የብሔራዊ ቡድኑ ጉዳይ ያከተመለት ይመስላል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ የማጣርያ በወሩ መጨረሻ እንዲጫወት ካፍ ቢያሳውቅም በፌዴሬሽኑ በኩል እስካሁን ምላሽ አለመሰጠቱ አስገራሚ ሆኗል።

ጥር 2021 በኮስታሪካ እና ፓናማ አዘጋጅነት እንደሚካሄድ የተገመተው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫን አንደኛ ዙር ማጣርያ ቡሩንዲን አሸንፎ በቀጣይ ዙር አልፎ ከዚምባብዌ ጋር ከነሐሴ 28-30 የመጀመርያው ጨዋታ ፤ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ከጳጉሜ 5-መስከረም 2 እንደደረግ ካፍ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ካሳወቀ ከአንድ ወር በላይ ሆኖታል።

ከዚህ ቀደም ፌዴሬሽኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እያሰበ ነው በማለት ላቀረብነው ጥያቄ ባገኘነው ምላሽ ውድድሩን ለማድረግ የሚያስችል ፍቃድ ለማግኘት ለመንግስት እና የሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን የዛሬ አስራ አምስት ቀን መዘገባችን ይታወቃል።

ነገር ግን በመንግስት በኩል ምላሽ ይሰጥ አይሰጥ እስካሁን ፌዴሬሽኑ ምንም ያለው ነገር ባለመኖሩ እና ጨዋታው ሊደረግ የቀረው 22 ቀን ብቻ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንዲሁም እስካሁን ብሔራዊ ቡድኑ ምንም ዓይነት ዝግጅት ያልጀመረ በመሆኑ ጨዋታውን የማድረጉ ነገር ያከተመለት መስሏል፤ ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ቀናት የሚለው የተለየ ነገር ከሌለ በቀር።

በዚህ ጉዳይ ላይ ካፍ ምን እያሰበ እንዳለ እና ምን ዓይነት ውሳኔ ያስተላልፋል የሚለውም ጉዳይ ተጠባቂ ነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ