የዘመኑ ከዋክብት | ዳግም የተወለደው ዮናስ ግርማይ

የዘንድሮ የውድድር ዓመት እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ጥሩ እንቅስቃሴ ካሳዩት የመሐል ተከላካዮች አንዱ የነበረው ዮናስ ግርማይ የዛሬው የዘመኑ ከዋክብት አምድ እንግዳችን ነው።

የእግር ኳስ ሕይወቱን በትራንስ ኢትዮጵያ ሦስተኛ ቡድን ጀምሮ በፕሪምየር ሊጉ ለሚገኙ በርካታ ክለቦች ተጫውቷል። በትራንስ ኢትዮጵያ የመጨረሻ ዓመታት በዋናው ቡድን ደረጃ መጫወት ጀምሮ በወቅቱ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ የነበረው ይህ ተከላካይ አሳዳጊ ክለቡ ከፕሪምየር ሊግ መውረዱ እና ቆይቶም ሙሉ ለሙሉ መፍረሱ ተከትሎ ለሰበታ ከተማ ፊርማውን በማኖር ከክለቡ ጋር ቆይታ አድርጓል። ከሰበታ ጋር ባሳየው ጥሩ ብቃት በወቅቱ ጥሩ ስብስብ ወደ ነበረው ዳሽን ቢራ በ2007 ያመራው ዮናስ ምንም እንኳ የመጀመርያ ዓመት የዳሽን ቆይታው በውጣ ውረዶች የተሞላ ቢሆንም በሁለተኛው ዓመት ግን በተሻለ ብቃት እና ወጥነት ቡድኑን ያገለገለበት ዓመት ነበር።

በመጀመርያ ዓመታት የእግር ኳስ ቆይታዎቹ ከእድሜው አንፃር ሲታይ የተሳካ ጊዜ የነበረው ይህ ተከላካይ ዳሽን ቢራ በ2008 መውረዱን ተከትሎ ከፈረሰ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መድን አምርቶ ከክለቡ የአንድ ዓመት ቆይታ በማድረግ ወደ መቐለ 70 እንደርታ ቢያመራም የክለቡ የአንድ ዓመት እና ስድስት ወር ቆይታው ያልተሳካ እና የእግርኳስ ሐይወቱ መጥፎ ግዜያቶች ነበሩ።
ይህን ተከትሎም በ2011 የውድድር ዓመት አጋማሽ ወደ ስሑል ሽረ አምርቶ ክለቡ በፕሪምየር ሊጉ እንዲቆይ ካስቻሉት ቁልፍ ተጫዋቾች አንዱ በመሆን በድጋሚ ማበብ ችሏል። በዘንድሮው የውድድር ዘመን ደግሞ በብዙ ረገድ ተሻሽሎ በመቅረብ በእግርኳሱ ድጋሚ መወለዱን አስመስክሯል።

በበርካታ ጨዋታዎች ቡድኑን በአምበልነት የመራው እና በርካታ ጨዋታዎች ላይ ግብ ሳይቆጠርበት የወጣውን ጠንካራ የተከላካይ ክፍል በመምራት የተሳካ ጊዜ ካሳላፉ የመሐል ተከላካዮች አንዱ ነበር። ተጫዋቹ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደርገው ቆይታ እንደሚከተለው ይዘንላቹ ቀርበናል።

ጊዜውን የሚያሳልፈው..

አብዛኛው ጊዜዬን ቤቴ ውስጥ ነው የማሳልፈው አስፈላጊ ካልሆነ ከቤት አልወጣም። አንዳንዴም በግሌ ልምምዶች እሰራለው።

እግር ኳስ ተጫዋች ባይሆን..

እግር ኳስ ተጫዋች ባልሆን በትምህርቱ እገፋ ነበር። ከኮንስትራክሽን ጋር በተያያዘ ሞያ ላይ እሰማራ ነበር፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ፍላጎት ነበረኝ። ትምህርትም ጀምሬ ነበር፤ በአጋጣሚ ግን በየሳምንቱ ከከተማ ውጭ ጉዞ ስለምናደርግ በትኩረት መከታተል ስላልቻልኩ መቀጠል አልቻልኩም።

ስለ ቅጣት ምት ዓመታት ብቃቱ

በልምምድ ያዳበርኩት ነው። በተለይም በመጀመርያዎቹ የእግርኳስ ዓመታት በልምምድ ቦታ ላይ ብዙ እለማመድ ነበር፤ በጨዋታ ላይም ከቅጣት ምት ያስቆጠርኳቸው ብዙ ግቦች አሉኝ።

የማይረሳት ጎል

የማልረሳት ጎል ትራንስ ኢትዮጵያ እያለው መብራት ኃይል ላይ ያስቆጠርኳት የቅጣት ምት ግብ ነች። ሁለታችንም ላለመውረድ ነበር የተጫወትነው። በዛ ጨዋታ የግድ ማሸነፍ ስነበረብን ያስቆጠርኳት ጎልን አልረሳትም።

በተቃራኒ ሲገጥመው የሚያስቸግረው

አንድ ለአንድ ስንገናኝ የሚያስቸግሩኝ ተጫዋቾች አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ያሬድ ከበደ ናቸው።

ከማን ጋር ቢጣመር ደስ ይለዋል

እንደነ ያሬድ ባየህ እና ዓይናለም ኃይለ ከመሳሰሉ ምርጥ የመሐል ተከላካዮች ጋር ተጫውቻለው። ከነሱ ውስጥ አንድ ለመምረጥ ትንሽ ከባድ ቢሆንም ከዓይናለም ጋር ብጣመር ደስተኛ ነኝ። በዳሽን ቢራ እያለው አብሬው ተጫውቻለው፤ ሁሉም ነገር ያሟላ ተጫዋች ነው። መሪ ፣ ታጋይ እና ያለውን ነገር ለመስጠት የማይሰስት ተጫዋች ነው።

የልጅነት አርዓያው

ገረሱ ሸመናን ለትራንስ ሲጫወት እያየሁ ነው ያደግኩት። ለብዙ ተጫዋቾች አርአያ መሆን የሚችል ተጫዋች ነበር።

በእግር ኳስ ያዘነበት አጋጣሚ

አሳዳጊ ክለቤ ትራንስ ኢትዮጵያ ከፕሪምየር ሊግ ሲወርድ በጣም አዝኜ ነበር።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ