ባህር ዳር ከተማ 3ኛ ተጫዋቹን ወደ ቡድን ለመቀላቀል ተስማምቷል

ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከቀናት በፊት ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል ከስምምነት የደረሰው ባህር ዳር ከተማ ከደቂቃዎች በፊት ተጨማሪ ተጫዋች አስፈርሟል።

በዝውውር ገበያው ላይ በከፍተኛ ንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች የመናፍ ዐወልን እና የበረከት ጥጋቡን ፊርማ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ከደቂቃዎች በፊት ደግሞ አህመድ ረሺድን ወደ ክለባቸው ለመቀላቀል ተስማምተዋል። ከደደቢት የታዳጊ ቡድን የተገኘው አህመድ ረሺድ ወደ ኢትዮጵያ ቡና በማቅናት ከ2007 ጅምሮ በዋናው ቡድን በመጫወት ድንቅ ጊዜን አሳልፏል። ከ2010 ጀምሮ ደግሞ ወደ ምስራቂቱ የሀገሪቱ ክፍል (ድሬዳዋ) አምርቶ የተጫወተው ተጫዋቹ ዘንድሮ ዳግም ወደ ቡናማዎች ቤት በመመለስ መጫወቱ ይታወሳል።

በሁለቱም መስመሮች በመሰለፍ መጫወት የሚችለው አህመድ ከቡናዎች ጋር ውሉን ለማራዘም ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም በዛሬው እለት ግን ለጣና ሞገዶቹ ለቀጣይ 2 ዓመታት ለመጫወት የቅድመ ስምምነት ፊርማውን ፈፅሟል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ