ምዓም አናብስት ሁለት ተጫዋቾች ለማስፈረም ተቃርበዋል

የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን ውል በማራዘም እንቅስቃሴያቸው የጀመሩት መቐለዎች ቀደም ብለው የአምስት ተጫዋቾች ውል ማራዘማቸው ይታወቃል። አሁን ደግሞ ተስፈኛው ነፃነት ገብረመድኅን እና ምንይሉ ወንድሙን ለማስፈረም በቃል ደረጃ ተስማምተዋል።

በመከላከያ ጥሩ ዓመታት ያሳለፈው እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማልያ ለብሶ የተጫወተው አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ ከሳምንት በፊት በቃል ደረጃ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ቢስማማም ከመቐለ የተሻለ ውል ስለቀረበለት ለምዓም አናብስት ፌርማውን ለማኖር ከጫፍ ደርሷል። በቀጣይ ቀናትም በይፋ ቅድመ ፊርማውን በማስቀመጥ ከቀድሞ አሰልጣኙ ጋር እንደሚገናኝ ለማወቅ ተችሏል።

ሁለተኛው ለክለቡ ለመፈረም የተስማማው ወጣቱ ነፃነት ገብረመድኅን ነው። በተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ የሚሰለፈው እና ባለፈው ዓመት ከስሑል ሽረ ጋር አስደናቂ ዓመት ያሳለፈው ይህ ተጫዋች ከአሳዳጊ ክለቡ ስሑል ሽረ ተለያይቶ ወደ መቐለ ለማምራት በቃል ደረጃ ተስማምቷል። በቀጣይ ቀናትም በይፋ ቅድመ ፊርማውን ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል። የተጫዋቹ ወደ ክለቡ መምጣትም ባለፈው ዓመት የነበረው የቡድኑ የተከላካይ አማካይ ክፍተት መልስ ያገኛል ተብሎ ይገመታል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ