ድሮ እና ዘንድሮ | ተጫዋቾችና ክፍያ…

እግርኳሳችን ከድሮ እስከ ዘንድሮ የተጓዘበትን ሁኔታ በምንዳስስበት አምዳችን ለዛሬ የተጫዋቾች ዝውውር እና ክፍያን ታሪካዊ ሒደት እናነሳለን።

ድሮ ድሮ እግርኳስ ወደ ሀገራችን በገባባቸው ዓመታት ተጫዋቾች ለአምሮታቸው እና ለፍላጎታቸው እንዲሁም ከተመልካች ለሚቸራቸው ጭብጨባ ብቻ እግርኳስን ሲጫወቱ ቆይተዋል። ቀስ በቀስ ደግሞ በትልቅም ሆነ በትንሽ ደረጃ የሚገኙ ተጫዋቾች የተለያዩ ዓይነቶች (ቁሳቁስና ምግቦች) እንደመደራደርያ እየቀረበላቸው ለበርካታ ዓመታት ሲጫወቱ አሳለፉ። ኋላ ላይ የእግርኳስ ክለቦችን የመሰረቱ ተቋማት ውስጥ ተጫዋቾች እንደ መደበኛ ሰራተኛ በመቀጠርና ሥራ በመስራት ደሞዝ እየተቀበሉ መጫወት ቀጠሉ። በመቀጠል ተጫዋቾች በየወቅቱ በነበረው የገንዘብ ዋጋ ለክለቦች እየፈረሙ መጫወት ያዙ። በ2008 ቀደም ብሎ የነበረው የፊርማ ገንዘብ ቀርቶ ክለቦች ለተጨዋቾች በደሞዝ መልክ ክፍያ እንዲፈፅሙ ተወሰነ። ከ9 ወራት በፊት ደግሞ እግርኳሱ የሚመለከታቸው አካላት ተሰብስበው ለተጫዋቾች የሚከፈለው ከፍተኛው የደሞዝ መጠን ከ50 ሺ ብር በላይ እንዳይሆን ጣራ አበጅተዋል። ይህንን ሒደት በማስመልከት ሶከር ኢትዮጵያ በዛሬው የድሮ እና ዘንድሮ አምዷ የተጫዋችን የተጫዋቾች ክፍያን ትላንት እና ዛሬ ትመለከታለች።

ታሪክ አዋቂው ገነነ መኩርያ በአንድ ወቅት በዚህ ጉዳይ ዙርያ ባሰፈረው ፅሁፍ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለአንድ ቡድን ለመጫወትና ለሙያው ጥቅም የጠየቀ የመጀመሪያው ተጫዋች ይድነቃቸው ተሰማ እንደሆነ ያወሳል። ታሪኩ እንዲህ ነው። በ1928 ምስረታቸውን ያደረጉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በየካቲት ወር ከአርመን ኮሚኒቲ ቡድን ጋር ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ይይዛሉ። ይህንን ጨዋታ ለማድረግ ተጫዋቾቹ ዶሮ ማነቂያ በሚገኝ ቤት ቢሰባሰቡም አንድ ሰው ግን ከመካከላቸው መጉደሉን በማስተዋል የጎደለውን ሰው ለማሟላት እንቅስቃሴ ጀመሩ። ተጫዋቾቹም ይድነቃቸው ተሰማን በመንገድ ሲያልፍ አግኘተው ሰው ስለጎደላቸው እንዲጫወትላቸው ፈለጉና ጠየቁት፡፡ “ለናንተ ስሰለፍ ምን ታደርጉልኛላችሁ?” አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ቆሎ እንገዛልሀለን››አሉና በነገሩ ተስማማ፡፡ ቆሎው ለሙያው የተከፈለ ነበር፡፡በኢትዮጵያ እግር ኳስ የመጀመሪያው የፊርማ ክፍያ ተብሎ የሚወሰደው ይሄ እንደሆን ይታመናል፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በቀጣይ ዓመታት የተፈጠሩት ታሪኮች በይበልጥ ተጫዋቾች ሙያቸውን በአይነት እንዲሸጡት ያደረገ ነበር። የገነነ ፅሁፍ ይቀጥላል። “ጊዮርጊሶች ፓቼ የተባለ የሀማሴን ተጫዋች ወደ ክላባቸው እንዲገባ ሲጠይቁት‹‹ ምን ታደርጉልኛላችሁ?›› ብሎ ላቀረበው ጥይቄ ሻይ ቤት ከፍተው ሰጡት፡፡ ደጋፊው የሚመገበው እዛ ስለሆነ ፓቼ ተጠቃሚ ነበር። ጀሚል ሀሰን የተባለ የቴሌ ተጫዋችም ለመፈረም ሲደራደር ቴሌ ከሀገር ውጭ ስልክ በነጻ እንዲደውል ተስማሙ፡፡ ነገር ግን ከውሉ በኋላ ዘመዶቹ ወደ ሀገር ቤት ስለተመለሱ ጀሚል የቴሌን ጥቅማጥቅም አልተጠቀመበትም። የአፍሪካ ዋንጫው ባለውለታ ጌታቸው ወልዴ በበኩሉ የኮተን ደጋፊዎች የቤት እቃ ስለገዙለት ሌላ ክለብ ሳይሄድ እዛው ለመቀጠል ተስማማ፡፡ ዳኛቸው ደምሴም ኮተን ሊወስደው ስለፈለገ የቅዱስ ሚካኤል ኃላፊ <<አምስት ታኬታ ስጡኝና ለቅላችኋለው>> ስላለ ተስማሙ፡፡ ሰለሞን የተባለ ተጫዋች ደግሞ አውራ ጎዳና በጥብቅ ስለፈለገው የአባቱን መኪና ጋራዥ ውስጥ በነጻ እንዲሰራላቸው ስለተስማሙ ፈረመ፡፡ ተስፋልደት ወደ ሀማሴን ቡድን ለማምጣት ሙከራ ተደርጎ ሳይሳካ ለቴሌ ሊፈርም ጫፍ ደረሰ፡፡ ለጋብቻም ሽማግሌ ወደ እጮኛው ቤት ላከ፡፡ አባት ግን ልጃቸውን ለመስጠት አንገራገሩ፤ ጭራሽ አሻፈረኝ አሉ፡፡ አባትየው የሀማሴን ደጋፊ ስለነበሩ ለክለቡ ካልፈረመ ልጄን አልሰጥም አሉ፡፡ አባትየው ብቻ ሳይሆኑ ክለቡ እዚህ ነገር ውስጥ እጁን እንዳስገባ ስላወቀ ለሀማሴን ፈርሞ የሚወዳትን ልጅ አገኘ፡፡ የዚህ ፊርማ ደግሞ ለትዳር የተከፈለ በመሆኑ ዋጋው ከፍ ያለ ነው፡፡ በአትሌቲክሱ የምናውቀው ወልደመስቀል ኮስትሬ ተማሪ እያለ ለጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በተጫዋችነት በሁለተኛው ቡድን ሊያስፈርሙት አነጋግረውት ነገርግን የአንበሳ ቡድን በጣም ስለፈለገው ምን ታደርጉልኛላችሁ ብሎ ሲጠይቅ ‹‹የዓመት የአውቶብስ ቲኬት እንሰጥሀለን›› ሲሉት ወልደመሰቀል ለአንበሳ ቡድን ፈረሙ፡፡ ” ይላል በፅሁፉ። ከእነዚህ የገነነ መኩርያ የታሪክ ፅሁፎች የምንረዳው የዓይነት ማግባቢያዎች የእግርኳሳችን ቀደምት የዝውውር መሳርያ ስለመሆናቸው ነው።

እንግዲህ እዲያ እያለ ለእግርኳስ ሙያ የጥቅም እውቅና መሰጠት የጀመረው የኢትዮጵያ የተጨዋቾች የዝውውር እና የደሞዝ ክፍያ በ1980ዎቹ መጨረሻ ወደ መደበኛ የኮንትራት ጥቅም መዞር መጀመሩን ገነነ በፅሁፉ እንዲህ ይገልፃል። “በዚህ ጊዜ የባንኮች ተጫዋች የነበረው ፋሲል አብርሃ ኒያላ ሲጠይቁት ተስማማ፡፡ ደሞዙንም ተነጋገረና ለክለቡ ለመጫወት መፈረም ነበረበት፡፡ ቴሴራ ላይ ፈርም ሲሉት ‹‹ለመፈረም ስንት ትሰጡኛላችሁ? ›› አላቸው፡፡ ከብዙ ክርክር በኋላ በአንድ ሺህ ብር ተስማሙ፡፡ ተጫዋቹ ይህንን ጥያቄ የጠየቀው አስመራ የሚገኙትን እናቱን ለመጠየቅ መሄድ ስለፈለገ እንደሆነ ይሰማል። ቀጥሎም ጌታቸው ካሣ በተመሳሳይ ቡና ለመፈረም በ2 ሺህ ተስማማ፡፡ ፋሲል ‹‹ለመፈረም ክፈሉኝ›› ካለ በኋላ ግን ወሬው ተራባ ‹‹ምን አይነት ስግብግብ ነው? ለመፈረም እኮ ገንዘብ ስጡኝ አለ›› በሚል ተወራ፡፡ በዚህ የተነሳ ስያሜው ‹‹ የፊርማ›› ተባለ፡፡ፋሲል በሚቀጥለው ዓመት መድን ሲገባ ‹‹ ባለፈው አመት (በ1988) ኒያላ ለመፈረም 1 ሺህ ከፍለውኝ ነበር፡፡ እናንተ ስንት ትሰጡኛላችሁ›› አላቸው፡፡ መድን የፊርማ የሚባለውን ነገር ስለማያውቁ ብዙ ተከራከሩት። ነገር ግን ስለፈለጉት ብቻ የጠየቀውን ለመፈጸም ተስማሙ፡፡አንዳንድ ተጫዋቾች ፋሲልን ‹‹ፈጣጣ ነው›› ሲሉ የነበሩ እነርሱ ራሳቸው እሱ በቀደደው መንገድ ገቡና ክለብ ሲጠይቃቸው ‹‹የፊርማ ››ማለት ጀመሩና መፈረም ያዙ። ”

ይህ የፊርማ ክፍያ ባህል ከፕሪምየር ሊጉ ውልደት በኋላም ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ከተለያዩ ምንጮች እና በይፋ ከተነገሩ የገንዘብ መጠኖች ካሰባሰብነው መረጃ መካከል ለአብነት በ1990 ቅዱስ ጊዮርጊስ ቴዎድሮስ በቀለ ‹‹ቦካንዴ››ን (15ሺህ)፣ ሰይፈ ውብሸት (10ሺህ) እና አንተነህ ፈለቀን (10ሺህ) ለማስፈረም የከፈለውን የገንዘብ መጠን እንደሆነ ይነገራል። በ1991 አንዋር ያሲን ለኢትዮጵያ ቡና ሲፈርም 20ሺህ ብር በመቀበል ሪከርድ መያዙ ሲነገር በ1992 ደግሞ ከሱዳኑ ሂላል የተመለሰው አንተነህ አላምረው ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመመለስ 30 ሺህ ብር በመቀበል ሪከርዱ መሻሻሉን ቀጠለ። በቀጣዮቹም ዓመታት አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ ሲል የቆየው የፊርማ ክፍያ ከሚሌኒየሙ መጀመርያ ወዲህ እጅግ ለቁጥጥር ባስቸገረ ፍጥነት አሻቅቧል። በ1990ዎቹ በአምስት እና አስር ሺህ የልዩነት ፍጥነት ሲጓዝ የነበረው ክፍያ በድንገት የ100ሺህ ብሮች ጭማሪ እያሳየ መጓዝ ጀምረ፡፡ በተለይ ወደ ሊጉ ያደጉ አዳዲስ ቡድኖች ተጠናክረው ለመቅረብ የሄዱበት መንገድ ቀድሞውንም ያልተለመደ የነበረው የፊርማ ክፍያ ባህል ላይ ግሽበት እንዲኖር አደረጉ። ሰበታ ከተማ በ2001፣ ደደቢት በ2002 እንዲሁም ዳሽን ቢራ በ2006 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲያድጉ ቀደሞ ከነበረው እጅግ የላቀ የፊርማ ክፍያ በማቅረብ ነበር የወቅቱ ኮከቦችን የግል ማድረግ የቻሉት።

ሰበታ ከነማ በ2001 ወደ ፕሪምየር ሊግ ባደገበት ዓመት የተጫዋች ስብስቡ የሃገሪቱ መነጋገርያ ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ ሰበታ ከነማ የሊጉን ታላላቅ ተጫዋቾች ለማማለል ከፍተኛ ገንዘብን ጨምሮ የመሬት ስጦታን መጠቀሙ ይነገራል፡፡ በተጨማሪም በ2002 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያደረገው ደደቢት የተጫዋቾችን የገንዘብ መጠን ጣርያ በመስቀል ሌላ አዲስ ምእራፍ ከፍቷል፡፡ በጊዜው ሙሉጌታ ምህረትን ለ2 ዓመት ለማስፈረም 110ሺህ ብር የከፈለው ደደቢት ቀድሞ ከፍተኛ ሲባል የነበረው የበረከት አዲሱን የ100ሺህ ብር ሪኮርድ አሻሻለው፡፡ ከደደቢት በኋላ ደግሞ ዳሽን ቢራ የተጫዋቾችን የፊርማ ክፍያ እጅጉን በማናር ወደ ሚሊዮን አሳደገው፡፡ በ2005 ክረምት ዳሽን ለዓይናለም ኃይለ 1.1 ሚልዮን ብር ፣ ለአሥራት መገርሳ ደግሞ 800ሺህ ብር በማውጣት የድራማው ዋና ተዋናይ ሆነ፡፡ ሃገራችን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፈችበት ወቅት መሆኑም በይበልጥ ተጨዋቾች የሚያገኙት ገንዘብ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲንር አድርጎታል።

በ2007 ክረምት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን በይፋ “የፊርማ ክፍያ ብሎ ነገር አላውቅም፤ ተጫዋቾች በወር ክፍያ ይጫወቱ” የሚል ሕግ ካወጣ በኋላም የክለቦች ወጪ ይበልጥ ቢንር እንጂ አልቀነሰም። በወቅቱ ፌዴሬሽኑ ይፋ በሚያደርገው የተጫዋቾች የደሞዝ ሒሳብ መሰረት ከፍተኛው የሃገሪቱ ወርሃዊ ተከፋይ አሥራት መገርሳ ሆነ። ተጫዋቹ ዳሽን ቢራ እያለ 66,666 ብር በ30 ቀን ቆጥሮ ይረከባል። ተመስገን ተክሌ እና በኃይሉ አሰፋ እያንዳንዳቸው ከነበሩበት ሀዋሳ ከተማና ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ 65 ሺህ እንዲሁም 66 ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ ሶስት ብር ይቀበላሉ። በወቅቱ በወጣው መረጃ መሰረትም የሊጉ 10ኛው ወርሃዊ ተከፋይ ቶክ ጀምስ እንኳን ከክለቡ ንግድ ባንክ ከ60 ሺህ ብር በላይ ይከፈለው ነበር። በቀጣይ ዓመት በነበረው ይፋዊ የደሞዝ ዝርዝር ላይ ደግሞ ኤሊያስ ማሞ በኢትዮጵያ ቡና ቤት ያለውን ውል ሲያድስ 95,135 ብር ወርሃዊ ደሞዝ ይከፈለው ነበር። በተጨማሪም በዚሁ ዓመት መከላከያ የቴዎድሮስ በቀለን ውል ሲያድስ እና ዐወል አብደላን ከሲዳማ ቡና ወደ ስብስቡ ሲያመጣ የተደራደረበት 88,724 ብር ወርሃዊ ደሞዝ ከኤሊያስ በመቀጠል ያለውን ከፍተኛ የደሞዝ ጣራ ቦታ አገኘ።

በ2009 የክረምት የዝውውር መስኮት ደግሞ ክለቦች እጅጉን ከፍተኛ የሆነ ደሞዝ ለተጨዋቾች እየከፈሉ ወርሀዊ የክፍያ መጠን መቶ ሺህን አለፈ። በዚህም ዓመት ዳዊት እስጢፋኖስ ከድሬዳዋ ከተማ ወደ ፋሲል ከነማ ሲዘዋወር በወር 166,922 ብር በማግኘት የዓመቱ ከፍተኛ የደሞዝ ተከፋይ ሆነ። ከዳዊት በመቀጠልም የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ጃኮ ፔንዜ ውሉን ሲያድስ የተስማማው 165,385 ወርሃዊ ደሞዝ የዓመቱ ሁለተኛ ውዱ ደሞዝ በመባል ተመዘገበ። በቀጣዩ የ2010 ክረምት የዝውውር መስኮት የተመዘገበው የተጨዋቾች ወርሃዊ ደሞዝ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እጅን አፍ ላይ የሚያስጭን እምርታ አሳይቷል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ህዳር 18 ቀን 2011 ባወጣው መረጃ መሰረትም የሊጉ ከፍተኛ ከፋይ ክለብ ኢትዮጵያ ቡናዎች ናቸው። በወቅቱ ኢትዮጵያ ቡናዎች ለአልሃሰን ካሉሻ 251,630 ብር ይከፍሉ ነበር። ከቡናዎች በመቀጠል አዳማ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር ለዳዋ ሁቴሳና አዳማ ሲሶኮ የሚከፍሉት 228, 462 ብር ሁለተኛው የዓመቱ ከፍተኛ ወርሃዊ ገንዘብ ሆኖ ተፅፏል። ነገር ግን በዚሁ ዓመት አጋማሽ ላይ በተከፈተ የውድድር አካፋይ የዝውውር መስኮት ይህ ወርሃዊ ክፍያ በ53 ሺህ አደገ። ጅማ አባጅፋሮች ኦኪኪ አፎላቢን በ304,000 ወርሃዊ ደሞዝ ባስፈረሙት ውል አማካኝነት።

ከቆሎ የጀምሮ ለተጫዋቾች የሚሰጥ የሙያ ጥቅም ከ10 ወራት በፊት ልጓም ተበጅቶለታል። በዚህም ክለቦች ለተጫዋቾች የሚከፍሉት የደሞዝ መጠን ከ50 ሺህ ብር እንዳይበልጥ ሆኗል። እርግጥ ውስጥ ውስጡን ክለቦች ለተጫዋቾች ከ50 ሺህ ብር በተጨማሪ ሌላ ክፍያ እንደሚሰጡ ቢወራም በይፋ በተቀመጠ መረጃ ግን ተጫዋቾች 50 ሺህ ብር በደሞዝ እየተቀበሉ ይገኛሉ።

የተጫዋቾች የዝውውር እና የክፍያ ሁኔታ ከድሮ እስከ ዘንድሮ ከላይ በተገለፀው አካሄድ መልኩን እቀያየረ እዚህ ደርሷል። ያልተለወጠው አካሄድ የዝውውር አካሄዱ ብቻ ነው። ያኔም ክለቦች ጉዳያቸውን የሚፈፅሙት ከተጫዋቾች ጋር ነው፤ አሁንም ምንም እንኳ በመሐላቸው ወኪል ቢኖርም ግንኙነቶች የክለቦች እና የተጫዋቾች ነው። በሌላው ሀገር የሚታየው የክለቦች ከክለቦች ግንኙነት በጥቂት አጋጣሚዎች ካልሆነ በኢትዮጵያ የዝውውር ታሪክ ውስጥ ቦታ የለውም። ተጫዋች የአንድ እና ሁለት ዓመት ኮንትራት ብቻ የሚፈርም በመሆኑ ከኮንትራት ነፃ ሲሆን ከክለቦች ጋር በነፃነት ይደራደራል።

ከላይ ከተጠቀሰው ጋር በተያያዘ የክለቦች ተጠቃሚነት ድሮም ሆነ ዘንድሮ ተመሳሳይ በአንድ ጎኑ ብቻ የሚታይ ነው። ክለብ ተጫዋችን ገንዘብ ከፍሎ ይቀጥራል። ተጫዋቹ ስኬታማ ጊዜ ካሳለፈ ቀጣሪው ክለብ በሜዳ ላይ ብቃቱ ይጠቀማል። ኮንትራቱ ካለቀ ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ ከፍሎ ያስቀጥለዋል፤ ካልሆነ ተጫዋቹ ወደ ሌላ ክለብ ይጓዛል። በዚህ ሒደት ክለቡ ከተጫዋቹ የሚያገኘው በሜዳ ላይ የሚያሳየውን ብቃት ካልሆነ በቀር የኮንትራት ጊዜው አጭር በመሆኑ ለሽያጭ በማቅረብ ገንዘብ በማግኘት የሚጠቀምበት መንገድ ዝግ ነው።

በኮንትራት ረገድ በድሮ እና ዘንድሮ መካከል ያለው ልዩነት እምብዛም ነው። የፊርማ ክፍያ መጀመር ያመጣው ልማድ ተጫዋቾች በአጭር ኮንትራት በፈረሙ ቁጥር ከውል ነፃ ሲሆኑ የፊርማ ክፍያቸውን በማናር ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸው ቆይቷል። በዚህም ምክንያት የረጅም ዓመት ኮንትራት መፈረም ለተጫዋቾች ራስን በራስ የማጥፋት ያህል ይቆጠር ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በይፋ የፊርማ ክፍያ እንዲቀር ቢደረግም አሰራሩ ግልፅነት የጎደለውና አፈፃፀሙ ላይ ጥርጣሬ የሚያሳድር በመሆኑ ተጫዋቾች አሁንም የፊርማ ክፍያ እንደሚቀበሉ ሀሜታ እንዲበዛ ሆኗል። በአግባቡ በወርሀዊ ደሞዝ የሚጫወቱትም ቢሆን አጭር ኮንትራት ምርጫቸው መሆኑ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

በቀጣይ ጊዜያት የዝውውር መስኩ የተለየ አካሄድ ይኑረው አይኑረው አሁን ላይ ሆኖ መገመት አዳጋች ነው። ነገር ግን የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖውን የማያሳርፍበት ዘርፍ አይኖርምና የእግርኳሱ ኢኮኖሚ ሁኔታ የዝውውር ባህላችንን መልክ ሊያስይዘው የሚችልበት እድል ይኖራል ተብሎ ይታሰባል። ክለቦች ኢኮኖሚው እስኪረጋጋ ከመንግሥት የሚያገኙት በጀት እንደከዚህ ቀደሙ ከፍተኛ ላይሆን ይችላል። ይህን ተከትሎ የዝውውር ሥርዓቱን በራሱ ገንዘብ የሚያመነጭ ለማድረግ ሊገደዱ ይችሉ ይሆናል። የተጠኑ ዝውውሮች፣ ረጅም የኮንትራት ጊዜዎች፣ የሽያጭ ሥርዓት እና የመሳሰሉትን የምንመለከትበት አስገዳጅ ጊዜ ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ