ስለ ቴዎድሮስ በቀለ (ቦካንዴ) ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

በሁለቱ ታላላቅ ክለቦች እየተወደደ መጫወት ችሏል። ሜዳ ውስጥ የቡድን እንቅስቃሴን በመቆጣጠር ተረገድ የተዋጣለት እንደነበር የሚነገርለት የዘጠናዎቹ ድንቅ አማካይ ቴዎድሮስ በቀለ (ቦካንዴ) ማነው?

የዛሬን አያርገውና ብዙ ትውልድ በዚህ ሜዳ ጠዋት መጥተው ፀሀይ እስክትጠልቅ ድረስ ሲጫወቱ ውለው ማታ ወደ ቤታቸው ይሄዱበታል። በዚህ ሒደት ውስጥ ደግሞ ለቁጥር የሚታክት ስመጥር የሆኑ ተጫዋቾች ፈልቀውበታል። ይህ አሁን ለታሪክ ብቻ ቀርቶ ላይመለስ ፈርሶ እንደዘበት የቀረው ሜዳ አዲስ አበባ ስታዲየም አጠገብ የሚገኘው ትንሿ ሜዳ (“ሲ”ሜዳ) ይባላል። በዚህ ታሪካዊ ሜዳ ከተገኙ ድንቅ ባለ ክህሎት አማካይ ተጫዋቾች መካከል ደግሞ ቴዎድሮስ በቀለ አንዱ ነው።

ፍልውሃ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ቴዎድሮስ የአባቱ ጋሽ በቀለ የቅርብ ጓደኛ የሆኑት ጋሽ ግርማ ከበደ ሁሌም በልጅነቱ ወደ ተለያዩ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች ይዘውት ይሄዱ ነበር። በአብዛኛው ደግሞ ወደ እግርኳስ ሜዳ ይዘውት መሄዳቸው የኳስ ፍቅር በውስጡ እያደረ ተፅእኖ እያደርገበት መጥቷል። ከቤቱ አስር ደቂቃ የእግር መንገድ እየተጓዘ ሁሌም እግርኳስን ለመጫወት ወደ “ሲ” ሜዳ ይሄድ ነበር። አሁን ሸራተን ሆቴል በተገነባበት አካባቢ ይገኝ ለነበረው ሎተሪ ለሚባል ክለብ እየተጫወተ እስከ መንግሥት ለውጥ መዳረሻ ድረስም ቆይቷል።

ቴዎድሮስ በአጋጠሚ ቡና የታዳጊ ቡድኑ ምልመላ እንደሚያደርግ ከሠፈር ጓደኞቹ ይሰማና ከእነርሱ ጋር በመሆን “ሲ” ሜዳ ይሄዳል። በወቅቱ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ታዳጊዎቹን ይመለምል የነበረው አንጋፋው የስፖርት ሰው ጋሽ ሥዩም አባተ እና በድሉ ኃይሌ ነበሩ። በጊዜው እዛው ሜዳ ስም እየመዘገቡ ሲሞክሩ አይቶ ቦካንዴ ስሙን አስመዝግቦ ለሙከራ ወደ ሜዳ ይገባል። በሚገርም ሁኔታ አንድ ኳስ ብቻ ሲነካ አይቶት ጋሽ ሥዩም ለኢትዮጵያ ቡና “ሲ ” ቡድን በ1983 እንዲጫወት አድርጎታል።

በነበረው አቅም ተደምመው እና ወደፊት ተስፋ እንደሚጣልበት ከግምት አስገብተው ገና በታዳጊ እድሜው ነበር የአዲስ አበባዎቹ ባላንጣ ክለቦች እርሱን የመፈለግ እና የመወሳሰድ ፉክክር ውስጥ የገቡት። በቡና ሲ ቡድን ብዙም ሳይቆይ በ1984 እና 85 ለሁለት ዓመት ሊጫወት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ “ቢ” ቡድን አምርቶ መጫወትም ችሏል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዋናው ቡድን የማደግ እድል አለማግኘቱን የተረዱት ቡናዎች ደግሞ በአፀፋው ይህን ታዳጊ አማልለው እንደገና በ1986 ወደ ክለባቸው መልሰው ማጫወት ጀምረዋል። ለስድስት ዓመት በኢትዮጵያ ቡና ቆይታው የ1989 የኢትዮጵያ ቻምፒዮን ሲሆን የ1990ው ጥሎ ማለፍ አግኝቷል። ቡና የግብፁ ኃያል ክለብ አል አልሀሊን በደርሶ መልስ ውጤት ከውድድሩ ውጭ ሲያደርግም ግብፅ ላይ አሰግድ ተስፋዬ ላስቆጠራት አስደናቂ የመቀስ ምት ጎል በጠባብ ሜዳ በተከላካዮች መሐል አሳልፎ በግሩም ሁኔታ ያቀበለው ቦካንዴ ነበር።

በኢትዮጵያ ቡና ከሚወደዱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው የምንግዜው አስራ ሁለት ቁጥር ለባሹ አሸናፊ በጋሻው ቦካንዴን ሲገልፀው ” ቴዎድሮስን ከቀድሞ የአርሰናል ተጫዋች ፈረንሳዊው ፓትሪክ ቪዬራ ጋር ነው የማመሳስለው። ቪየራ ለክለቡ ለአርሰናል ምን አይነት አስፈላጊ ተጫዋች እንደነበረ ይታወቃል። ሆኖም በብዙዎች ዘንድ ብዙም ዕይታ የለውም። ቴዲ ማለት ለክለቡ እንዲህ ያለ ተጫዋች ነበር። ለተመልካች የማይታይ ግን በጣም ወሳኝ እና ቁልፍ የቡድኑ ተጫዋች ነበር። በዚህ ላይ እጅግ የተለየ ፀባይ ነው ያለው። በጣም ትሁት እና ሰው አክባሪ ነው። የእኛ ሀገር ሆነና አልተጠቀምንበትም እንጂ ልምዱን እንዲያካፍል አላደረግነውም። ቦካንዴ ለአሁን ለሚገኙ ተጫዋቾች ብዙ ነገር ማስተማር የሚችል ልምድ ያለው ተጫዋች ነው። በሁለቱም ትልልቅ ክለቦች ተጫውቶ ማለፉ የነበረውን አቅም ያሳያል።” ሲል ገልፆታል።

በ1991 የወቅቱ ሪከርድ በሆነ የፊርማ ገንዘብ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ዳግመኛ በመውሰድ የግላቸው አድርገውታል። የመጀመርያውን የውድድር ዓመት የተሳካ ቆይታ ባያደርግም በኃላ ከቡድኑ ጋር እየተላመደ መጥቶ እስከ 1995 አጋማሽ ድረስ ለአራት ዓመት ከመንፈቅ አገልግሏል። ከፈረሰኞቹም ጋር በነበረው ቆይታም የሊጉን ዋንጫ ሁለት ጊዜም ማንሳት ችሏል።

ሌላኛው የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ጳውሎስ ጌታቸው (ማንጎ) ቦካንዴን ሲገልፀው ” ኢትዮጵያዊ ተጫዋች የማይመሰል በመልኩ ከምዕራብ አፍሪካ ተጫዋች የሚመስል ጥሩ የእግርኳስ ችሎታ የነበረው በጣም ጉልበተኛ፣ ከጥቂዎች ጋር ተደርቦ ጎል የሚያስቆጥር፣ አጠገቡ ካሉት አማካዮች ጋር በደንብ ተናቦ የሚጫወት በጣም ትልቅ ተጫዋች ነበር።” ሲል ያነሳዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ብሔራዊ ቡድን ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በመጫወት ሀገሩን ያገለገለው ቴዎድሮስ ከሀገሩ ከወጣ አስራ ስድስት ዓመት የሆነው ሲሆን አሁን ከሚኖርበት ለንደን ከተማ አግኝተነው ተከታዩን ሀሳብ አካፍሎናል።

“ከሀገሬ ከወጣው ወደ አስራ ስድስት ዓመት ሆኖኛል። እዚህ ለንደን የራሳችን ቡድን መስርተን እንቅስቃሴያችንን አላቆምንም፤ እየተጫወትን ነው። እኛ አካባቢ ብዙ ተጫዋቾች አሉ ከኔ በኃላ የመጡ። ቆጬ፣ ኩኩሻ፣ ናይጄሪያ ብቻ ብዙ ልጆች አሉ። በየዓመቱ የኢትዮጵያውያን የአውሮፓ ውድድር ላይ እንካፈላለን። ከእንቅስቃሴ አልወጣንም። በተለይ ፀሀይ ሲሆን ረቡዕ እና እሁድ ክረምት ከሆነ በሳምንት አንዴ እንጫወታለን እስካሁን ድረስ ይህን ቃለ መጠይቅ እስካደረከኝ ድረስ ኳስ እየተጫወትን እንገኛልን።

” በሀገሩቱ ውስጥ አሉ ለሚባሉ ትልልቅ ቡድኖች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና መጫወት ችያለው። ይሄ ለኔ ትልቅ ስኬት አድርጌ ነው የምወስደው። በብሔራዊ ቡድን ከወጣት ቡድን እስከ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ድረስ ተጫውቻለው። ከልጅነት እድሜ ጀምሮ በእግርኳስ ሙያ ውስጥ አልፌ ትልቅ ተጫዋች መሆን አለብኝ ብዬ ብዬ አስብ ነበር። የማስበውን ነገር በማድረጌ በጣም ደስተኛ ነኝ። በምትፈልገው ሙያው ውስጥ ማለፍ በራሱ ለኔ ስኬት ነው።

” ዘጠኝ ዓመት ያህል በእግርኳሱ ተጫውቼ አልፌያለው። በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። ማድረግ የሚገባኝን ነገር ሁሉ አድርጌ ነው እግርኳስ ተጫዋችነትን ያቆምኩት። ሳላደርገው ቀርቻለው ብዬ የምቆጨው ነገር የለም። ነገር ግን አንድ ነገር አላደረኩም የምለው ጉዳይ አለ። ካምፕ (የተጫዋቾች ማደርያ) ቦታን በተመለከተ ነው። እርሱም ምድነው ካምፕ ቁጭ ብለን ያጠፋነው ጊዜ ትንሽ አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ይቆጨኛል። እንዳው አሁን ላይ ቢሆን አላደርገውም ብዬ እቆጫለው። ለነገሩ ጊዮርጊስ እያለው የምጫወተው እየተመላለስኩ ስለነበረ በዚህ አጋጣሚ እማስበውን አድርጌአለው ተንቀሳቅሻለው። ቡና እያለው ግን አምስት ዓመት ካምፕ ውስጥ ከእግርኳስ ውጭ ሌላ ሥራ ሳልሰራ ቁጭ ብዬ ያሳለፍኩት፣ የባከነው ጊዜ በጣም ይቆጨኛል። አሁን የተረዳሁት ነገር ቢኖር ለተጫዋች በምንም መንገድ ካምፕ እንደማያስፈልግ ነው። ከኳስ ውጭ የሚንቀሳቀሱበት ሌላ ሙያ ያስፈልጋቸዋል የሚል ሀሳብ አለኝ። አምስት ዓመት ከካምፕ ውጭ በሌላ ዘርፍ ሳልሰማራ ቁጭ ብዬ ያሳለፍኩት ጊዜ ይቆጨኛል።

” የ1989 እና የ90ው የቡና ስብስብ በጣም የሚገርም ቡድን ነበር። ለኔ በእግርኳስ ህይወቴ ካየሁት ስብስብ ከነ ሙሉጌታ ወልደየስ፣ ሚሊዮን በጋሻው ቀጥሎ እንዲህ ያለ የተደራጀ፣ የተሟላ ስብስብ አይቼ አላቅም። በጠንካራ ቡድን ነበር። የአል አህሊ ጨዋታ ኢንተርናሽናል መድረክ ስለሆነ ጎልቶ ይወጣ እንጂ በሌሎች ጨዋታዎችም ላይ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እናደርግ ነበር። አሰግድ አል አህሊ ላይ ላስቆጠረው ጎል ያቀበልኩት ኳስ እጅግ ወሳኝ ነበረች። ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ አንድ ጎል ያስፈልገን ነበር። ለአሰግድ አመቻችቼ አቀብየው አል አህሊን ጥለን ያለፍንበትን ጎል ሲያስቆጥር የነበረኝ ደስታ መጠን የለውም። እኔም ስላቀበልኩት ደስታዬን የበለጠ አድርጎታል። ለኔም በእግርኳስ ዘመኔ መቼም የማረሳው ውጤት ነው። በነገራችን ላይ ያን የመሰለ ስብስብ የኢትዮጵያ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አለማንሳቱ እስካሁን ድረስ ይገርመኛል።

“ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የማይረሳ ጣፋጭ ቆይታ ካደረኩኝ በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስገባ በወቅቱ ሪከርድ በሆነ የፊርማ ገንዘብ አስራ አምስት ሺህ ብር ተከፍሎኝ ነበር። የአሁኑ መቶ ሺህ ብር በለው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከገባው በኋላ ቡና የነበረኝ ጥሩ አቅም ለመድገም በተወሰነ መልኩ ተቸግሬ ነበር። ምክንያቱም የቅዱስ ጊዮርጊስ የወቅቱ አሰልጣኝ የነበረው አሥራት ኃይሌ ነው። የአሥራት ስልጠና የሚያተኩረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ ስለነበረ ይህ ደግሞ ለኔ ከብዶኝ ነበር። ለምን ቡና እያለው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ብዙ አንሰራም ከኳስ ጋር የተያያዘ ልምምድ ነው በብዛት የምንሰራው። በዚህ የተነሳ ልምምዱ በጣም ከብዶኝ መቋቋም አቅቶኝ ነበር። በዚህ የተነሳ አንድ አስር ጨዋታ ላይ ጥሩ አልነበርኩም። በኃላ ግን ልምምዱን እየለመድኩት ስመጣ እንዲሁም በወቅቱ ከነበሩ ተጫዋቾች ሙሉዓለም ረጋሳ፣ ሰይፈ ውብሸት፣ ፋሲል ተካልኝ እና አንተነህ አላምረው ጋር ተነጋግረን ጥሩ ኳስ የሚጫወት ቡድን በማድረግ በውጤት የታጀበ ጊዜ አሳልፌለው።

“ለምን የ1995 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበረህን ቆይታ ሳትጨርስ አጋማሽ ላይ ሄድክ ላልከው፤ ያው ከቤተሰቤ ጋር ተማክሬ አስቤበት ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፍኩ ነበር። ውድድሩን ብጨርስ የሊጉን ዋንጫ የማንሳት ዕድሉ ነበረኝ። በወቅቱ ከሀገሬ ስለመውጣት እንጂ ስለ ዋንጫ አላሰብኩም ነበር። ምክንያቱም ከሀገሬ መውጣትን ብቻ ነው በጊዜው አስብ የነበረው። ያም ሆነ ይህ የውድድሩን ግማሽ ተጫውቻለው። ለንደንም ሆኜ እነርሱ ዋንጫ ሲያነሱ ከነርሱ ጋተር ግንኙነቱ ነበረኝ። እኔም ዋንጫ እንዳነሳው ነው የምቆጥረው ያን ያህል ብዙ አያሳስበኝም ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫ በማንሳቱ በጣም ተደስቻለው። በሥጋ ነው እንጂ አብሬ ያልነበርኩት በሀሳብ፣ በመንፈስ ከእነርሱ ጋራ ያልነበርኩት። በስልክ እናወራ ነበር በሁሉ ነገር እንገናኝ ነበር። እንዲሁም ከቦርድ አመራሮቹ ጋር ጭምር እንገናኝ ስለነበረ በዚህ መልኩ ነው የማየው።

” በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ጥሩ ቆይታ አድርጌያለው። ግብፅ ላይ አምስት ለባዶ ተሸንፈን እዚህ አምስት አግብተን በመለያ ምት የወደቅንበት ቡድን ውስጥ ነበርኩ። በተለያዩ ጊዜአት ተመርጬ ተጫውቻለው። እንደው በዚህ በአንድ ወቅት ያጋጠመኝን አንድ ነገር ላጫውትህ። አሁን ስሙን የማልጠቅስልህ ተጫዋች ሁልጊዜ ልምምድ ከሰራን በኃላ ክፍል ውስጥ ገብቶ በሶ መጠጣት ነው የምፈልገው እያለ በወረቀት ጠቅልሎ (ሸፍኖ) ከኪሱ እያወጣ ይጠጣ ነበር። ያው በሶ ነው የሚጠጣው ብለን ለአንድ ለሁለት ወር እኛ አናውቅም በሶ ነው እያልን ዝም ብለን እናልፈው ነበር። አንድ ቀን ለምድነው እርሱ ብቻ በሶ የሚጠጣው እኛም መጠጣት አለብን ብለን በወረቀት የተጠቀለለውን ከፍተን ስናየው ድራፍት ቢራ ሆኖ አገኘነው። በአጋጣሚ ሁሌ ከአዕምሮዬ የማይወጣ የሚያስቀኝ ነገር ነው።

” ቦካንዴ የሚለውን ቅፅል ስም ያወጣልኝ ዻውሎስ ጌታቸው (ማንጎ) ነው። የካሜሩን አማካይ ተጫዋች ነው። ሙሉ ስሙ ኢማኑኤል ቦካንዴ ይባላል። ስሙን ያወጣበት ዋና ምክንያት በመልክ በመመሳሰል ይመስለኛል። ይህን ስም ያወጣልኝ እንጂ በእንቅስቃሴ ተመሳስለን አይደለም። ይኸው ከዋና ስሜ በላይ ፀድቆ መጠርያዬ ሆኗል።

“ኢትዮጵያ ቡና እያለው አንድ ገጠመኝ ልንገርህ፤ 1990 ነው ነፍሱን ይማረውና ጋሽ ሥዩም አባተ አስራ አንድ፣ አስራ አንድ አድርጎ ለሁለት ቡድን ከፍሎ የልምምድ ጨዋታ ያሰራናል። እኔ ደግሞ በጣም ኳስ እየያዝኩ አስቸግረዋለው። ቶሎ አላቀብልም ተጫዋች እያለፍኩ እግሬ ላይ ኳሱን አዘገይበት ነበር። ጋሽ ሥዩም ኳስ ልቀቅ፣ ልቀቅ እያለ ይጮሀል። እርሱ የሚፈልገው ቶሎ ቶሎ ለቀቅ ለቀቅ አድርጌለት እንድጫወት ነበር። እኔ ደግሞ አልለቅም። በጣም ሲቸግረው ሌላ ኳስ ከቅርጫት ውስጥ አምጥቶ ያዘው ብሎ አሳቀፈኝ። እኔ ያንን ኳስ ታቅፌ ሌላ ኳስ ፍለጋ እጫወታለው። ተጫዋቾች በጣም ይስቃሉ። ሲስቁብኝ ሳይ በጣም ተበሳጨቸው። ካለፈ በኃላ ሳስበው በጣም ያስቀኛል። ጋሽ ሥዩም በጣም ኳስ ስለምትወድ እንዳትለቀው ብሎ ኳስ ያሳቀፈኝ አጋጣሚ ሁሌም አስታውሰዋለው።

“አሰልጣኝ የመሆን ሀሳቡ የለኝም። አንድ የራሴ የምሰራው ሥራ ስላለኝ አሰልጣኝ መሆንን ለጊዜው አላስበውም። ግን የሀገሬን እግርኳስ በጣም ነው የምከታተለው። ከእኛ ጊዜ ጋር ያለው ልዩነት የሙያው ፍቅር ትንሽ ላላ ብሏል። በኛ ጊዜ የሙያው ፍቅር፣ ትግሉ ነበር። አሁን ይሄን አልመለከትም። ሌላው የሚጫወቱበት ሜዳ በጣም አስቸጋሪ ነው። በመሬት ኳስ ተልኮልህ እግርህ ጋር ኳሱ ሲደርስ ጉልበትህን ይነካል። ሜዳው አስቸጋሪ ነው። ፌደሬሽኑ ይህን ሜዳ መስራት ይገባው ነበር እነርሱ ግን ቸል ብለውታል። ከዚህ ውጭ ግን ከኔ ጋር አብረው የተጫወቱ አሁን በስልጠና ውስጥ ካሉ ልጆች ጋር እንገናኛለን። ባለኝ የሙያዬ ልምድ አንዳንድ ነገር እንመካከራለን።

“የቤተሰብ ህይወቴ አንድ ወንድ ልጅ አለኝ። በጣም ኳስ ይመለከታል፤ ልምምድም በደንብ ይሰራል። ሆኖም ኳስ እየተጫወተ የሚገኘው እግርኳስ ተጫዋች ለመሆን ሳይሆን ፍላጎቱ ስላለው ነው። እርሱ አሁን ሙሉ ትኩረቱ ትምህርቱ ላይ ነው። የሁለተኛ ዓመት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አምስት ኪሎ ካምፓስ ተማሪ ነው። ትምህርቱ ትንሽ ጠንከር ያለ ስለ ሆነ ወደዛ ነው የሚያዘነብለው።

” የሁለቱን ታላላቅ ቡድኖችን ማልያ ለብሼ ተጫውቼ አልፌያለው። ኢትዮጵያ ቡና የልጅነት ክለቤና እግርኳስን በደንብ ያወኩበት ነው። በተለይ ከታላላቆቼ ከነ ካሣዬ አራጌ ብዙ ነገር የተማርኩበት አሳዳጊ ክለቤ ነው። ጊዮርጊስም ከገባው በኃላ በዋንጫ ታጅቤያለው። ስለዚህ ሁለቱም ቡድኖች ለኔ ልዩ ትውስታ አላቸው። በእግርኳስ ሕይወቴ ትልቅ አስተዋፆኦ አድርገውልኛል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!