መንግሥቱ ወርቁ ሲታወሱ (፪) | የክለብ ታማኝነት ፣ የ8 ቁጥር ቁርኝት ፣ የሜዳ ላይ ብቃት እና የውጪ ዕድል

በህይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን በምናስታውስበት አምዳችን የቀድሞው እና በበርካቶች ዘንድ የምንጊዜውም ታላቅ እግርኳስ ተጫዋች እንደሆኑ የሚነገርላቸው መንግሥቱ ወርቁን ይዘን ቀርበናል። ታላቁን የእግርኳስ ሰው ማስታወስ በጀመርንበት ፅሁፉችን ከተወለደበት ቋራ ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን እስከተቀላቀለበት ጊዜ ድረስ ስላሳለፈው ህይወቱ አስነብበናችኋል። ዛሬ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጊዜውን፣ የሜዳ ላይ ክህሎቶቹን እና ወደ አውሮፓ ተሻግሮ ለመጫወት አጋጥሞት ስለነበረው ዕድል እናወሳለን።

ማስታወሻበገነነ መኩሪያ በመፅሀፍ መልክ የተዘጋጀው ከመንግሥቱ ወርቁ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ ፣ ‘ይድረስ ለባለንብረቱ’ የሚለው በፋንታሁን ኃይሌ ፣ ኃይማኖት ቃኘው እና ተዘራ አለነ የተዘጋጀው መፅሀፍ እና በልሣነ-ጊዮርጊስ ጋዜጣ መንግስቱ ወርቁ የተዘከሩባቸው ፅሁፎችን ለግብዓትነት ተጠቅመናል።

ታዳጊው መንግስቱ ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ ሊያደርግ የነበረውን የጎንደሩን ጉዞውን ሰርዞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ወደ ድሬዳዋ ቀጥሎም ወደ ናዝሬት በማምራት ባደረጋቸው ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ግቦች እስከወዲያኛው ከክለቡ ጋር እንዲቀጥል አድርገውታል። በዚህም ከ1951 – 1966 ለ16 ዓመታት በ1949 ክረምት ድሬዳዋ ላይ ከጥጥ ማህበር ጋር ካደረገው (በመጀመሪያው ፅሁፋችን የተጠቀሰው ) ጨዋታ አንስቶ ከቆጠርን ደግሞ ለ17 ዓመታት አካባቢ የቅዱስ ጊዮርጊስን መለያ አጥልቆ ተጫውቷል። በጨዋታ ዘመኑም የሌላ ክለብ መለያ አልለበሰም። በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስን ለ23 ዓመታት ካገለግሉት እና መንግሥቱንም ወደ ቡድኑ ከቀላቀሉት ሌላኛው ታላቅ የእግር ኳሳችን ባለውለታ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ በመቀጠል ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለበርካታ ዓመታት የተጫወተ ሁለተኛ ተጫዋች ሆኖ በታሪክ ይታወሳል።

ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው ያለመስዕዋትነት አልነበረም። የወቅቱ እግርኳሰኞች በገንዘብ ደረጃ ከስፖርቱ የሚያገኙት ጥቅም እምብዛም በመሆኑ በተጓዳኝ ህይወታቸውን የሚመሩበት ሥራ ሊኖራቸው ግድ ይል ነበር። በመሆኑም በወቅቱ ብዙ አቅም ባልነበራቸው እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓይነት ክለቦች ውስጥ ከሜዳ ውጪ ባሉ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ሳይማልሉ እና ወደሌሎች ክለቦች ሳይሄዱ ለረጅም ዓመታት መጫወት ቀላል አልነበረም። መንግሥቱም ለጊዮርጊስ ላለው የመለያ ፍቅር ከከፈላቸው መስዕዋትነቶች አንዱ በመብራት ኃይል መስሪያ ቤት ተቀጥሮ በሚሰራበት ወቅት የገጠመው ጉዳይ ነበር። መንግስቱ በአቪዬሽን የኤሌክትሪክ ትምህርት ምሩቅ የነበረ በመሆኑ በመብራት ኃይል ይሰራ ነበር ፤ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው የመስሪያ ቤቱ ስቶር ውስጥ በ325 ብር ደመወዝ። ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ ለቆቃ ግድብ ትራንስፎርመር መጥቶ ስለነበር ወደ ጣልያን ሀገር ሄዶ የመማር ዕድል እንደሚሰጠውም ቃል ተገብቶለት ነበር። በጊዜውም በእግር ኳሱ ቅዱስ ጊዮርጊስ መብራት ኃይልን 4-1 ባሸነፈበት ጨዋታ መንግስቱ ሦስት ግቦችን አስቆጠረ። “የኛን ደመወዝ እየበላ እንዴት መብራት ኃይል ላይ ያገባል? ” የሚል ጥያቄም ተነሳበት። ለመብራት ኃይል እንዲጫወት ብዙ ቢያግባቡትም አሻፈረኝ አለ። በመብራት ኃይል መስሪያ ቤት የተመደበበትን ስራ በአግባቡ ቢቀጥልም በዚሁ ምክንያት የደመወዝ ዕድገት እና ቃል የተገባለት የጣልያን የትምህርት ዕድል ቀሩበት። እሱም መተዳደሪያው የነበረውን ደመወዝ ትቶ ምንም ሳንቲም ለማይከፍለው ክለቡ ለመጫወት ሲል መስሪያ ቤቱን ለቀቀ።

ለመንግሥቱ ወርቁ ብቸኛ ሆኖ በጨዋታ ዘመኑ የዘለቀው ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን የ8 ቁጥር መለያውም ጭምር ነበር። የራሱ ሙሉ ስም እና የክለቡ መጠሪያ ፊደሎች ቁጥር ብዛት ስምንት ነው። በመጀመሪያው ዓመት ኮከብ ተብሎ የተሸለመበት የግቦች ቁጥርም እንዲሁ ስምንት ነበር። ታላቁ የእግር ኳስ ሰው የተጨዋችነት ዘመኑ አብቅቶ በአሰልጣኝነት ሙያ ላይ እያለ በአንድ ወቅት ስለዚህ የእሱ እና የስምንት ቁጥር ቁርኝት ተጠይቆ ይህን ብሎ ነበር። “ስምንት ቁጥር መለያ ታሪክ ሆኖ አሁን ድረስ የሚነገርለት እኔ የዚህችን ስምንት ቁጥር ሹራብ መልበስ ከጀመርኩ በኋላ ይመስለኛል። ለምን ግን ስምንት ቁጥር መለያን መጀመሪያ እንደመረጥኩ ማስታወስ አልችልም። በኋላ ላይ ግን መጠሪያ ስሜ ሆና ቀረች። የሚገርመው ደግሞ ከስምንት ቁጥር መለያ ጋር በጣም በመቀራረቤ የምታወቅባት ጭምር በመሆኗ በአጋጣሚ እንኳን ተሰልፌ ባልጫወት መልያዋ በእኔ የተከበረች በመሆኗ ማንም አይለብሳትም ነበር። እኔ ሌሎች ተጫዋቾች ለብሰው እንዳይጫወቱ ከልክዬ ሳይሆን የእኔ ልዩ መታወቂያ ሆና በመወሰዷ ይመስለኛል። እስካሁን ስምንት ቁጥርን በጣም ስለምወድ ብቻ ሌላው ቀርቶ በአጋጣሚ ሎቶሪ ከቆረጥኩ እንኳን መጨረሻው ስምንት ቁጥር ያለበትን ነው። የመኪና ታርጋዬ ላይም ስምንት ቁጥር አለ። በሀገርም ውስጥ ሆነ በውጪ ሀገር ለተለያዩ ስራዎች ስሄድ የምተኛበት የአልጋ ክፍል ቁጥር ስምንት ቁጥር ከሌለበት ደስ አይለኝም።” ይህም በመሆኑ በብቸኛው ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ ይህች ስምንት ቁጥር መለያ በ2003 ከሕልፈቱ በኋላ ለእርሱ ክብር ሲባል በሌላ ተጫዋች እንዳትለበስ ሆኗል።

ታሪካዊው ስምንት ቁጥር በጨዋታ ዘመኑ ተለይቶ ከሚነሳባቸው ጠንካራ ጎኖቹ መካከል አብዶኝነቱ ፣ የአልሸነፍ ባይነት መንፈሱ እና የግንባር ኳስ አጠቃቀሙ ይገኙበታል። በልጅነቱ በባዶ እግር በጉለሌ ጫካ ጉቶዎች መሀል አብዶ እየሰሩ ማለፍን እንደልምምድ የጀመረው መንግስቱ ኋላ ላይ በነበረው የእግር ኳስ ህይወቱም አጠር በሚለው ቁመቱ እና በተክለ ሰውነቱ በመታገዝ ተከላካዮችን እንደዘበት ማለፍ እና ግብ ማስቆጠር የሚከብደው አጥቂ አልነበረም። ነገር ግን እንደአሁኑ እግርኳስ በወቅቱ ለአጥቂዎች የነበረው የዳኝነት ጥበቃ እምብዛም ነበር። ተከላካዮችም ከፍ ያለ ኃይልን በመጠቀም ግብ እንዳይቆጠር የማድረግ ልማድ ነበራቸው። እንደመንግስቱ ዓይነት አብዶኛ ሲገጥማቸው ደግሞ እልህ ውስጥ ስለሚገቡ ይበልጥ ጉልበት መጠቀማቸው የማይቀር ነው። በስድብ እና በመታፋት ማስደንገጥ ፣ ከኳስ ውጪ ሜዳ ላይ መራገጥ እንዲሁም የግንባር ኳስ በሚሻሙበት ወቅት በክርን መማታት በተከላካዮች ዘንድ የሚዘወተሩ ነበሩ። ታድያ ዱላ እና ጉሽሚያን ተቋቁሞ ተከላካዮች ማለፍ እና ደጋግሞ ግብ ማግባት ለመንግስቱ ቀላል ያደረገለት እልኸኝነቱ ይመስላል። በጠለፉት እና በጎሸሙት ቁጥር ይበልጥ እልህ ውስጥ የሚገባው ተጫዋቹ እየደማ እና በህመም ውስጥ እያለ እንኳን አይምራቸውም። በተለይም የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀሙ እጅግ አስደናቂ ነበር። ቁመቱ አጠር ያለ ቢሆንም ከረጃጅሞቹ በላይ እየዘለለ በግንባሩ ግቦች ማስቆጠር ይቀናው ነበር። በዚህ ወቅት በሚፈጠሩ ጉሽሚያዎችም ከጥርስ መውለቅ በተጨማሪ በብዛት ግንባሩ ላይ የመተርተር ጉዳት እየገጠመው ለመሰፋት ይገደድ ነበር።

የአየር ላይ ኳስን በተመለከተ በወቅቱ ተዘዋውሮ በመጫወት የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በሚካሄድበት ወቅት ከሸዋ በሚሄደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ ከኤርትራ ክለቦች አስመራ ቴሌ ፣ ሀማሴንእና እምባሶይራ ዓይነት ቡድኖች ጋር ሲገናኝ በመከላከል ብቃታቸው ከሚታወቁ ተከላካዮች ጋር ይገናኝ ነበር። ያም ቢሆን ግን መንግሥቱ ግቦችን ያስቆጥር ነበር። በአስመራም ለነበረው ከፍተኛ ተወዳጅነት ይህ የአየር ላይ ብቃቱ አንዱ ምክንያት ነው። ” ቴስታ የብልጠት ጉዳይ ነው። የታይሚንግ እንጂ የቁመት አይደለም” የሚለው መንግሥቱ ከገነነ ሊብሮ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ በአንድ ወቅት ሱዳኖች እሱን ለማቆም በጣም ረጅም ተከላካይ አሰልጥነው ጠብቀውት ከእሱም በላይ ዘሎ ግብ ከማስቆጠሩ ጋር በተያያዘ ሲናገር ” …በተለይ ክሮስ ከተደረገ እነሱ ቴስታ መምታት እስከዚህም ስለሆኑ ታይሚንግ ጠብቄ በአየር ላይ ተነስቼ ቦታ አይቼ ጎል ውስጥ አስቀምጥ ነበር። ኮርና ሲመታ ‘መንግስቱን ያዙት’ ነበር የሚባለው። እኔ ደግሞ በዚህ እንደማይችሉኝ አውቃለው። ምክንያቱም እዚህ ከሀማሴን እምባሶይራ ጋር ስንጫወት ተንኮሉንም ግጭቱንም ተቋቁሚያለው። በቴስታ ዘለው መምታት እና ማስጣል አፍሪካ ውስጥ የሚያስቸግረኝ ቢኖር ከአስመራ የሚመጡ ቡድኖች ናቸው። በአየር ላይ ሆነን ኳስ የሚመቱ አስመስለው በቴስታ አናትህን ብለው ቁልቁል ይደፍቁሀል። እኔም አንዳንዴ ስንዘል በክርን ትከሻቸውን ገፋ ሳደርግ እነሱ ሲመለሱ እኔ ኳሱን መትቼ አገባለው። የተቀናጣው ጊዜ ደግሞ በአይር ላይ ዘለን በክርን አፍንጫቸውን ገጨት ሳደርጋቸው ተበሳጭተው ይመለሳሉ። ታድያ የመታሁት ልጅ ጠብቆ ዋጋዬን ይሰጠኛል። …” ብሎ ነበር።

መንግሥቱ ወርቁ በዚህ መልኩ ተከላካዮችን እያሸበረ ግቦችን እያስቆጠረ የዘመኑን የኳስ ተመልካች በማስደመም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ዘልቋል። ከ1958 እስከ 1963 ድረስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሻምፒዮና ዋንጫን ፣ በ1965 እና 1966 ደግሞ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ጋር ማሸነፍም ችሏል። በአንድ ወቅት ግን ብዙ ታሪክ ከሰራበት እና ከሚወደው ክለቡ ለቆ ለሌላ ክለብ ለመጫወት ዕድሉን አግኝቶ ነበር። ታድያ ሀገር ውስጥ አልነበረም ፤ በጣልያን ሀገር በኤሲ ሚላን እንጂ። መንግስቱ በወቅቱ በክለቡ እና በብሔራዊ ቡድን በሚያሳየው እንቅስቃሴ ዝናው ከሀገር እና ከአህጉር ማለፍ ችሎ ነበር። በጋሽ ይድነቃቸው አሰልጣኝነት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በአውሮፓ ለወዳጅነት ጨዋታ በሚያመራበት ወቅት የሜዳ ላይ ብቃቱ በፈረንሳይ ጋዜጠኞች አይን ውስጥ ገብቶ ነበር። በኳስ አቀባበሉ ፣ በአዘላለሉ ፣ ኳስ ሲመታ ቀኝ እግሩን ወደ ኋላ በሚያነሳበት መንገድ እና ከመሰንዘሩ በፊት በቋሚ እግሩ እና በኳስ መሀል በሚኖረው ርቀት እንዲሁም የዓመታት ስልቱ ጭምር የሀገሪቱ በለሙያዎች ከታዋቂው ተጫዋቻቸው ‘ሬይሞን ኮፓ’ ጋር አመሳስለውት ‘ኮፓ ኑዋር’ ወይም ጥቁሩ ኮፓ የሚል ስያሜ ሰጥተውት ነበር። በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በግሪኩ ኦሎምፒያኮስ ፣ በቱርኩ ኤስ ዮዘ እና በፈረንሳይም ጭምር ይፈለግ ነበር። ከሁሉም በላይ ግን በጣልያኑ ታልቅ ክለብ ኤሲ ሚላን በሁለት መቶ ሺህ ዶላር የዝውውር ክፍያ የመፈለጉ ነገር በጣልያን ጋዜጣ ላይ መውጣቱ ብዙ አነጋግሮ መንግሥቱም አዲስ አበባ በሚገኙ ጣልያናዊ የኳስ ወዳጆች ጭምር የእንኳን ደስ ያለህ ምኞት እና ግብዣ እንዲጎርፍለት አድርጎ ነበር። ሆኖም በወቅቱ በሀገራችን በነበረው የአማተር እግር ኳስ ስርዓት ‘ተጫዋቾች እንዲህ ከሀገር መውጣት ከጀመሩ ብሔራዊ ቡድኑ ባዶ ይሆናል’ የሚለው ፍራቻ እንዲሁም ‘በጣልያን ቡድን ሊገዛ?’ የሚለው ነገር ‘ማንን ባርያ ለማድረግ ነው ?’ በሚል ከንጉሡም ጥሩ ምላሽ ባለማግኘቱ ዕድሉ ሳይሳካ ቀረ። መንግሥቱ ወደ ኤሲ ሚላን አምርቶ የሙሉ ጊዜ ኳስ ተጫዋች ሆኖ ቢሆን ኖሮ ስኬቱ ለቀጣዮቹ ተጫዋቾች ምን ያህል ዕድሎችን ይከፍት ነበር? የሚለውን ጥያቄ ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው ብዙ የሚያስቆጩ ሀሳቦችን መፍጠሩ አይቀርም።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ