የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሊራዘም ይችላል

ለ2013 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የተጫዋቾችን ዝውውር እንዲያደርጉ የተያዘው ቀን ሊራዘም የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ የእግር ኳስ ውድድሮችን በ2013 ለማስጀመር የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እየሰራ ይገኛል፡፡ ክለቦችም ቀጣዩን የውድድር ዘመን ታሳቢ በማድረግ በርካታ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እየተስማሙ ይገኛሉ፡፡የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቦች ዝውውር የሚፈፅሙበት ወቅትን ከመስከረም 2 እስከ ህዳር 25 ቀን 2013 እንደሚሆን ለፊፋ ባስገባው መረጃ ቢገለፅም አሁን ካለንበት ሁኔታ አንፃር ሊራዘም እንደሚችል የፌዴሬሽኑ የፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ጠቁመዋል፡፡ ዝውውሩ ሊከፈት አስራ ሦስት ቀናቶች ቢቀሩትም መንግሥት ምላሽ ለመስጠት በመዘግየቱ የተባለለትን ቀን ላይጠብቅ ስለሚችል መራዘሙ የማይቀር ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

“መንግሥት ውድድሩ መቼ ይጀመር የሚለውን ጉዳይ እስከ አሁን አላሳወቀንም። ይህ ባልሆነበት ይፋ ባደረግነው ቀን ለማካሄድ ትንሽ አስቸጋሪ ነው፡፡ ፊፋም እርግጠኛ የሆንበትን የዝውውር ቀን ግለፁልኝ ስላለ መንግሥት ምላሽ ባልሰጠበት ሁኔታ መስከረም 2 ይከፈታል የተባለውን ጊዜ እንዳንጠቀም የሚያደርጉ ምክንያቶች ስለሆኑ መራዘሙ አይቀርም። የሚራዘምበትም ሁኔታ ይኖራል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት መንግስት ምላሽ መስጠቱ ከታወቀ በኃላ የዝውውር መስኮቱ በቶሎ በተፈቀዱበት ቀናት መካከል በይፋ ሊከፈት ይችላል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!