ከፍተኛ ሊግ ምድብ 1 ፡ መቐለ መሪነቱን ሲቆናጠጥ ወልድያ በእዮብ 4 ግቦች ታግዞ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል 

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደዋል፡፡ መቐለ ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ የምድቡን መሪነት ሲቆናጠጥ ወልድያ ወደ አሸናፊነት በተመለሰበት ጨዋታ እዮብ ወልደማርያም የ4 ግቦች ጀግና ሆኗል፡፡

ፋሲለደስ ላይ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የፋሲል ከተማ እና መቐለ ከተማ ጨዋታ በመቐለ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የመቐለን የድል ግቦች ክብሮም አስመላሽ እና ወልዳይ ገብረስላሴ ከመረብ ሲያሳርፉ የፋሲል ከተማን ግብ ሮቤል ግርማ አስቆጥሯል፡፡ በጨዋታው ዳኞች እና ደጋፊዎችን ያወዛገቡ ክስተቶች የተስተናገዱ ሲሆን ድሉ መቐለ ከተማ 17 ነጥቦች ሰብስቦ በምድቡ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡

አዲስ አበባ ፖሊስ አበበ ቢቂላ ላይ ሱሉልታ ከተማን አስተናገዶ 0-1 ተሸንፎ የደረጃ ሰንጠረዡን አናት ለመቐለ አስረክቧል፡፡ ሱሉልታ ከተማን ከወራጅ ቀጠና ያወጣች ወሳኝ የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው ኤርሚያስ ዳንኤል በሁለተኛው አጋማሽ ነው፡፡ በጨዋታው መጨረሻ በሁለቱ ቡድን ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች መካከል ግርግር የተፈጠረ ሲሆን የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና መድን ተጫዋች ሳሙኤል ደግፌ ድርጊት በስፍራው የተገኘውን ደጋፊ አሳዝኗል፡፡

ወልድያ የምድቡ ግርጌ ላይ የሚገኘው አክሱምን 4-0 በማሸነፍ ባለፈው ሳምንት የደረሰበትን ከባድ ሽንፈት አወራርዷል፡፡ የወልድያ ሁሉን ግብ ከመረብ ሳረፈው እዮብ ወልደ ማርያም ነው፡፡ እዮብ ለዘንድሮው የወልድያ ውጤታማነት ቁልፍ ሚና መጫወቱን የቀጠለ ሲሆን በ8 ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት መምራት ጀምሯል፡፡

መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ መድን ወሎ ኮምቦልቻን አስተናገዶ 2-0 አሸንፏል፡፡ ወሎ ኮምቦልቻ የውድድር ዘመኑ የመጀመርያ ሽንፈት እንዲደርስበት ያስገደዱ ግቦችን ከመረብ ሳረፉት ሀብታሙ ወልዴ እና አስራት ሸገሬ ናቸው፡፡

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃንን አስተናግዶ በብሩክ ገብረአብ እና ኤፍሬም ሃይላት ግቦች 2-1 አሸንፏል፡፡ ለደብረብርሃን የማስተዛዘኛውን ግብ ያስቆጠረው እሱባለው አንለይ ነው፡፡ ውጤቱ ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ አሰልጣኝ እንድርያስ ብርሃኑን ያሰናበተው ወልዋሎን ወደ ድል ሲመልሰው ደብረብርሃንን ከወራጅ ቀጠናው እንዳይወጣ አድርጎታል፡፡

ቡራዩ ከተማ ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርትን በበደረጄ ጋዲሳ ግብ 1-0 ሲያሸንፍ ሰበታ ከተማ ሙገር ሲሚንቶን በቴዎድሮስ ወርቁ ግብ ታግዞ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡

በዚህ ምድብ ቀሪ የ7ኛ ሳምንት ጨዋታ ማክሰኞ ሲደረግ ባህርዳር ላይ አማራ ውሃ ስራ ባህርዳር ከተማን ይገጥማል፡፡

የደረጃ ሰንጠረዡ ይህንን ይመስላል፡-

HL A

 

ፎቶ – መቀለ ከተማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *