አስተያየት | የታዳጊና ወጣት ቡድኖቻችን የስልጠና ስርዓት

በየትኛውም ሀገር በእግርኳስ እድገት ለማምጣትና በየደረጃው ጠንካራ ብሔራዊ ቡድኖችን ለመገንባት በየሃገራቱ የሚገኙ ክለቦች የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ የላቀ ነው፡፡ ሐሳቡን በቀላል አገላለፅ ለማስቀመጥ “ ያለ ጠንካራ ክለቦች እና ሚዛናዊ ፉክክር የሌለበት ሊግ  የተደራጀ ብሔራዊ ቡድን ሊኖር አይችልም፡፡” ከዚህ በመነሳት በየእድሜ እርከኖቹ ደካማ ብሔራዊ ቡድኖች የሚያቀርበው ብሔራዊ ቡድናችን የደካማ ክለቦቻችን ነፅብራቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በብቁ የአመራር አካላት እጥረት፣ የጥራት ደረጃቸው በወረዱ የመጫወቻ ሜዳዎች፣ ተገቢ ትኩረት በማይቸራቸው የልምምድ ማዕከላት፣ በእቅድ የመመራት ልማድ ባልዳበረበት የሥልጠና ከባቢ፣ በነባር የስልጠና ሥርዓት የማዝገም ሒደት፣ ከእግርኳስ ትርፍ የማግኘት አሰራር እጦት፣ ድክመት የሚታይበት የደጋፊዎች ምዝገባ ወይም አያያዝ እና መሰል ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሰለባ የሆኑት ክለቦቻችን ዛሬ ላነሳው በወደድኩት የታዳጊዎች ስልጣና ደግሞ እጅጉን ኋላ-ቀር ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

እንደሚታወቀው የሃገራችን ክለቦች ደረጃቸውን የጠበቁ የታዳጊ ማሰልጠኛ ማዕከላት ስለሌላቸው ታዳጊዎችን በተለያየ አማተራዊ የምርጫ መስፈርት በመመልመል ወደ ቡድናቸው ይቀላቅላሉ፡፡ በየውድድር ዓመቱ መጀመሪያ የሚደረገው ምልመላ ለታዳጊ ተጫዋቾች በጣም አሰልቺ፣ እጅጉን አድካሚና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ብቃታቸውንም ለመለየት እንኳ የማያስችል ሆኖ ይገኛል፡፡ “አድርጎልን!” ደረጃቸውን የጠበቁ ማሰልጠኛ ማዕከላት ቢኖሩን እንኳ ታዳጊዎችን ተቀብሎ በየክለቦቹ ባሉ ከአስራ ሰባት ዓመት እና ከሃያ ዓመት በታች ቡድኖች ውስጥ የማስገባት እድሎች ሲመቻቹ ተጫዋቾቹን በተገቢው መንገድ የማሳደግና ፍሬያቸውን በትዕግስት የመጠበቅ ሁኔታ አሁን ባለው አሰራር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ይህን የማድረግ ከልብ የሆነ ፍላጎት እና መልካም ፍቃደኝነቱ አብዛኞቹ ክለቦች ጋር የለም፡፡ የእነዚህን ታዳጊዎች ተፈጥሯዊና በልምምድ የተገኘ ክህሎት ከፍ ባለ ደረጃ አሳድጎ፣ አካላዊና አዕምሯዊ እድገታቸውን ተከታትሎ፣ ስነ-ልቦናዊ ጥንካሬያቸውን አጎልብቶና ሥነ-ምግባራቸውን ሞርዶ ወደ ከፍታ የሚያሻግር የስልጠና ሥርዓት አልተዘረጋም፡፡ የሃገራችን አብዛኞቹ ክለቦች ለወጣት ተጫዋቾች እድገት ዘላቂ እቅድ የማቀድ አስተማማኝ አቅም አልገነቡም፡፡ በዘመናዊ ስልጠናና አያያዝ እነዚህን ታዳጊና ወጣት ተጫዋቾች ብቁ የማድረግ ፍላጎት፣ ትዕግስትና  ተስፋ አይታይባቸውም፡፡ ባሉት ማዕከላትም የሚታየው ዝርክርክ አሰራር ባለክህሎቶቹን ተጫዋቾች “እግርኳስ ለምኔ?” የሚያስብል ሆኖባቸው ከስፖርቱ ሸሽተዋል፡፡

ክለቦቻችን በታዳጊ ተጫዋቾች ላይ የረጅም ጊዜ እቅድ አይነድፉም፡፡ ለዚህ ችግር በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ክለቦቹ ዘንድ ታዳጊ ተጫዋቾችን በብዛትና በጥራት ትልቅ ደረጃ ለማድረስ የመጣር ጉጉትና ፍላጎት አለመኖሩ ነው፡፡ ይህን ከማድረግ ይልቅ በተጫዋቾች ዝውውር ላይ በማተኮር የገንዘብ፣ የጊዜና የክህሎት ብክነት ይፈጽማሉ፡፡ በላይኞቹ የሊግ እርከኖች የውል ዘመናቸው እስኪያከትም ድረስ ጥቂት የመሰለፍ እድል ለሚያገኙና የረባ ግልጋሎት ለማይሰጡ ተጫዋቾች በሁለት ዓመት እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚደርስ ደመወዝ መክፈሉን ቀዳሚ ተግባራቸው ያደርጉታል። የሃገራችን ክለቦች በእግርኳስ አስተዳዳሪው አካል የሚጣልባቸውንና ታዳጊዎችን የማወዳደር ግዴታን
ለመወጣት ብቻ ሲሉ እምብዛም ትኩረት የማይሰጧቸውን የታዳጊና ወጣት ቡድኖች ያቋቁማሉ፡፡ የአወዳዳሪ አካል ግዴታን ለመተግበርና ከቅጣት ለማምለጥ እንጂ እነዚህን ቡድኖች ለመገንባት የሚፈልጉት ከልባቸው አይደለም፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እግርኳሳዊ ራዕይ ያለው አመራር በክለቦች አለመኖር ነው፡፡ ይህን ራሴ ባጋጠመኝ ተመክሮ ላስረዳ፦ በአንድ ወቅት በከተማችን የሚገኝ አንድ ትልቅ የፕሪምየር ሊግ ክለብ አስተዳደርን ለሥራ ጉዳይ ለማነጋገር ከባልደረባዬ ጋር ሆነን ቢሮዋቸው ተገኝን፡፡ በሚመሩት ክለብ ስላላቸው የታዳጊዎች ቡድን እቅድ ስንወያይ ” ከሃያ ዓመት በታች ቡድናችንን የያዘው አሰልጣኝ ተተኪዎች እንዲያፈራና ለዋናው ቡድን እንዲያበረክት እንፈልጋልን፡፡ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድናችን ደግሞ ቀደም ብሎ ሲሰለጥን በነበረው አሰልጣኝ ሥር ዋንጫ ሲያገኝ ነበር፡፡ እርሱ (አሰልጣኙ) ዋንጫ ስላስለመደን  ሌላም አሰልጣኝ ሲመጣ ይህንኑ ዋንጫ እንዲያመጣልን ነው የምንፈልገው፡፡” አሉን፡፡ ይህ እንግዲህ አስተዳደሩ ከሞላ ጎደል ለሁለቱ የታዳጊና ወጣት ቡድን ያላቸውን ዓመታዊ እቅድ ያሳያል፡፡የታዳጊዎች ስልጠና ውጤታማነት በዋንጫ አለመመዘኑን ለምናምንና ታዳጊዎችን ለምናሰለጥን ባለሙያዎች ይህን የአጭር ጊዜ ዕቅድ ከአንድ ትልቅ ክለብ አመራር መስማት አስደንጋጭ ሆነብን፡፡ በእርግጥ በሰውየው መፍረድ አይቻልም፡፡ አጠቃላይ የሃገራችን የእግርኳስ አመራር ሥርዓት የፈጠረው ይመስለኛል፡፡ በርካታ የክለብ አመራሮች አመለካከታቸው ተመሳሳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ብዙዎቹ የእግርኳስ አስተዳደር ሰዎች የታዳጊና ወጣት ቡድናቸውን አሰልጣኞች ውጤታማነት የሚለኩት “ምን ያህል የበቁ ተጫዋቾችን ለዋና ቡድን አደረሱ?” በሚለው መስፈርት ሳይሆን በታዳጊዎች ውድድር በሚያገኙት የዋንጫ ብዛት ነው፡፡ ይህ ምናልባት መጥፎ መስፈርት ላይሆን ይችላል፤ ነገርግን ብቸኛውም መመዘኛ መሆን አይገባውም፡፡ በሃገራችን በታዳጊዎች ውድድር ቡድኖች ዋንጫ የሚያሳኩባቸው ብልሹ አሰራሮች ተቆጥረው አይዘለቁም፡፡ የእድሜ ማጭበርበር ዋነኛው ነው፡፡ ለጊዜያዊ ውጤት ሲባል ለወደፊት እድገት የማይመቹ የስልጠና መንገዶችና የጨዋታ ዘይቤዎችን መከተልም ሳይጠቀስ የማይታለፍ በውድድሩ “ውጤታማ” ሲያስደርግ ታስተውሏል፡፡ የዳኝነት ችግሮችና የሥርዓት አልበኛ ደጋፊዎች  ተጽዕኖም በአጭር ጊዜ ስኬትን ለሚሹት አካላት አቋራጮቹ መንገዶች ሆነው “ጥቅም” ላይ ውለው ያውቃሉ፡፡ ይህ አስተዳደራዊ አመለካከትና የአመራር ሥርዓት እግርኳሳችን ላይ በሁለት መንገድ ጉዳት አስከትሏል፡፡ አንደኛው የምርጦቹንና የባለክህሎቶቹን ታዳጊዎች አቅም  በአግባቡ በማጎልበት ነገ የተሻለ ስብዕና ያላቸው አዋቂ ተጫዋቾችን እንዳናገኝ አደረገን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሃገራችን ዘላቂ የእግርኳስ እድገት ይልቅ ለጊዜያዊ ውጤት ብቻ የሚያስቡና የሚሰሩ አሰልጣኞችን እንደናፈራ አስገደደን፡፡

ከታዳጊ እና ከወጣት ቡድኖቻቸው አዳዲስ ተጫዋቾችን ያሳደጉና በማሳደግ ላይ ያሉ በጣት የሚቆጠሩ ክለቦች አሁንም ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሃገራዊ ተልዕኮዋቸውን ለመወጣት ሌትተቀን የሚባዝኑ ክለቦቻችን ልፋታቸው ፍሬ አፍርቶ ቢያዩት መልካም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እንዚህ ክለቦችም ለታችኞቹ ቡድኖቻቸው የተሻለ እቅድ አውጥተው የሚሰሩ ሳይሆን በአብዛኛው በዋና ቡድን ከሚቀጠሩት አሰልጣኞች ፍላጎት ጋር በተያያዘ የሚተገብሩት እንደሆነ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ አስልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሎቲን (ሚቾ) ለዚህ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡ ሚቾ በክለቡ በቆየባቸው ዓመታት ለሌሎች የሃገራችን አሰልጣኞች አርአያ መሆን በሚያስችል መልኩ የክለቡን የታዳጊና ወጣት ቡድኖች ጨዋታ ለተመልካች በማይመቸው ጃንሜዳ ድረስ በመሄድ ይከታተል እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በዚህም እርሱ በቅዱስ ጊየርጊስ ባሳለፋቸው ዓመታት እንደ ኤሊያስ ማሞ፣ ምንተስኖት አዳነ፣ ዮናታን ብርሃኔ እና ሌሎችም በርካታ ታዳጊዎችን ወደ ዋናው ቡድን እንዲያድጉ በማድረግ ውጤታማ ተጫዋቾች አድርጓቸዋል። ከቅርብ ዓመታት በፊት አሰልጣኝ ውበቱ አባተም በሀዋሳ ከተማ ሳለ በርካታ ታዳጊ ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን ማሳደጉ ይታወሳል፡፡

ሌላው በክለቦች የታዳጊና ወጣት ቡድኖች ውስጥ የሚታየው ችግር የስልጠናው ይዘትና ጥራት ጉዳይ ነው ፡፡ እኔ እንደታዘብኩት በታዳጊዎች ስልጠና ላይ የተገቢ አሰልጣኞች ቁጥር ማነስ፣ በሳምንት ውስጥ ያለው የልምምድ ሰዓታት ማጠር፣ የስልጠና ድግግሞሽ መታየት፣ የዘመናዊ ማሰልጠኛ መሳሪያዎች እጥረት እና የእውቀት ችግርም ጎልቶ ይታያል፡፡ አንድ አሰልጣኝ ሃያ አምስት ተጫዋቾችን በሚያሰልጥንበት የታዳጊና ወጣት ቡድኖች በሳምንት ውስጥ በአብዛኛው ሁለት የልምምድ ቀናትና አንድ የጨዋታ መርኃግብር ብቻ መኖሩ ስልጠናውን አስቸጋሪ እና ዘላቂ ውጤት የሌለው እንዲሆን አስደርጓል፡፡ ለአጥቂዎች የጎል አጨራረስ ዘዴዎችን፣ በግልና በጋራ መከላከል እና ማጥቃት ላይ ያተኮሩ የልምምድ አይነቶችን፣ የሽግግር ሒደት ልምምዶች (Transition Phase Trainings)፣ የጨዋታ ምስረታ (Build-Up)፣ ተጫዋቾችን በሚጫወቱበት ቦታ በግልና በጋራ ከፋፍሎ ማሰልጠንና የመሳሰሉ አስፈላጊ የእግርኳስ ልምምዶችን ማሰራት እምብዛም አልተለመደም፡፡ በዚህ ደካማ የስልጠና ስርዓት ውስጥ እየኖርን ብቁ ተጫዋቾችን በዋናው ሊግና በብሔራዊ ቡድን ላይ መጠበቃችን አግባብ አይመስለኝም፡፡ ድርጊቱ ያልዘሩትን ለመሰብሰብ የመዘጋጀት ያህል ነው፡፡ ” በታዳጊና ወጣት ቡድን ሁለትና ሶስት ዓመታት ቆይቶ ግብ ከማስቆጠር ጋር መዛመድ ያልቻለን ተጫዋች በምን ሒሳብ ነው ብዙ ጎል እንዲያገባ የምንጠብቀው? በተለይ በዋናው ብሔራዊ ቡድናችን የሚታየው የታክቲክ አረዳድና አተገባበር ችግር ዋናው መነሻ ከዚህ እንደሆነ መረዳት ያቃተን ለምንድን ነው?  ክለቦቻችን በየእድሜ እርከኑ በያዟቸው ቡድኖች ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾች ስለ አጨዋወት ፍልስፍና፣ የጨዋታ ዘይቤና ዘመናዊ የእግርኳስ ታክቲክ ሐሳቦች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ይደረጋል ወይ?” የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ በሃገራችን የሚገኙ ክለቦች ውስጥ የሚገኙ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድኖች፣ ከሃያ ዓመት በታች ቡድኖች እና ዋናው ቡድን በተመሳሳይ የአጨዋወት ፍልስፍና እንዲሁም የጨዋታ ዘይቤ የመጫወት ልማድ አላዳበሩም፡፡ የየቡድኖቹ አሰልጣኞች የፈለጉትን መንገድ ይከተላሉ፡፡ ከዓመታት በፊት የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የታዳጊው፣ ወጣቱና ዋናው ቡድን ጨዋታዎች ሲያደርጉ ደጋግሜ የማየት እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ይመራ የነበረው የታዳጊው ቡድን በ 4-4-2 ፎርሜሽን ቀጥተኛና ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም የሚጫወት ቡድን እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በፋሲል ተካልኝ ይሰለጥን የነበረው የወጣቱ ቡድን ደግሞ በ4-3-3 ፎርሜሽን የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለመያዝ በአጫጭር ቅብብሎች ላይ ተመስርቶ ሲጫወት ታዝቤያለሁ፡፡ በተለያዩ አሰልጣኞች ሥር ያለፈው ዋናው ቡድን ደግሞ በ4-4-2 ፎርሜሽን መልሶ ማጥቃትና ረጃጅም ኳሶች የሚተገብር ቡድን ነበር፡፡ ይህ ኹነት በአንጋፋው ክለብ ብቻ የታየ አይደለም፤ አብዛኞቹ ክለቦች በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የሚዳክሩ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከታዳጊ እና ወጣት ቡድን ሾልከው ወደ ላይ የሚያድጉት ተጫዋቾች በዋናው ቡድን ለመላመድና ብቃታቸውን ለማሳየት ሲቸገሩ ተደጋግሞ ታይቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች ሃገራት አንጻር ሲነፃፀር በሃገራችን ያሉ ታዳጊዎች በአመት ውስጥ በቂ የጨዋታ ቁጥር አያገኙም፡፡ በዚህም ሳቢያ ወደ ላይኛው ደረጃ ሲሸጋገሩ በውድድሩ ያለውን ጫና ለመቋቋም በቂ የጨዋታ ልምድ አይዙም። የተጫዋቾች ደካማ አያያዝና ክትትልም ሌላኛው በክለቦችየ ታዳጊና ወጣቶች ስልጠና ስርዓት ላይ የሚታይ ችግር ነው፡፡ የመለማመጃና የመጫወቻ ጫማና መለያ በወቅቱ ካለማቅረብ ጀምሮ ተጫዋቾች ጉዳት ሲደርስባቸው ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ያለማድረግም ተጠቃሽ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ክለቦቻችን ከአስራ ሰባት እና ከሃያ ዓመት በታች ቡድኖች ብቻ ስላላቸው እና በሁለቱ ቡድኖች መሃል ደግሞ የእድሜ ልዩነት ስላለ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድን እድሜያቸው ሲያበቃ በለስ ካልቀናቸው ከክለብ ውጪ ይሆናሉ፡፡ ይህም ታዳጊዎቻችንን ለከፍተኛ  የሥነ-ልቦና ችግር እና ሱሰኝነት ይዳርጋል፡፡

 


ስለ ፀሐፊው

የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ  ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ