ይህንን ያውቁ ኖራል? (፬) | የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ክለቦች…

በተከታታይ 3 ሳምንታት ስለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ክለቦች እውነታዎችን ስናነሳ ቆይተናል። ዛሬም ሊጉ እና ክለቦችን የተመለከተውን ክፍል 4 ጥንቅር ይዘንላችሁ ቀርበናል።

*ማስታወሻ – እውነታዎቹ በኮቪድ-19 ምክንያት የተሰረዘው የ2012 ውድድርን አያካትቱም።

1 – በሊጉ የ22 ዓመት ጉዞ በርካታ ጨዋታዎችን ያሸነፈው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ቡድኑ በሊጉ በተካፈለባቸው 21 ዓመታት ባከናወናቸው 565 ጨዋታዎች በድምሩ 350 ድሎችን አግኝቷል።

2 – በሊጉ ታሪክ ባደጉበት ዓመት ዋንጫ የወሰዱ ክለቦች 2 ብቻ ናቸው። እነርሱም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋር ናቸው። ሊጉ በአዲስ መልክ እና መዋቅር በ1990 ሲጀመር ተሳትፎ ያላደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣይ ዓመት (1991) ከሁለተኛው የሀገሪቱ የሊግ እርከን በማደግ ዋንጫውን የግሉ ማድረግ ችሏል። በተመሳሳይ ጅማ አባጅፋር ከ19 ዓመታት (2010) በኋላ ይህንን ታሪክ በመስራት ስሙን የታሪክ መዝገብ ላይ አፅፏል።

3 – በአሁኑ ሰዓት በሊጉ ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል በእድሜ ትንሹ ስሑል ሽረ ነው። ቡድኑ በ2005 ዓ/ም ነበር የተመሰረተው። ቡድኑ ምስረታውን ካደረገ ከስድስት ዓመታት (2011) በኋላ ደግሞ ወደ ዋናው የሃገሪቱ የሊግ እርከን አድጓል።

4 – ከ1990 ዓ/ም ጀምሮ በሊጉ ከተሳተፉት 51 ክለቦች መካከል 5ቱ መጠሪያ ሥያሜያቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ቀይረዋል። በዚህም መብራት ኃይል ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ (1993)፣ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (2003)፣ ሐረር ቢራ ወደ ሐረር ሲቲ (2006)፣ ወልዲያ ከነማ ወደ ወልዲያ (2009) እንዲሁም ኒያላ ወደ ልደታ ኒያላ (2003) ሥያሜያቸውን ለውጠዋል። መቐለ 70 እንድርታ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ጅማ አባጅፋር ደግሞ ወደ ሊጉ ባደጉበት ክረምት ነበር ስያሜያቸውን የቀየሩት።

5 – እስካሁን በሊጉ በትንሽ የውድድር ዓመታት የተሳተፉ ክለቦች 12 ናቸው። እነሱም ፐልፕ እና ወረቀት፣ ብርሃንና ሠላም፣ ኦሜድላ፣ እህል ንግድ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ፣ ሜታ አቦ ቢራ፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ ጅማ አባ ቡና፣ ሀዲያ ሆሳዕና፣ ባህር ዳር ከተማ፣ ስሑል ሽረ እና አዲስ አበባ ፖሊስ ናቸው። እነዚህ 11 ክለቦች በሊጉ ላይ በአንድ የውድድር ዓመት ብቻ ነው ተሳትፎ ያደረጉት። (የዘንድሮ የውድድር ዘመን መሰረዙ ልብ ይሏል።)

6 – ከ1990 ጀምሮ በሊጉ እየተሳተፉ ካሉት ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ውጪ በሊጉ ለረጅም ዓመታት ያልወረደው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ቡድኑ ከ1991 ዓ/ም ጀምሮ በሊጉ መሳተፍ ከጀመረ በኋላ ለ21 የውድድር ዓመታት ወደ ታችኛው የሊግ እርከን አልወረደም። በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሊጉ አድጎ ለረጅም ዓመታት በሊጉ የዘለቀ ክለብ አስብሎታል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ18 የውድድር ዓመት ቀጣዩ ረጅም ዓመት የቆየ ክለብ ነው።

7 – ከመውጣት መውረድ ጋር በተያያዘ በወረዱበት ዓመት ተመልሰው የመጡ ክለቦች ስድስት ናቸው። እነሱም ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ (1993)፣ ወንጂ ስኳር (1996)፣ ጉና ንግድ (1996 እና 2000)፣ ኒያላ (1998 እና 2003)፣ ወልዲያ (2009) እና አዳማ ከተማ (2007) ናቸው።

8 – በሃገሪቱ ከሚገኙ ከተሞች ብዙ ክለቦችን በሊጉ ያሳተፈው ከተማ አዲስ አበባ ነው። መዲናዋ በድምሩ 15 ክለቦችን እስካሁን አሳትፋለች። እሱም ኢትዮጵያ መድን፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ሙገር ሲሚንቶ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኒያላ፣ ብርሃንና ሠላም፣ መከላከያ፣ ውሃ ስፖርት፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ እህል ንግድ፣ ኦሜድላ፣ ደደቢት እና አዲስ አበባ ከተማ ናቸው። (ክለቦቹ የተካተቱት መጀመሪያ መቀመጫቸውን ካደረጉበት ከተማ አንፃር ነው)

9 – ጅማሮውን ብሔራዊ ሊግ ብሎ የጀመረው ሊጉ ከ1990 ዓ/ም በኋላ በተደረጉት 22 የውድድር ዓመታት አራት የተለያዩ ሥያሜዎችን ተጠቅሟል። በዚህም ከ1992-1999 ፕሪምየር ሊግ፣ በ2000 ዓ/ም ላይ ሚድሮክ ሚሌኒየም ፕሪምየር ሊግ፣ በ2001 ሚድሮክ ፕሪምየር ሊግ ሲባል 2005 ላይ ደግሞ ፕሪምየር ሊግ መለስ ዋንጫ ተብሏል። ከ2006 ጀምሮ እስካሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመባል እየተጠራ ይገኛል።

10 – ሊጉ ላይ ከተሳተፉ 51 ክለቦች አንጋፋው እና እድሜ ጠገቡ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ቡድኑ በ1928 ዓ/ም በመመስረቱ እና ዘንድሮ 84ኛ የምስረታ በዓሉን በማክበሩ የሊጉ አንጋፋው ክለብ አስብሎታል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ