የሴቶች ገፅ | የአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የኦሊምፒክ ማጣሪያ አስገራሚ ክስተት

ትውልድ እና እድገቱ በኦሮሚያ ክልል በሚገኝ ሸኖ በሚባልና ልዩ ስሙ መኑሻ በተባለ ቦታ ላይ ነው። እስከ 11 ዓመቱ በኖረበት መኑሻ የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ቤተሰቡ ሯጭ እንዲሆን ይፈልጉ ነበር። ነገር ግን ትምህርቱን ለመቀጠል እና ኑሮን ለማሸነፍ በ11 ዓመቱ ወደ አዲስ አበባ መጣ። ብርሃኑ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ የተለያዩ ስራዎችን ያለእድሜው እንደሰራ ይናገራል። ከእንቁላል እስከ ሸንኮራ ንግድ ውስጥ እንደነበረም ያወሳል። ከዚህም አልፎ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ስደትን መርጦ እንደነበረ ያስታውሳል። ከእነዛ አስከፊ ጊዜያት በኋላ ግን ብርሃኑ ወደ እግርኳስ ፊቱን በማዞር በከፍተኛ ዲቪዚዮን ደረጃ አራት ኪሎ አካባቢ ለሚገኘው ወረዳ 14 ቡድን ተጫውቶ አሳልፏል። ከዛም በመቀጠል ወደ ጃን ሜዳ ብቅ በማለት የአሰልጣኝነት ህይወትን እንደቀልድ “ሀ” ብሎ ጀምሯል። ብርሃኑ በዋናነት የአዲስ አበባን የፕሮጀክት ቡድን፣ ፀደይ የወንዶች ቡድን፣ ምስራቅ ሃረር የሴቶች ቡድን፣ ወወክማ፣ ወሴክማ፣ የካ ክ/ከተማ የሴቶች ቡድን እና ሴንትራል የጤና ኮሌጅ አሁን ከሚገኝበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፊት አሰልጥኗል። ከክለብ በተጨማሪ ደግሞ ከ2002 ጀምሮ በተለያዩ በርካታ ወቅቶች የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ አገልግሏል።

በድምሩ 21 ዋንጫዎችን ከተለያዩ ክለቦች ጋር ያነሳው የአሁኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ለ2012 የለንደን ኦሊምፒክ ለማለፍ በተደረገ የማጣሪያ ጨዋታ የፈፀመውን አስገራሚ ነገር እንዲህ አጫውቶናል።

“በጣም ትዝ የሚለኝ ገጠመኝ ለለንደን ኦሊምፒክ ለማለፍ ባደረግነው የማጣሪያ ጨዋታ የተከሰተ ነው። በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ ኮንጎን በድምር ውጤት 3-0 አሸንፈን በቀጣይ ጋናን ለመግጠም ተደለደልን። አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ጋናን 1-0 አሸንፈን ወደ መልሱ ጨዋታ አመራን። በመልሱም ጨዋታ ጋናዎች በፍጥነት 2 ጎሎች አገቡብን። በጨዋታውም ጋናዎች በርካታ የግብ እድሎችን እየፈጠሩ አስጨነቁን። ጨዋታው በዚህ ውጤት ከተጠናቀቅ ተስፋችን በእንጭጩ መና ሊቀር ሆነ። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃ ሲቀረው ግን ብዙሃን እንዳለ ጎል አስቆጠረች። በዚህ ጊዜ እራሴን መቆጣጠር ተሳነኝ። ጃን ሜዳ እና አዲስ አበባ ስታዲየም እንደለመድኩት ዘልዬ ወደ ሜዳ ገባሁ። ደስታ ዓይኔን ሰውሮታል መሰለኝ ብዙሃን መስላኝ የዕለቷን ዳኛ ለማቀፍ በሜዳው ሩጫ ያዝኩ። ዳኛዋም ደንግጣ እየሸሸችኝ ስትሮጥ ብዙሃን በሌላ አቅጣጫ መጥታ አስቆመችኝ። አስቁማኝም ‘ትቀጣለህ እኮ ዳኛ ማቀፍ አትችልም’ ስትለኝ መለስ አልኩኝ። ጨዋታውም በዛው ተጠናቆ ወደ ቀጣይ ዙር አለፍን። በ88ኛው ደቂቃ የተጀመረው የደስታው ማዕበል ግን ጨዋታው ካበቃ በኋላም አልበረደም። ጋናን ማሸነፋችን የውሀ ዋና ሳልችል የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ዘልዬ እንድገባ አድርጎኝ ነበር። የመዋኛ ገንዳው ግን ደስታዬን ወደ ስቃይ በፍጥነት ቀየረብኝ። እንደውም ዶ/ር አያሌው ባይደርሱልኝ እና ባይረዱኝ ኖሮ መትረፌንም አሁን ሳስበው እርግጠኛ አደለሁም።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ