“የዘመናችን ከዋክብት ገፅ ” ከአምሳሉ ጥላሁን ጋር …

የፋሲል ከነማው የግራ መስመር ተከላካይ አምሳሉ ጥላሁን የዛሬ የዘመናችን ከዋክብት ገፅ እንግዳችን ነው። ወቅቱን እያሳለፈበት ካለው መንገድ እና ከሌሎች አዝናኝ ጥያቄዎች ጋር ይዘንላችሁ ቀርበናል።

ጎንደር ከተማ ተወልዶ ያደገው አምሳሉ ጥላሁን በቅርብ ዓመታት በፕሪምየር ሊጉ ስማቸው በጉልህ ከሚጠሩ የግራ መስመር ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። እግርኳስን የጀመረው በፋሲል ከነማ ወጣት ቡድን ሲሆን በ2004 ወደ አውሥኮድ በማምራት ሁለት የተሳኩ የውድድር ዓመታት ማሳለፍ ችሏል። በመቀጠል በ2006 ወደ ትውልድ ከተማው ተመልሶ ዳሽን ቢራን በመቀላቀል ከፕሪምየር ሊጉ ጋር መተዋወቅ የቻለ ሲሆን ዳሽን ከወረደና ቡድኑን ካፈረሰ በኋላም ወደ ፋሲል ከነማ በማቅናት ከ2009 ጀምሮ በወጥተነት ስኬታማ የሚባሉ ጊዜያትን እያሳለፈ ይገኛል። የግራ መስመር ተከላካዩ በአብርሃም መብራቱ አማካኝነት ከብሔራዊ ቡድኑ በተደጋጋሚ ጥሪ እንደደረሰውም የሚታወስ ነው። በአሁኑ ወቅት የፋሲል ከነማ ሁለተኛ አምበል የሆነው አምሳሉ ጥላሁን የኢትዮጵያ ዋንጫን እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ከክለቡ ጋር ሲያነሳ በሊጉ ላይም ዓመቱን ሙሉ በወጥ አቋም በመዝለቅ ከወቅቱ ኮከቦች መሀል አንዱ መሆኑን እያሳየ ይገኛል።

ጊዜህን በምን እያሳለፍክ ነው ?

ጠዋት ተነስቼ መስራት ያለብኝን ልምምድ እሰራለሁ። ልምምድ ጨርሼ የተወሰነ ሰዓት እረፍት አደርጋለሁ። ከዛም ከአምስት ሰዓት በኋላ የተወሰኑ ሰዓታትን ከልጆቼ ጋር ነው የማሳልፈው። ከዚያ በኋላ የያለውን ጊዜ ከሠፈር ልጆች ጋር ነው የማሳልፈው፤ የተለያዩ ነገሮችን በመስራት በብዛት ከሠፈር ልጆች ጋር ነው ጊዜዬን የማሳልፈው።

እግር ኳስ ተጫዋች ባትሆን ምን እሆናለሁ ብለህ ታስባለህ ?

(እየሳቀ …) እግርኳስ ተጫዋች ባልሆን ምን እንደምሆን ግራ ነው የሚገባኝ ። በጣም ከባድ ነው፤ ይሄን እሆናለሁ ብዬ አላስብም። መጀመሪያም እግር ኳስ ተጫዋች እሆናለሁ ብዬ አላስብም ነበር። ነገሮች ሲመቻቹ ነው እግር ኳስ ተጫዋች የሆንኩት እና ይህ ነው የምለው ነገር የለኝም።

ካስቆጠርካቸው ጎሎች የማትረሳው ?

አብዛኞቹ ግቦቼ አምስት ወይም ስድስት የሚሆኑት ቅጣት ምት ናቸው። ከእነሱም ውስጥ የማልረሳው መቐለ ላይ ከደደቢት ጋር ስንጫወት ያስቆጠርኩትን ነው። ጨዋታው በጣም ጫና ነበረው፤ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ውጥረቶች ስለነበሩ። በዚያ ላይ የመጀመሪያ ግብ ስለነበር እና እኔም ካለው ውጥረት አንፃር እንዳገባሁ ራሴን እንኳን አላውቅም ነበር። ያው ያልተገቡ ቃላት ከተመልካች ሲሰነዘሩ ስለነበርና የዚሁ አካበቢ (ጎንደር) ልጅ ስለሆንኩ ለየት ያለ ስሜት ይኖረዋል እና ያን ግብ አልረሳውም። ጨዋታው ላይ ብዙ ነገር ሆነን ነው የወጣነው፤ ማስታወስም አልፈልግም።

ከገቡባችሁ ግቦች በጣም ያዘንክበትስ ?

ከገቡብን ግቦች በህይወቴ የማልረሳው እና ቅስሜን የሰበርው ሽረ ላይ የተቆጠረብን ግብ ነው። ግብ ነው ማለት ይከብደኛል ፤ ፍፁም ቅጣት ምት ነበር። እኛ ቻምፒዮን የምንሆንበት ጨዋታ ነበር። እና ያንን ግብ ማየትም አልፈልግም ነበር ፤ ግቡ ሲቆጠር አላየሁትም። ያ ግብ ነበር በጣም ያስከፋኝ።

ከተቆጠሩባችሁ ግቦች የማትረሳው ድንቅ ግብ ?

ከሲዳማ ቡና ጋር ስንጫወት ጎንደር ላይ ወንድሜነህ ዓይናለም ከሳጥን ውጪ ሳማኪ ላይ ያስቆጠረው ግብ ነው ፤ እስካሁን ዓይኔ ላይ አለ። በጣም በሚገርም ሁኔታ በሜዳቸውም ተመሳሳይ ግብ አስቆጥሮብን ነበር። እና እንዴት እንደሚመታው ሁሉ ይገርመኛል። ከተቆጠሩብን ድንቁ ግብ ለኔ እሱ ነው።

በተቃራኒ ስትገጥመው ይከብደኛል የምትለው ተጫዋች?

እኛ የምንጫወተው እንደ ቡድን ነው። ግን ለየት ያለ ተጫዋች ካልክ እነአቡበከር ናስር ፣ አቤል ያለው እና ሌሎችም አሉ። የእነሱ መክበድ ሳይሆን ይበልጥ በጥንቃቄ እንድትጫወት ያደርጉናል። ፈጣኖች ስለሆኑ ተጠንቅቀሀቸው እና ትኩረት ሰጥተሀቸው እንድትጫወት ያደርጉሃል።

በእግር ኳስ የቅርብ ጓደኛህ ማነው ?

ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ዳሽን ቢራ እያለሁ ኤርሚያስ ኃይሉ ፤ ለፕሪምየር ሊጉም አዲስ ስለነበርኩ ከሱ ጋር ነበር ብዙ ነገር ያሳለፍነው። ከዚያ በኋላም ቴዎድሮስ ጌትነት ፣ ፍፁም ዓለሙ (አሁን በህርዳር ከተማ ያለው) ከነሱ ጋር ደግሞ በፋሲል ቤት ብዙ ነገር አሳልፈናል። ሌሎችም አሉ ግን ከቴዲ፣ ከኤርሚያስ እና ፍፁም ጋር በኳስ ያሳለፍኳቸው ለየት ያሉ ትውስታዎች አሉኝ።

በእግር ኳስ ያዘንክበት እና የተደሰትክበት ጊዜ ?

ያዘንኩበት ሽረ ላይ በተፈጠረው ነው። ከዛም በላይ ግን ዳሽን በወረደ ጊዜ በጣም አዝኜ ነበር። እንደ ጎንደር ልጅ እና እንደ ጎንደር ማኅበረሰብ ብዙ ልጆችን ማፍራት የሚችል ክለብ ነበር ዳሽን ቢራ። እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሪምየር ሊግ የተጫወትኩት በዳሽን ነው። እና ዳሽን በመውረዱ በጣም ነበር ያዘንኩት። ብዙ የጎንደር እና የአካባቢው ልጆች ማደግ ይችሉ ነበር። ፋሲል ከነማን ብቻ አይጠብቁም ነበር። ቢያንስ ከዚህ አምስት ሰው በቢጫ ቴሴራ ሲይዙ ከዛም አምስት ይይዙና አማራጮች ይሰፉ ነበር። ፉክክር ሲኖር ኳሳችንም ያድግ ነበር። ለከተማውም ሁለት ክለብ ቢኖር በጣም ጥሩ ነበር እና በእግር ኳስ ህይወቴ ያዘንኩት በእነዚህ ሁለት አጋጣሚዎች ነው። የተደሰትኩበት ቀን መቐለ 70 እንደርታን አዲስ አበባ ላይ በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ስናሸንፍ ነው። ለኛ ትልቅ ትርጉም የነበረው ጨዋታ ነበር። ፕሪምየር ሊጉን ያጣንበት መንገድ የሚያስቆጭ ስለነበር ያንን ዋንጫ አንስተን ደጋፊያችንን መስደሰት ነበረብን። በዚያ ላይ እልህ ስለነበረብን በጣም ነበር ደስተኛ የነበርኩት። እኔ ብቻ አይደለሁም የቡድን አጋሮቼም ደስተኛ ነበሩ። ደጋፊዎችም ‘ያንን ዋንጫ በላን ማለት ፕሪምየር ሊጉን በላት ማለት ነው’ እያሉ በተደጋጋሚ ሲነግሩን ስለነበር ከላው ነገር አንፃር ውጥረት ነበረው እና ተጨንቀንም ነበር። በመጨረሻም ዋንጫውን አንስተን ለደጋፊዎች ስለሰጠናቸው በጣም ደስተኛ ነበርኩ።

ከዚህ በኋላ በእግር ኳስ ማሳካት የምትፈልገው ?

የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት እፈልጋለሁ። ከሀገር ወጥቼ መጫዎትም እፈልጋለሁ። ሀገሬንም በደንብ ባገለግልም ደስ ይለኛል። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከፋሲል ከነማ ጋር የማንሳት ትልቅ ፍላጎት አለኝ። የህዝቡ ጉጉት ምን ያህል እንደሆን አውቃለሁ። የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማሳካት ከቻልን የህዝቡ ደስታ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ይገባኛል።

አሁን ውድድር ቆሟል ፤ እንቅስቃሴ ላይ የፈጠረብህ ተፅዕኖ ምን ያህል ነው?

እንዳየኸው ነው። እኔንም መጥተህ ያገኘኸኝ ስፖርት ሜዳ ላይ ነው። እኛ ሀገር አብዛኞቻችን ዕረፍት ሲባል መስራት አይታየንም ፤ ማረፍ ብቻ ነው። አሁን ለምን ያህል ጊዜ እንደምናርፍ አናውቅም። ስለዚህ ጠንክረን በምንችለው መጠን መስራት አለብን። ቢያንስ እንኳን አንድ ቀን እያረፍን ላብ ማውጣት አለብን። ውድድሩ ሲጀምር እንቸገራለን። ይሄ በራሱ ትልቅ ተፅዕኖ ነው ያለው። በቻልነው አቅም ተጠንቅቀን ከሰው ርቀን ቤት ውስጥ ሆነን በተገኘው አጋጣሚ እንቅስቃሴ ብናደርግ ጥሩ ነው።

የጎንደር ልጅ ከመሆንህ አንፃር ራስ ግንብ ቤተ-መንግሥት እና የባህል ሙዚየም ጎብኝተህ ታውቃለህ?

(እየሳቀ… )  ራስ ግንብ ሲባል እሰማለሁ፤ አይቼው ግን አላውቅም። ያው ብዙ ተጫዋቾች ከሌላ ቦታ እንደመጡ የጎንደርን ታሪክ ነው ማወቅ የሚፈልጉት። እኛ ደግሞ ጎንደር ያለነው ‘የኛ ነው’ ብለን ስለምናስብ ትኩረት አንሰጠውም። (እየሳቀ…) ፋሲል ግንብን ራሱ 4ኛ ክፍል እያለሁ በትምህርት ቤት እንዳየሁት ነው። ከዚያ በኋላ ለሠርግ ስሄድ ምናምን እገባለሁ እንጂ መጎብኘት አይባልም። ሰዎች ከአውሮፓ እና ከኤዢያ ከሌሎች ቦታዎች መጥተው እያዩት እኔ ትኩረት ሰጥቼ አይቸው አላውቅም። እንዲያውም ከዚህ በኋላ እንደዚህ ዕረፍት በሆንኩባቸው ወቅቶች እንዚህን ነገሮች ትኩረት ሰጥቼ መጎብኘት እፈልጋለሁ። ሌሎችም እነዚህን የታሪክ አሻራዎች ትኩረት ሰጥተው ቢጎበኙ ጥሩ ነው እላለሁ። ምክንያቱም ከዚህ በፊት ይሄን ያህል ዕረፍት አግኝተን አናውቅም። ለምሳሌ የዛሬ ዓመት ፕሪምየር ሊጉ እንደተጠናቀቀ ወዲያው ወደ ዝግጅት ገባን ፤ አንድ ወር እንኳን አልነበረንም። እና ይህ አጋጣሚ መዝናኛም ይሆናል ፤ ታሪክም ይታወቅበታል። እና ጎንደር ያለ ስፖርተኛ እና የአካባቢው ማህበረሰብ የራሱን ታሪክ ቢያውቅ ደስ ይለኛል። ”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ