለማቀናበር በየመሐሉ አንዳች ሐሳብ ቢያካፍሉን ብሎ መጠበቅና ዓይን ዓይናቸውን መመልከት ይጠይቃል፡፡

በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ቀደምት ተጫዋቾች የሰውነት አቋማቸውና በተፈጥሮ ያገኙትን የጨዋታ ክህሎት በልምምድ ለማዳበር የሚያደርጉት ጥረት ለቡድናቸው ውጤት ማማር ትልቅ ድርሻ እንደነበረው በዝግታ አወጉኝ፡፡ ለስፖርታዊ ሥነ-ምግባር የመገዛታቸውን ነገር ከሁሉ ቅድሚያ የሚሰጡት እንደነበር ራሳቸውን ምሳሌ አድርገው ይገልፃሉ፡፡

ረዥም ቁመት፣ የተመጣጠነ ውፍረትን በነፃነት የመንቀሳቀስ ችሎታን ካነሳን ሙሉ ሜዳን ለመቆጣጠር፣ ከላይ የመጣን ኳስ ተሻምቶ ለመያዝና በቀላሉ ለመቆጣጠር እንዲሁም ተገፍቶ በቀላሉ ላለመውደቅ ወሳኝነት ነበራቸው፡፡ ምንም የተመቻቸ የእግር ኳስ ሜዳና ባለሙያ በሌለበት ሁኔታ ነው ጋሽ ከቤ ራሳቸውን ፈር ቀዳጅ የእግር ኳስ ተጫዋች ሆነው ያገኙት፡፡ በከቤ ዘመን ጥቅምንና ጉዳቱን መዝኖ፣ ያዋጣል ብለው ሳይሆን በደመ-ነፍስ ፍላጐታቸውን ለማርካት ሲባል የሚደረግ የእግር ኳስ ግጥሚያ የተፈጠሩለትን ዘርፍ በፀጋ ከመቀበል የሚቆጠር ነበር። ቤተ-ሰብና መምህራን ቢቆጡ የቅጣት ጫናውን ቢያበዙም ከተፈጥሮ ያገኙትን ፀጋ የሙጥኝ ለማለት ወዶ ገብነት እንደሆነ ይታመናል። ጋሽ ከበደ መታፈርያ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሯቸው ትምህርት ቤት ቢላኩም እንኳ በተራበ አንጀት እና በልጅነት እድሜ ፊደል ከመቁጠር ማለፍ የሚሞከር አልነበረም። መምህራን በትምህርታቸው ደካማ ናቸው ብለው ሳያሰራብቷቸው ለምግብ ፍለጋ ሲሁ በራሳቸው ጊዜ ትምህርት ቤትን እርም ብለው ቀሩ።

የአካባቢው ተጽእኖ ቀላል እንደማይሆን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይቻላል፡፡ የልብስና የጫማ ውድድር ቢቀር ከእኩዮቹ ጋር እንደልብ ተሯሩጦ የሚወዱትን ኳስ መጫወት አለመቻል ጋሽ ከቤን ተፈታትኗቸዋል፡፡ ይህ እውነታ ከዓለም የእግር ኳስ ንጉሥ ፔሌ ጋር የሚያመሳስላቸው ዳራ እንዳለው ያመላክታል፡፡ ፔሌ ዘግየት ብሎ በእግር ኳስና በገንዘብ በኩል ካሳውን በእጥፍ ማግኘቱ ግን ያለያያቸዋል፡፡

ከ1941 ዓ.ም. እስከ 1953 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ ጨዋታዎች ተሰልፈው ካደረጓቸው ግጥሚያዎች ለብሔራዊ ቡድን ብቻ 62 ጊዜ ተሰልፈዋል፡፡ በአጥቂነት ቦታቸው ረዣዥም ኳሶችን ወደ ግብ በመምታት ሲታወቁ ከሰነዘሯቸው መካከል 44ቱ ከመረብ ተዋህደዋል፡፡ በዚህ ብቃታቸው አመለሸጋነት ታክሎበት ከስፖርት ማኀበረ-ሰቡ ጋር መልካም ግንኙነት እንደነበራቸው ይወሳል፡፡

የጋሽ ከቤ ዘመንኞች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቀደምት ትውልዶች እንደመሆናቸው አሠልጣኝና ተጫዋች ብዙ ልዩነት ሳይኖራቸው አብረው ያደጉበት እውነታ ነበር፡፡ በግል ጥረትና ተክለ-ሰውነታቸው ተማምነው ሲጫወቱ ቆይተው ነበር። የውጭ አገራትን የአጨዋወት ቴክኒክ የማየት ጭላንጭል የገጠማቸው፡፡ በዚሁ ሲፍጨረጨሩ ደግሞ ከውጭ አገራት የሚመጡ አሠልጣኞችን የማግኘት እድል ተፈጠረላቸው። የአጨዋወት ብቃትና አዲስ ቴክኒክ ለመቀበል ያላቸውን ፍላጐትና አቅም የተመለከቱ የግሪክና የዩጉዝላቪያ አሠልጣኞች ከቤን በአገራቸው ለማስቀረት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም፡፡ በኘሮፌሽናልነት እንዲጫወቱላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ «አገሬ ደርሼ ልመለስ፡፡» በሚል ሰበብ ተመልሰው ሲጫወቱና ተተኪዎችን ለማፍራት ሲሠሩ ነበር እድሜያቸውን የገፉት።

ቀድሞውንም በራሳቸው ብርታት ላይ የተመሠረተው የእግር ኳስ ክህሎታቸዉ ያገኙትን እገዛ በአግባቡ እንደተጠቀሙ ይነገርላቸዋል፡፡ ጋሽ ከቤና መሰሎቻቸዉ ለስፖርተኛ ከሚከለከሉት ከአልባሌ ቦታ መዋል እንደሌለባቸው የመሳሰሉ ምክሮችን በአግባቡ ማስተናገዳቸው የጨዋታ ብቃታቸው ለረዥም ዓመታት ሳይዋዥቅ ለመቆየቱ አብይ ምክንያት ተደርጐ ይጠቀሳል፡፡

መጋቢት 5 ቀን 1953 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ወክሎ በእሥራኤል አገር የተደረገ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ጋሽ ከቤ ተሰልፈዋል፡፡ በጨዋታዎቹ የብሔራዊ ቡድን አምበል በመሆን የ10 ቁጥር ማልያ ለብሰው የተሰለፉት ጋሽ ከበደ መታፈሪያ ነበሩ። ከእሥራኤል ቡድን ጋር የተደረገውን የደርሶ መልስ ጨዋታ ከቤና ጓደኞቻቸው በእሥራኤል አገር ሜዳ ነበር ያደረጉት፡፡ ይህ ለምን ሆነ ቢባል የአዲስ አበባ ስቴድዮምን የሚያስገነባው እሥራኤላዊ ተቋራጭ በወቅቱ ግንባታውን ጨርሶ ባለማስረከቡ ነበር፡፡ በተጋጣሚ ቡድን አገር፣ ሜዳና ደጋፊ ፊት ሁለቱንም ጨዋታ ለማድረግ ሲገደዱ 1 ለ ዐ እና 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ነበር የተሸነፉት። ግጥሚያቹ የእኩያ ቡድኖች ያህል እንደነበርና በሰው አገር በአንድ የግብ ብልጫ መሸነፋቸው በእሥራኤል መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ጋሽ ከቤ የተሰለፉበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግምቱ ታላቅ እንደነበር ተዘግቧል።

ከዘመናዊ አጨዋወት ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ የሚደረገው ጥረት እምብዛም በነበረበት ወቅት ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው ክህሎታቸውን ማዳበር ተቀዳሚ ተግባራቸው ነበረ። ከኢትዮጵያ ውጭ ተጉዘው የእግር ኳስ ክሂሎችን ያዳበሩባቸው ውድድሮችን ማድረግና የራሳቸውን ብቃት ማሳደግ ለጋሽ ከቤ ያለፉባቸው የእግር ኳስ ቴክኒክና ታክቲክ ትምህርት ቤቶች እንደነበሩ ይናገራሉ። ከአውሮፓና ከአፍሪካ አገራት ምርጥ ቡድኖች ለሚደረጉ ግጥሚያዎች ትኩረት ሰጥተው እየተጫወቱ በተመሳሳይ ሰዓት ትምህርት ይወስዱ ስለነበር በአጥቂነት ኢትዮጵያን ለማስጠራት የሚያበቁ ውጤቶችን ለማስቆጠር በቅተዋል። ጋሽ ከቤ የውጪ አገር ቡድኖች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡና እሳቸው ወደ ውጭ አገራት ተጉዘው ሲጫወቱ ክህሎታቸውን መቅሰም ሥራዬ ብለው የሚያከናውኑት፡፡

የመቻል የመሐል አጥቂ ሆነው በአምበልነት ለአሥራ አምስት ዓመታት ያህል ተሰልፈዋል፡፡ እንደ ሌሎች አንጋፋ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾች ጋሽ ከቤም የእኔ ለሚሉት የመቻል ቡድን ረዥሙን ዓመት እንደተጫወቱ ነበር ዕድሜያቸውን የገፉት፡፡ መቻል ከፈረሰ ወዲህ ደግሞ የበራሪ ኮከብ አጥቂ ተጫዋች ሆነው ተሰልፈዋል። የብሔራዊ ቡድን መከታ መሆናቸው የአገር ጉዳይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከብሔራዊ ቡድኑ ማልያ በተጨማሪ የመቻልንና የበራሪ ኮከብን ማልያ በመልበስ ዝናቸውን ለመላው አገሪቱ የእግር ኳስ አድናቂ አስተዋውቀዋል።

ለመቻል በተጫዋችነት መሰለፍ ሲያቆሙ የቡድኑ አሠልጣኝ በመሆን ያሳደጋቸነን ቡድን መልሰው አገልግለዋል። ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ በተለያዩ። ጊዜያት የተከታተሏቸው የአሠልጣኝነትና የዳኝነት ኮርሶች ከጠንካራ ተጫዋችነታቸው ጋር ተዳምረው ነበር፡፡ በአጥቂ ቦታ ተሰልፈው ያሳለፉት ዘመን ያበረከተው አንዳች ነገር ያለ ይመስል በጋሽ ከቤ የአሠልጣኝነት ቆይታ ካፈሯቸው መካከል የበረኞች ብዛትና ብቃት ከማንም አይወዳደርም:: ራሳቸው ካሠለጠኗቸው መካከልም በተናጠል ሲታዩ የግብ ጠባቂዎች አቋም በአስገራሚ ሁኔታ የተለየ እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ከመቻል አልፈው ለብሔራዊ ቡድን ብረት መዝጊያ የሆኑ በረኞችን የማፍራት ተስጥኦ ባለቤት ነበሩ፡፡ ለእማኝነት እንጥቀስ ካልን የመቻልና የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የነበረው በቅጽል ስሙ ‹‹ካንጋሮ» አንዱ ነበር፡፡ ከወንጂ የተገኘው በለጠ ወዳጆና ኃይላት ገ/ጊዮርጊስ የተባሉት ይገኙበታል፡፡ በ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ የቀድሞ ደረጃዋን መልሳ ልታገኝ ነው የተባለለትን ቡድን በግብ ጠባቂነት ያስከበረው አፈወርቅ ጠና-ጋሻውም የጋሽ ከቤ የሥልጠና ውጤት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ የእግር ኳስ አሠልጣኝነት ስሜትና አቅማቸው ከፍተኛ በነበረበት ወቅት ከመቻል በተጨማሪ በርካታ ቡድኖችን አሠልጥነዋል፡፡ ሙያውን በአገር ዓቀፍ ደረጃ ሲያስፋፉ የጠበሉ ተካፋይ የነበሩት የሸዋ ምርጥ፣ ጉምሩክ፣ አንበሣ፣ አደይ አበባ፣ አቃቂ ጨርቃጨርቅ፣ ኢትዮ-ቃጫ፣ ኢትዮ-ሲደር (ብረታ ብረት) ፣ አምቼ፣ ጃፓን ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ በርታ ኮንስትራክሽንና የከንባታና ኃድያ የእግር ኳስ ቡድኖች በጋሽ ከቤ ትውስታ በቅርብ የተገኙት ነበሩ፡፡ በተለያየ ጊዜ ከቡድኖቹ አባላት ጋር የነበራቸውን ቆይታ የሚያስታውሱት ተጫዋቾች አሠልጣኝ ለሚሰጠው መመሪያና በስፖርታዊ ሥነ-ምግባር ከመገዛታቸው ሌላ ተመጣጣኝ የሰውነት አቋም እንደነበራቸው ነው፡፡

በጋሽ ከቤ እምነት ወደ ስቴድዮም ኘሮግራሙን ጠብቆ የሚያመራው እግር ኳስ አድናቂ ቡድኖቹ በሚያሳዩት ማራኪ እንቅስቃሴ ውስጥ ለማሸነፍ፣ አቻ ለመለያየትና በጨዋታ ከተበለጡ ጥሩ ተሸናፊ ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት ተደስቶ ይመለስ ነበር። እንዲህ እንዲህ ያሉትን ተጫዋቾች ለማፍራት በየትምህርት ቤቱ ተዘዋውሮ ግጥሚያዎችን መመልከትና የተሻለ የእግር ኳስ ተሰጥኦ ያለውን ታዳጊ ወጣት የመምረጥ አማራጭ መከተላቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ በዚህ መልኩ ከጋሽ ከቤ ጋር የመገናኘት እድል ከገጠማቸውና በከፍተኛ ደረጃ የእግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን ካበቋቸው መካከል ይድነቃቸው አዳሙ፣ ፀሐይ ባህረ፣ ሽፈራሁ አጐናፍር፣ ዘውዴ ሣሙኤልና አለማየሁ ታደሰ የተባሉትን ማንሳት ይቻላል፡፡ ዕድሜያቸው ገፍቶ ስቴድዮም ተገኝተው የአገር ውስጥ የእግር ኳስ ጨዋታችን መከታተል ባቆሙበት ወቅትም ፍላጐታቸውን የሚያረኩት የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንና የቀድሞ ባልንጀሮቻቸው ከሚያቀብሏቸው መረጃ ነበር፡፡

ከሚያዳምጧቸው ኢትዮጵያ በቀድሞ ጊዜ ታሸንፋቸው የነበሩ አገራት ከሚሳተፉበት መድረክ የእኛዎቹ ለመድረስ እንዳልቻሉ መገንዘባቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ የእነሱን ዘመን ድል ለመጨበጥ የተከፈለውን መስዋአትነት እያስታወሱም «የዛሬዎቹ አሠልጣኞችና ተጫዋቾች ምን ነካቸው?» የሚል ሐሳብ በአዕምሯቸው እንደሚመላለስ ይገልፃሉ፡፡ በወታደር ቤት ደመወዝ አንድ ሴትና ሁለት ወንድ ልጆችን ወልደው አሳድገዋል፡፡ ጋሽ ከቤ ካፈሯቸው ሦስት ልጆች አንደኛው የልጅነት ጊዜውን እንደአባቱ በእግር ኳስ ሜዳ ማሳለፍ አዘወትሮ የነበረ ቢሆንም ከቀበሌ ተጫዋችነት በላይ አልገፋበትም፡፡ የአባቱ ድጋፍና ማበረታቻ አልታከለበትምና የያዘው ክሂልና በተግባር ያዳበረው የእግር ኳስ ተጫዋችነት ስሜት ከወጣትነቱ ሳይዘል ቀርቷል፡፡ ከውትድርናው ዓለም በጡረታ ሲሰናበቱ ጥንካሬያቸውንና የአገር ባለውለታነታቸውን በሚረዱ ሰዎች ትብብር ሚድሮክ ኢትዮጵያ በሹፌርነት ተቀጥረው አገልግለዋል፡፡ ኑሯቸውን ቂርቆስ ሠፈር አድርገው የነበረው ጋሽ ከበደ መታፈሪያ ሕይወት ተሳክቶላቸው ለኑሮ የሚያስፈልገውን ወጪ በቀላሉ ሸፈነው የሚጦሩ ልጆች አባት ለመሆን አልታደሉም፡፡ በመጨረሻዎቹ ዓመታት የገንዘብ ማጣት አንገላቷቸው ነበር:: ከወታደር ቤት በሚያገኙት የጡረታ ደመወዝ ሁለት ልጆቻቸውንና አካል ጉዳተኛ ባለቤታቸውን እያስተዳደሩ የጤና መታወክ ሲገጥማቸው ለሕክምና የሚያውሉት ብር ከሳጥን ማውጣት የሚታሰብ አልሆነም።

በእርጅና ዘመናቸው ሕመም በአልጋ ላይ እንዲውሉ ሲያደርጋቸው ሰለሞን እና ፀሐይ ከበደ የተባሉ ልጆቻቸው ግርጌ እና ራስጌ ሆነው አስታመዋቸዋል። ዕድሚያቸው ከ30 ዓመት በላይ ቢሆናቸውም ሁለቱም ልጆች ለእለት ጉርስ ወይም ለመዋያ ያህል እንኳን ሥራ የላቸውምና የአባታቸውን ጭንቅ አጠገባቸው ሆነው ከማየት የዘለለ ድጋፍ ለማድረግ እጅ አጥሯቸዋል፡፡ ፀሐይ ጀርመን አገር ለሁለት ዓመታት የኖረች ቢሆንም አባቷና አሳዳጊ እናቷ መድከማቸውን ተመልክታ «አብሮ መሆን ከሁሉ ይበልጣል::» በሚል እጅና እግሯን አጣምራ ተቀምጣለች፡፡ አባወራው በሕመም የሚሰቃዩበትን መጠን ለማገዝ አቅም ስለሌላቸው ሁሉም የቤተ-ሰቡ አባላት በራቸውን ዘግተው በቀዝቃዛ ቤት ከመቀመጥ ውጭ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ ዘወትር የጣፈጠ መመገብ የሚወዱትን፣ በቀድሞ ብሔራዊና በክለቦች በሚያደርጉት ተሳትፎ ታላቅ የሕዝብ ፍቅር የነበራቸውን እግር ኳስ ተጫዋች በደከሙ ጊዜ የእነሱ ብቻ አባት የሆኑት ጋሽ ከቤ በባዶ ቤት የመተኛት ጭንቀት «አባታችን ስሙ ትልቅ፣ ኑሮ ግን ትንሽ ነው። በማለት ነበር ሰሎሞን ከበደ ስሜቱን የገለፀው። በፈለጉት መጠን ማስታመም አለማቻላቸውን እያሰላሰለች ሕይወታቸውን ሙሉ ለተሰለፉለት የእግር ኳስ ስፖርት የነበራቸውን ፍቅር ፀሐይ ትገልፃለች፡፡ እንደአባት ልጆቻቸውን ትልቅ ቦታ ማየት የሚመኙ መሆናቸውን «አባታችን፣ እሱ በፈለገው መንገድ ብቻ እንድንሄድ የሚፈልግና ልጆቹን ተቆጥቶ ያሳደገ ነው። ዛሬ አልጋ ላይ መዋሉ ነው እንጂ ፤ ማታ ወደ ቤት ሲመጣ ባዶ እጁን መግባት የማይወድ ሩህሩህ ነበር፡፡» በማለት የአባቷን ስብዕና ታስቀምጣለች፡፡

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እንቅስቃሴ ቅርበት ያላቸው ሁለት ግለሰቦች የጋሽ ከበደ መታፈሪያን የህክምና ወጪ ሸፍነው ከሐምሌ ወር 1999 ዓ.ም. ጀምሮ በግል ሆስፒታሎች እንዲታከሙ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ነገር ግን ለሶስት ወራት ገደማ በህክምና ሲረዱ ቆይተው መስከረም 18 ቀን 2000 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡የቀብራቸውም ሥነ-ሥረዓት በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በሚገኘው ቂርቆስ ቤተ-ክርስቲያን ቤተ-ሰቦቻቸው፣ ወዳጆቻቸውና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት በዕለተ እሁድ አዲሱ ሚሊኒዬም በገባ በ19ኛው ቀን ተፈጽሟል፡፡

“ይድረስ ለባለታሪኩ”

ሚያዚያ 2000


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ