ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ አስር – ክፍል ዘጠኝ

ጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ምዕራፍ አስር ላይ ደርሷል። ይህ ምእራፍ በእግርኳስ ታክቲክ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ካገኙ የአጨዋወት አቀራረቦች አንዱ የሆነው ካቴናቺዮን ከስር መሠረቱ ጀምሮ ያለፈባቸውን መንገዶች ይመለከታል። የዛሬው መሰናዶም ካለፈው ሳምንት የቀጠለ ነው።


በ1965 በተካሄደው የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሳንሲሮ ላይ ኢንተር ሚላን እና የፖርቹጋሉ ቤኔፊካ አወዛጋቢ የሆነ የፍጻሜ ፍልሚያ አደረጉ፡፡ ይህ ጨዋታ በወቅቱ የሄሬራ ቡድን የሚታወቅበትን ዓይነተኛ አጨዋወት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩ ጃየር ወደ ጎል የላከውን ጠንካራ ምት የቤኔፊካው ግብ ጠባቂ ኮስታ ፔሬይራ ሊያድን ሳይችል ቀረ፡፡ በዚህም ኢንተሮች 1-0 እየመሩ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ቤት አቀኑ፡፡ የፖርቹጋሉ ክለብ ግብ ጠባቂ ፔሬይራ በሁለተኛው አጋማሽ በጉዳት ምክንያት ሜዳ ለቆ ለመውጣት ሲገደድ ተከላካዩ ጀርማኖ እርሱን ተክቶ በጎሉ ቋሚዎች መካከል የመቆም ዱብዕዳ ወደቀበት፤ ቤኔፊካዎች በሜዳቸው ቢጫወቱም በአስር ተጫዋቾች ጨዋታውን መጨረስ ተጠበቀባቸው፡፡ ኢንተሮች የቁጥር ብልጫ ኖሯቸውም የያዙትን የ1-0 መሪነት አስጠብቀው ለመውጣት በጥብቁ መከላከልን መረጡ፡፡ ሁኔታው በርካታ ጥያቄዎችን ያጭራል፡፡ በገቢራዊነትን መርህ (Pragmatism) ችክ የማለት አባዜ ነበር? ሄሬራ ቡድኑ በራስ የመተማመን ደረጃው ከፍ እንዲል ያን ያህል ጥሮ ሳይሳካለት ቀርቶ ይሆን? ተጫዋቾቹ በችሎታቸው እምነት አልነበራቸውም? አልያስ ክለቡ ከተጫዋቾቹ አቅም ይልቅ በዳኞች አድሎአዊ ውሳኔ ላይ ጥገኛ የመሆን ልማድ ተጸናውቶት ነበር?

በሦስት ተከታታይ ዓመታት ለሁለተኛ ጊዜ የፍጻሜ ጨዋታ ማሸነፍ የተሳናቸው ቤኔፊካዎች ሁኔታውን ከቤላ ጉትማን እርግማን ጋር አቆራኙት፡፡ እውነታው ግን በታላቁ ባለውለታቸው ቅያሜ ላይ ብቻ የሚንተራስ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ይልቁኑ የችግሩ መንስኤ ሲጠቀሙበት የነበረው ጊዜው ያለፈበት የማጥቃት አጨዋወታቸው ፍሬያማ አለመሆኑ ነው፡፡ በክለቦች ጨዋታ በወቅቱ በብዙዎች ካቴናቺዮ ቅቡል የነበረ አቀራረብ ባይሆንም እንደ አንድ አማራጭ መውሰድ ግን ምክንያታዊ ነበር፡፡ ይህ የጨዋታ ዘይቤ ቀስ በቀስ በ4-2-4 ፎርሜሽን የሚዋቀረውን የጥንቱን የ”ዳኑቢያን” አጨዋወት ሥልት መተካቱም አጠያያቂ አልነበረም፡፡ ሁሉም ቡድኖች እኩል የዳኝነት ውሳኔ ቢያገኙ፣ ክለቦች ዳኞችን ባይደልሉ፣ ካቴናቺዮ ጠንካራ የማጥቃት አቅም ያላቸው ተጋጣሚዎችን ለመገዳደር የሚያስችል ዘዴ ነበር፡፡

በ1965-66 የውድድር ዓመትም ኢንተሮች በድጋሚ ስኩዴቶውን አሸነፉ፤ በአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ግን ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ በሩብ ፍጻሜው በሪያል ማድሪድ ተሸንፈው ከውድድሩ ተሰናበቱ፡፡ ለዚህኛው ጨዋታ ሁለተኛው ዙር የተመደበው ዳኛ ሃንጋሪያዊው ጂዮርጂ ቫዳስ ነበር፡፡ ሰውየው ጥንቁቅ ሆኖ ጨዋታውን በመምራት ሁለቱንም ቡድኖች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ዳኛቸው፡፡ በዚህም ማድሪዶች 1-1 አቻ ተለያይተው ቀደም ሲል ባገኙት የ1-0 ድል በድምር የ2-1 አሸናፊነት ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቀሉ፡፡ ከዓመታት በኋላ ግን ቫዳስ ለሃንጋሪያዊው ዝነኛ ጋዜጠኛ ፒተር ቦሬኒች አንድ እውነታ ተናገረ፡፡ እርሱም እንደ ሌሎቹ ዳኞች ሁሉ በኢንተሩ ባለስልጣን ሶልቲ አማካኝነት መደለያ ቀርቦለት እንደነበር ገሃድ አወጣ፡፡ ቫዳስ ግን ከሌሎች በተለየ መልኩ ጉቦ ለመቀበል ፍቃደኛ አልሆነላቸውም፤ በእምቢታው ጸንቶ ኢንተሮችን ፊት ነሳቸው፡፡

በቀጣዩ ዓመት የኢንተር ስብስብ መበታተን ጀመረ፤ ቡድኑ ቀስበቀስ ተጫዋቾቹን እየለቀቀ መፈረካከሱን ተያያዘው፡፡ በእርግጥ ክለቡ የውድድር ዓመቱን ሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቦ በአስደናቂ ብቃት ለመጀመር ቢችልም በዚሁ ድንቅ አቋሙ አልዘለቀበትም፡፡ በሚያዝያ አጋማሽ ከጁቬንቱስ በአራት ነጥቦች ልቆ የሴሪአውን አናት ከመቆናጠጡ በላይ በአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ሪያል ማድሪድን በደርሶ መልስ 3-0 ረትቶ የቀደመውን በቀል ተወጣ፡፡ ከዚያ ግን ሁኔታዎች መስመራቸውን ሳቱ፤ ነገሮች ምስቅልቅል ይሉ ጀመር፡፡ በግማሽ ፍጻሜው ከሲ.ኤስ.ኬ. ሶፊያ ጋር በተደረጉት የደርሶ መልስ ግጥሚያዎች በተመሳሳይ 1-1 አቻ ተጠናቀቁ፡፡ እናም ቀጣዩ የጥሎ ማለፍ የመለያ ፍልሚያ በቦሎኛ እንዲካሄድ የቡልጋሪያው ክለብ ደጋፊዎች ሦስት አራተኛ የመግቢያ ቲኬት እንዲወስዱ ኢንተሮች መምረጥ ተጠበቀባቸው፡፡ የሚላኑ ክለብ ጨዋታውን በጠባብ ውጤት 1-0 ማሸነፍ ቢችልም የቡድኑ አቋም እምብዛም የሚያስተማምን አልነበረም፡፡ በመቀጠል ኢንተር እያሳየ የሄደው የብቃት መዋዠቅ በጥርጣሬ ዓይን መታየቱ አስማሚ ሆኖ ተገኘ፤ የሄሬራው ቡድን ኃያልነት እየወረደ መምጣቱም ገሃድ ታየ፡፡ አስከትሎ ኢንተሮች በሴሪአው ከላዚዮ እና ካግሊያሪ ጋር አቻ ተለያዩ፤ በጁቬንቱስ 1-0 ተረቱ፤ በደረጃ ሰንጠረዡ በመሪነት ሳሉ ከተከታያቸው የነበራቸው የሰፋ የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ አለ፡፡ ከናፖሊ ጋርም ባካሄዱት ወሳኝ ጨዋታ እኩል ለእኩል አለቀ፤ ጁቬንቱስ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀረና ከሞንቶቫ ጋር አቻ ተለያየ፡፡ ነገሮች አንዴ ሲጠሙ ለማስተካከል ጊዜ ይወስዳልና ኢንተር በሜዳው ፊዮረንቲናን አስተናግዶ 1-1 ከመለያየት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተሳነው፡፡ አሁን ጁቬንቱሶች እጃቸው የገባውን እድል መጠቀም ነበረባቸውና ሌናሮዚ ቪቼንዛን አሸንፈው ተጠቀሙበት፡፡ ይህም በሴሪኤው ከመሪው ኢንተር የነበራቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ምቹ አጋጣሚ ፈጠረላቸው፡፡

የሄሬራ ቡድን የወድድር ዘመኑን ለማገባደድ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ቀረው፥ በሴሪአው ከሜዳቸው ወጪ ሞንቶቫን የሚያስተናግድበት እና በፖርቹጋል ሊዝበን ከሴልቲክ ጋር የሚደረገው የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ፍጻሜ፡፡ እነዚህን ሁለት የሞት-ሽረት ትግል የሚከወንባቸው ፍልሚያዎች ካሸነፉ ኢንተሮች ዓመቱን በሁለትዮሽ ድል ይዘጋሉ፡፡ ያን የሚያሳኩበት ወኔ እንዲሁም ለወትሮ የሚታወቁበትና መለያቸው የነበረው በራስ የመተማመን ስሜት ግን እነርሱ ጋር የነበረ አይመስልም፡፡      

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡