የወልዋሎ ተጫዋቾች ጥያቄ እና የክለቡ ምላሽ

የወልዋሎ ተጫዋቾች የደሞዝ አልተከፈለንም ጥያቄ ሲያቀርቡ የክለቡ ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ኪዳነ ሀፍተ ምላሽ ሰጥተውናል።

ከሦስት ሳምንታት በፊት ገደማ የወልዋሎ ተጫዋቾች የደሞዝ ጥያቄ እንዳላቸው እና ከወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ተዳምሮ ችግር ውስጥ እየገቡ እንዳሉ ጠቅሰው ነበር። በቁጥር በርከት ካሉ ተጫዋቾች የተነሳው ይህ የደሞዝ ጥያቄ ምንም እንኳ በክለቡ ጆሮ ዳባ ልበስ ባይባልም አብዛኞቹ ተጫዋቾች ውላቸው በቀጣይ ወራት የሚጠናቀቅ እንደመሆኑ ይህ ግዜ ካለፈ በኃላ ጥያቄያቸው ችላ እንዳይባል ስጋት እንዳደረባቸው አንዳንድ ተጫዋቾች ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። 

የተጫዋቾቹን ጥያቄ በመቀበል ከወልዋሎ ስራ አስከያጅ ኮማንደር ኪዳነ ሀፍተ ጋር ባደረግነው ቆይታም ስራ አስከያጁ ይህንን ምላሽ ሰጥተዋል።

“ትክክል ነው ደሞዝ አልተከፈሉም። የነሱ ደሞዝ ብቻ ሳይሆን የአሰልጣኞች እና የፅሕፈት ቤት ሰራተኞች ደሞዝም አልተከፈለም። ይህ ሊሆን የቻለውም በበጀት ችግር ነው፤ ከገቢዎቻችን ውስጥ የነበሩት የሜዳ ገቢ፣ የከተማ መስተዳደር የሚሰጠን ድጋፍ እና በዋናነት ደሞ ከዓድግራት ዩንቨርስቲ የነበሩትን ድጋፎች በወቅታዊው ችግር ምክንያት በግዜው ማግኘት አልቻልንም። ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ቅድም የጠቀስኳቸው ድጋፍ የሚደርጉልን አካላት በዋናነት በተፈጠረው ወረርሽኝ መከላከል ላይ ትኩረት በማድረጋቸው ነው። ” ብለዋል።

ክለቡ በቀጣይ የተጫዋቾቹን ጥያቄ ለመመለስ ምን አይነት እርምጃዎች ይወስዳል የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ኪዳኔ የተጫዋቾቹን ጉዳይ ለመፍታት የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ በጥረት እንዳሉ ገልፀዋል። “የተጫዋቾቹ የደሞዝ ጉዳይ በምንም ምክንያት ችላ የምንለው ጉዳይ አይደለም። ጉዳዩ በዋናነት ከሚመለከታቸው ዋና ዋና አምበሎች ባሉት ጉዳዮች እንነጋገራለን፤ ከሌሎች አካሎች በመሆንም መፍትሔ እየፈለግን ነው። ችግሩ የጋራ ችግር ነው ፤ ሁሉም የቡድኑ አባላት ተመሳሳይ ችግር አለው። ከወራት በፊት ችግሩ በተወሰነ መልኩ ለመፍታት ጥረቶች አድርገን ነበር ከአንዳንድ ደጋፊዎች በመሆን ግን አልቻልንም። ከከንቲባችን እና ከዓዲግራት ዩንቨርስቲ ጋር በመነጋገር ላይ ነን በቀጣይ በምን መንገድ ነው ችግሩ መቅረፍ የሚቻለው በሚል መፍትሔ ላይ እንደርሳለን ብዬ እገምታለው።
ፌደሬሽን የቀነ ገደብ ሕግ መከበር እንዳለበት አምናለው። የአቅም ጉዳይ እንጂ እኛም ደሞዝ የመክፈል ግዴታ እና የክለባችን አባላት ማክበር ስላለብን ችግሩን ለመፍታት እየሰራን እንደሆነ መታወቅ አለበት። ” ብለዋል።

ስራ አስከያጁ ከጠቀሱት ጉዳይ ውጭ በክለቡ የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች የሚታዩበት ሚዛን ልክ አይደለም ተብሎ የሚወራው ነገር ፍፁም ስህተህ መሆኑ ተናግረዋል። ” የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ደሞዝ ሳትከፍሉ ከውጭ ለመጡት ከፍላቹሀል ብለው የሚተቹን ነገር ፍፁም ፍፁም ስህተት ነው። በክለቡ እንደዚህ አይነት አሰራር የለም። በሌሎች የኢትዮጵያ ክለቦችም እንደዚህ ዓይነት አሰራር ይኖራል ብዬ አልገምትም።” ብለዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ