በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሳምንቱን እንዴት አሳለፉ?

መልካሙ በመጀመርያው ጨዋታ ግብ ሲያስቆጥር ኢዮብ ዛምባታሮ እና ቢንያም በላይም በትናንትናው ዕለት ጨዋታ አድርገዋል። ከእረፍት መልስ የመሰለፍ ዕድሉን መልሶ ያገኘው ሽመልስ በቀለም ዛሬ ይጫወታል።

👉 ትውልደ ኢትዮጵያዊው በሊቨርፑል የመጀመርያ ጨዋታው ግብ አስቆጥሯል

መልካሙ ፍራውንዶርፍ በቀዩ ማልያ የመጀመርያው ግብ አስቆጥሯል። ባለፈው ሳምንት ከሆፈንሄይም ወደ ሊቨርፑል የተዘዋወረው ትውልደ ኢትዮጵያዊው የቀጣይ ኮከብ መልካሙ ባሳለፍነው ቅዳሜ የሊቨርፑል ከ18 ዓመት በታች ቡድን ሀደርስፊልድን 5-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ አንድ ግብ አስቆጥሮ የቀያዮቹ የቀጣይ ተስፋ መሆኑን አስመስክሯል።

ከወራት ክትትል በኃላ ከጀርመኑ ክለብ ወደ መርሲሳይድ የደረሰው መልካሙ ከሌሎች ሁለት ታዳጊ ፈራሚዎች ልቆ በስፋት መነጋገርያ ሆኗል።

👉 ኢዮብ ዛምባታሮ የመጀመርያው ጨዋታ አደረገ

ከቀናት በፊት ከአታላንታ ታዳጊ ቡድን ወደ ሴሪ ሲ ክለብ ሞኖፖሊ 1966 በውሰት የተቀላቀለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ኢዮብ ዛምባታሮ ክለቡ ከፖሊስፖርት ሳንታማርያ ጋር ባደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ በቋሚነት ተሰልፎ ተጫውቷል። በፖሊስፖርት ሳንታማርያ ሜዳ የተደረገው ይህ ጨዋታ በባለ ሜዳዎቹ 2-1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ቡድኑ ዋናው የሴሪ ቸ ውድድር ከመጀመሩ በፊት ተጨማሪ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ሽመልስ በቀለ ዛሬ ጨዋታ ያደርጋል

የሀያ አራተኛ ሳምንት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሲቀጥል ምስር ለል መቃሳ ከሀራስ ኤል ሁዱድ ጋር ይጫወታሉ። ሊጉ በድጋሚ ከተጀመረ በኃላ የተሻለ የመጫወት ዕድል እያገኘ ያለው እና ባለፈው ጨዋታ አንድ ኳስ ለግብ አመቻችቶ ያቀበለው የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አምበል ሽመልስ በቀለም ጨዋታውን በቋሚነት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

ወጥ አቋም ማሳየት የተሳናቸው ምስር ለል መቃሳዎች በዛማሌክ ሽንፈት በገጣማቸው ማግስት ኤል ጎና እና አል መስሪን በተከታታይ አሸንፈው ከወራጅ ቀጠናው ፈቀቅ ማለት ቢችሉም ከቀናት በፊት በሜዳቸው በዋዲ ዴግላ 3-1 ሽንፈት ገጥሟቸዋል።

በውድድሩ አራት ግቦች ያስቆጠረው እና በቅርቡ ከረጅም ግዜ ጉዳት የተመለሰው የአስዋኑ ኡመድ ኡክሪም ክለቡን በሊጉ ለማቆየት በሚደረገው ትግል ለመቀላቀል በቅርቡ ወደ ጨዋታ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ኡምአዎች ተስፋቸው ያለመለሙበት ወሳኝ ድል አስመዘገቡ

ኢትዮጵያዊው ቢንያም በላይ የሚገኝበት የስዊድኑ ኡምአ በትናንትናው ዕለት ጨዋታውን ሲያደርግ በወሳኝ የሜዳ ውጭ ጨዋታው ድል አድርጎ ተመልሷል። ከብራግ ጋር በነበረው የትናንትናው ጨዋታ ቢንያም በላይ እንደተለመደው ዘጠና ደቂቃ ተጫውቶ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ሲወጣ የቡድኑ የማሸነፍያ ግብንም ዊስትሮይም አስቆጥሯል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!