የሴቶች ገፅ | “ሁሉም ነገር እንደሚያልፍ ስለማውቅ እየሰማሁ እንዳልሰማሁ ችዬ አሳልፋለሁ” የሀዋሳ ከተማዋ መሳይ ተመስገን

በሀገራችን በርካታ ሴት ተጫዋቾች ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈው ያለሙበት ቦታ ላይ ሲደርሱ ለመመልከት ችለናል። እንደ ሀዋሳ ከተማዋ አጥቂ መሳይ ተመስገን ግን በጫናዎች ውስጥ ያለፈ አለ ብሎ መገመት ያስቸግራል። በዛሬው የሴቶች አምድ መሰናዷችንም ዘንድሮ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ስትመራ የነበረችውን ፈጣኗን አጥቂ እንግዳ አድርገናታል፡፡

ኳስን የጀመረችው ተወልዳ ባደገችበት ሆሳዕና ከተማ አራዳ ተብሎ በሚጠራው ሠፈር ውስጥ ነው፡፡ የልጅነት ጊዜዋን ኳስን በመጫወት ያሳለፈችሁ በፕሮጀክት በመታቀፍ ሳይሆን ተማሪ በነበረችበት ወቅት ከወንድ የትምህርት ቤት ጓደኞቿ ጋር ኳስ በማንከባለል ነበር። የእግርኳስ ጥልቅ ፍቅር እያደረባት መጥቶም አባቷ ከትምህርት ቤት ስትመለስ ትምህርቷ ላይ አተኩራ እንድታጠና ቢገፋፏትም እሷ ግን የአባቷን ምክር ከመስማት ይልቅ በትምህርት ቤት የጀመረችውን ጨዋታ በሠፈር ውስጥም መቀጠሉን መርጣለች። ፈጣኗ አጥቂ መሳይ ተመስገን አቅሟ እያደገና እየጎለበተ ሲመጣ ግን “ለምን ለቀበሌ አትጫወቺም ? ” በሚል በአንድ የቅርብ ጓደኛዋ ግፊት ያለምንም ማንገራገር ለአካባቢዋ መጫወት ጀመረች፡፡

የቤተሰብ ጫና በተለይም የአባቷ የአትጫወቺ ተፅዕኖ ቢያድርባትም እየተደበቀች በመጫወት ካለመችሁ ግብ ለመድረስ ጥረት ከማድረግ ያስተጓጎላት ግን አልነበረም። ከቀበሌ የጀመረው የመጫወት ፍላጎቷ እያደገ መጥቶ ለወረዳ እና ለሀድያ ዞን አልፎም ደግሞ ክልሉን እስከ መወከል ጭምር ደርሳም ነበር፡፡ ለኳስ የተለየ ፍላጎት እንዳላት የምትገልፀው መሳይ 2006 ላይ ሀድያ ዞንን ወክላ በመጫወት ላይ እያለች ባሳይችው መልካም እንቅስቃሴ ለደቡብ ክልል ተመርጣ መጫወት ችላለች፡፡ በወቅቱ በነበራት ምርጥ አቋም የተነሳ በርካታ ክለቦች ፍላጎታቸውን ቢያሳድሩባትም እሷ ግን ስለ ክለብ ዕውቀት ስላልነበራት ለሁለት ክለቦች ልትፈርም ችላለች። ከግንዛቤ ዕጥረት የተነሳ 2007 ላይ ለሀዋሳ ከተማ እና ለሲዳማ ቡና በመፈረሟም በፌዴሬሽኑ የሁለት ዓመት ዕገዳ ሊጣልባት ቻለ፡፡ “በመጀመሪያ ለትምህርት ቤት ውድድር ተመርጪ ነበር። አዲስ አበባ ላይ በነበረው ውድድር ግን በመታወቂያ ችግር ምክንያት ወደ ቤተሰብ ተመለስኩኝ። ከዛን ሀድያ ዞንን ወክዬ አርባምንጭ ላይ በነበረው ውድድር ተካፍያለው። ያ ለኔ እጅግ ከባድ ነበር። ጫናዎች ነበሩበት ግን ጥሩ ጊዜ ነበረኝ በሂደት ደስተኛ ሆንኩኝ።” በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ሀድያ ዞንን ወክላ ስለተጫወተችበት 2006 የመላው ደቡብ ጨዋታ የነበራትን ስሜት ትገልፃለች፡፡

ለሁለት ክለቦች በመፈረሟ እስከ 2008 ድረስ በፌዴሬሽኑ የሁለት ዓመት ቅጣት ተላልፎባት ከእግርኳሱ ለመራቅ ተገዳ የነበረችው መሳይ ያን ጊዜ አሳልፋ ዛሬ ወደ እግርኳሱ ዳግም ብቅ ብላለች። ከቅጣቱ ባሻገር ብዙም የሴትነት ባህሪ የላትም እየተባለች በተመልካቹ እና በአሰልጣኞች ወቀሳ ሲቀርብባት የምትስተዋለው አጥቂ ስላሰለፈቻቸው አስከፊ የዕግድ እና የፆታ ጥያቄዎች ዙሪያ እንዲህ ትላለች ” ለኔ የተማርኩባቸው ጊዜያቶች ነበሩ። የተቀጣሁባቸው ወቅቶች በራሴ በደንብ አየሰራሁ ጠንክሬ የተሻለ ቦታ መድረስ ስለምፈልግ ወደ ኳሱ መጥቻለሁ። 2010 እና 11 እስከ ግማሽ ዓመት ድረስ በአንዳንድ ጉዳዮች አቋርጬ ነበር። ግን አባቴ ብዬ በምጠራው አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ አማካኝነት በድጋሚ ወደ እግርኳሱ ተመልሻለው። ስለ እሱ የማወራበት ቃል የለኝም፤ እንደ አባት ነው የማየው። በእሱ ጥረት በህክምና ተቋም ተመርምሬ እና ፌድሬሽኑ ፈቅዶልኝ ወደምወደው እግርኳስ ተመልሻለው።”

ከ2011 ግማሽ ዓመት ጀምሮ ሀዋሳ ከተማን ከተቀላቀለች በኋላ ለቡድኑ ስኬታማ የማጥቃት ኃይል የሆነችው ተጫዋቿ በገባችበት ዓመት የጥሎ ማለፍ ዋንጫን አንስታ ዓመቱን በድል ያጠናቀቀች ሲሆን በዘንድሮው የ2012 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ከታዩ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዷ ከመሆን ባለፈ ፕሪምየር ሊጉ እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ስትፎካከርም ጭምር ነበር። ምንም እንኳን ይህ ዓመት ለሷ የተሳካ ቢመስልም የሚሰነዘሩባት የፆታ ጥያቄዎች ከብደው የመጡበትም ነበር። መሳይ ስለ ጉዳዩ እንዲህ ትላለች “ፈጣሪ ሁላችንንም በዚህ ምድር ሲፈጥረን በምክንያት ነው። ብዙ ጊዜ ኳስን ከጀመርኩኝ ጊዜ አንስቶ ይሄ ጥያቄ ይነሳብኝ ነበር ፤ ቻሌንጆቹ ከባድ ነበሩ። ብዙ ስቃዮችንም አይቻለሁ። እስከ አሁንም አሉ። ልረሳቸው የማልችላቸው ብዙ ነገሮች ተወርተውብኛል። ነገር ግን እነኚህን ወሬዎች፤ የሰውንም ድምፅ ሰምቼ ቢሆን ኖሮ ዛሬ እዚህ የደረስኩበት ቦታ አልገኝም ነበር። ብዙ ነገር ይባላል ብዙ ነገር እሰማለሁ፤ ያው ነገሮች ሁሉ ያልፋሉ። በፈጣሪ ስለማምን ሁሌም ደስተኛ ነኝ። እነሱን ተቋቁሜ በመጫወት የሰውን አፍ እያስያዝኩ ነው። እነኚህ ደግሞ ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ ይነሱብኝ ስለነበረ ራሴን አሳምኜ ነው የመጣሁት። ለምን እንደሚደርስብኝም ቀድሜ አውቀዋለሁ። ሰው ባየኝ ቁጥር ብዙ ይባላል። ከመጀመሪያ ጀምሮ ስለመጣብኝ አሁን ላይ ራሴን አሳምኜዋለው። ‘ፈጣሪ ሆይ ትዕግስቱን መቻሉን ስጠኝ’ ብዬ ሁሌም እጠይቀዋለው። ሁሉም ነገር እንደሚያልፍ ስለማውቅ እየሰማሁ እንዳልሰማሁ ችዬ አሳልፋለሁ።”

በሊጉ በሀዋሳ ከተማ መለያ በግሏ የተሳካ ጊዜ ስታሳልፍ የነበረችው መሳይ ስለነበራት አቋም ስትናገር “አዎ እንደነገርኩህ ብዙ ቻሌንጆችን አሳልፌያለሁ። እኔም ከምን ዓይነት ቤተሰብ እንደተገኘሁ አውቃለሁ። ስራዬ ነው ብዬ ስለማምን በደንብ እንድበቃ አድርጎኛል። ሁሌም አሰልጣኝ ዮሴፍ ይነግረኛል ፤ ከእኔ በላይ እሱ ዋጋ ከፍሎልኛል። እሱን ከዚህም በበለጠ ማስደሰት እፈልጋለሁ። እሱም በእኔም ሆነ በሌላው እንዲጠራ እፈልጋለሁ። እሱ የሚያሰራኝን ስራ ከልቤ ነው የምሰራው። የተለየው እንድሆን አድርጎኛል። ሜዳ ላይም ማድረግ ያለብኝን አደርጋለሁ። ከዚህ በኃላ መክፈል ያለብኝን ዋጋ እከፍላለሁ። የምፈልግበት ቦታ እየደረስኩ ነው ፤ ወደፊትም የተሻለ ቦታ አቅሜን አሳይቼ መጫወት እፈልጋለሁ። ለዚህም ብዙ የረዳኝን ከፈጣሪ በታች አሰልጣኝ ዮሴፍን አመሰግናለሁ። ደመወዝ በማይከፈለኝ ጊዜ እየረዳኝ እዚህ አድርሶኛል። ውለታውን በቻልኩት መጠን ለመክፈል እሞክራለሁ። ከዛ ውጪ ለቀበሌ ስጫወት ለሚያበረታታኝ አሰልጣኝ ታምራት ከልቤ ማመስገን እፈልጋለሁ።” ያለች ሲሆን በመጨረሻም የሀገሯን መለያ ለብሳ የመጫወት ጉጉቷንም ገልፃለች።

“ሀገሬን ወክዬ የመጫወት ፍላጎቱ በደንብ አለኝ። አሰልጣኝ ብርሀኑ በቅርቡ ጠርቶኝ ነበር። በልምምድ ላይ በገጠመኝ ጉዳት ግን አልሄድኩም። ምኞቴ የሀገሬን መለያ መልበስ ነው። ከዚህም ፍላጎቴ ውጪ የተሻለ ቦታ መድረስን እመኛለሁ። ያሰብኩት ቦታ ለመድረስም ጠንክሬ እየሰራሁኝ እገኛለሁ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ