ባህር ዳር ከተማ የ2 ተጨማሪ ተጫዋቾቹን ውል አድሷል

ከትናንት በስትያ የሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል ያደሰው ባህር ዳር ከተማ ትናንት ከሰዓት ደግሞ የ2 ነባር ተጫዋቾችን ውል በተጨማሪነት አድሷል።

የአሰልጣኛቸውን ውል በማደስ ወደ ሥራ የገቡት የጣናው ሞገዶቹ በሳምንቱ መጨረሻ የፍቅረሚካኤል አለሙን እና ዜናው ፈረደን ውል ለ2 ዓመታት ማደሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ትላንት ደግሞ የቡድኑ ቀዳሚ አምበል ደረጄ መንግስቱ እና ተስፈኛው የመስመር ተጫዋች ኃይለየሱስ ይታየው በክለቡ ጽህፈት ቤት ተገኝተው ፊርማቸውን ለ2 ዓመታት አኑረዋል።

በፋሲል ከነማ፣ ሙገር ሲሚንቶ፣ ሀረር ቢራ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ዳሽን ቢራ የተጫዋችነት ጊዜውን አሳልፎ ከ2 ዓመታት በፊት የጣናው ሞገዶቹን የተቀላቀለው ደረጄ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማሳደጉ ይታወሳል።

ትናንት ከደረጄ ጋር ውሉን ያደሰው ሌላኛው ተጫዋች ተስፈኛው የመስመር ተጫዋች ኃይለየሱስ ይታየው ነው። በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ አማካኝነት በዘንድሮ የውድድር ዓመት ከተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ያደገው ኃይለየሱስ የፈረመው የ1 ዓመት ቆይታ መጠናቀቁን ተከትሎ ከክለቡ አመራሮች ጋር ድርድር ሲያደር ቆይቷል። ትላንት ከሰዓትም ሁለቱ አካላት ከስምምነት ደርሰው ተጫዋቹ ፊርማውን ለ2 ዓመታት አኑሯል።

ዛሬን ጨምሮ በተከታታይ በሚኖሩ ቀጠሮዎች ተጨዋቾችን ለማግባባት እየተጉ የሚገኙት ባህር ዳሮች የአሰልጣኙን ይሁኝታ ያገኙ የነባር ተጫዋቾችን ውል ካደሱ በኋላ ፊታቸውን ወደ አዳዲስ ተጫዋቾች እንደሚያዞሩ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ