ሁለገቡ ተስፈኛ አሸናፊ ሀፍቱ

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ነጥረው ከወጡት ተስፈኛ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ፈጣኑ አሸናፊ ሀፍቱ የዛሬ እንግዳችን ነው።

በትግራይ የተለያዩ የዕድሜ እርከኖች በተደረጉ ውድድሮች እና በመቐለ 70 እንደርታ ሁለተኛ ቡድን የተሳኩ ዓመታት አሳልፏል። ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ዋናው ቡድን አድጎ በዚህ ዓመት በተለያዩ ቦታዎች ቡድኑን ማገልገል የጀመረው ይህ ፈጣን ተጫዋች በመስመር ተከላካይነት ፣ በመስመር ተጫዋችነት እና በፊት አጥቂነት መጫወት የሚያስችል ብቃት አለው። በተለይም በሁለተኛ ቡድን ቆይታው በድንቅ አጨራረሱ ይታወቅ የነበረ ሲሆን ወደ ዋናው ቡድን ባደገበት ዓመት ብዙ ተስፋ ቢጣልበትም ሁኔታዎች አልጋ በአልጋ አልሆኑለትም።

ደስታ አረቄ ፋብሪካ በተባለ የታዳጊዎች ቡድን ሲጫወት በመቆየት ወደ መቐለ ሁለተኛ ቡድን ተዘዋውሮ በቡድኑ በግል ሽልማቶች የታጀበ የተሳኩ ዓመታት በማሳለፍ የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው አሸናፊ በ2010 ሁለተኛው ዙር ወደ ዋናው ቡድን አድጎ በዛ ዓመት ከደደቢት ጋር በነበረው ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት በዋና ቡድን ደረጃ የመጀመርያ ጨዋታ ቢያደርግም እስከ ዘንድሮ የውድድር ዓመት ድረስ በቡድኑ ውስጥ የነበረው ተሳትፎ እምብዛም አልነበረም።

በልምምድ ሜዳ ታታሪ መሆኑ የሚነገርለት ይህ ተስፈኛ ታዳጊ በመጀመርያዎቹ ዓመታት የዋና ቡድን ቆይታው እድገቱ የተገታበት እና አቅሙ ያላሳየባቸው ዓመታት ሆነው ቢያልፉም በዘንድሮው የውድድር ዓመት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን አሳምኖ በወሳኝ ጨዋታዎች ሳይቀር በቋሚነት መሳተፍ እና ግብም ማስቆጠር ችሏል። በተለይም በአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ላይ በግሉ ያሳየው ብቃት የበርካቶች ትኩረት ስቦ እንደነበር ይታወሳል።

ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ የነበረው አሸናፊ ስለ ገጠሙት ፈተናዎች እና ስለ ቀጣይ እቅዱ ይህንን ብሏል።

” ከታዳጊ ቡድን ካደግኩበት ግዜ ጀምሮ ከትላልቅ አሰልጣኞች እና ብዙ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾ ጋር ተጫውቻለው ይህም በጣም ጠቅሞኛል። ከግዜ ወደ ግዜ ጥሩ የጨዋታ ልምዶች እያገኘሁ ነው ለዚህም ከጎኔ ሆነው ብዙ ነገር ያስተማሩኝ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ማመስገን እፈልጋለው። በዚህ ዕድሜዬ መቐለን የመሰለ ትልቅ ክለብ ውስጥ መጫወቴ ዕድለኛ ነኝ።

” በሁለተኛ ቡድን የተሳካ ቆይታ ነበረኝ ፤ በግልና በቡድን በርካታ ነገሮች አሳክቻለው። አሁን ላለሁበት ደረጃ መድረስም በዛ ቡድን የነበረኝ ቆይታ ወሳኝ ሚና ነበረው። በዛን ሰዓት የፊት አጥቂ ነበርኩ ፤ ብዙ ግቦችም አስቆጥርያለው። ወደ ዋናው ቡድን ካደግኩ በኃላ ግን በአሰልጣኞቼ ምክር ወደ መስመር ተከላካይነት ነበር የተሸጋገርኩት፤ ፍጥነትም ስላለኝ ብዙ አልተቸገርኩም። ፈተናው ግን ቀላል አልነበረም፤ ተከላካይ ስትሆን ብዙ ኃላፊነቶች ትሸከማለህ። የመስመር ተከላካይ ስትሆን ደግሞ ነገሩ ከበድ ይላል። በማጥቃቱም በመከላከሉም የመሳተፍ ግዴታ አለብህ ሁለቱም ባንዴ መወጣት ደግሞ ቀላል ፈተና አይደለም። በልምምድ ጠንክሬ በመስራት ግን አሰልጣኜ ከኔ የሚጠብቀውን ነገር ለሟሟላት ጠንክሬ እየሰራው ነው። በቀጣይም ተመሳሳይ ነገር መስራቴን አላቆምም። በብዙ ጨዋታዎች አቅሜ እንዳሳይ ዕድል ተሰጥቶኛል። ከኢትዮጵያ ቡና እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበሩት ሁለት የውድድር ዓመቱ ትላልቅ ጨዋታዎች ግብ አስቆጥርያለው። በሁለቱም ጨዋታዎች ቡድናችን ሦስት ነጥብ ይዞ አይውጣ እንጂ በግሌ ባሳየሁት ነገር በሰዓቱ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። በቀጣይም መቐለ 70 እንደርታን በተሻለ አቅም ለረጅም ዓመታት ማገልገል እፈልጋለው ፤ ያለኝን ነገር ይበልጥ አሻሽዬ ብሔራዊ ቡድን መጫወትም ከእቅዶቼ አንዱ ነው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ