ሶከር ሜዲካል | ስብራት እና ውልቃት

በእግር ኳስ በጣም ተዘውትረው ከሚታዩ ህመሞች ወይንም ጉዳቶች የአጥንት መሰመር እና የመገጣጠሚያ አካባቢ የሚኖር መውለቅ አደጋዎች የሚጠቀሱ ናቸው። ከአጠቃላይ ጉዳቶችም 10% የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ። በእግር ላይ የሚያጋጥሙ ስብራቶች 44.4% ድርሻውን የሚይዙ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ በእጅ ላይ የሚደርሱት ወደ 27% የሚጠጉት ናቸው።

በዚህ ሳምንት የሶከር ሜዲካል ዓምዳችን የምንመለከተውም የስብራት እና ውልቃት መንስኤ እና መገለጫዋች እንደዚሁም እንዴት እንደሚመረመሩ እና እንደሚታከሙ ይሆናል።

 

ስብራቶች በሁለት አይነት ዋና መንገዶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። መጠኑ ከፍ ያለ ጫና በተደጋጋሚ አጥንት ላይ በሚኖርበት ወቅት የጫና ስብራት (Stress Fracture) የሚከሰት ይሆናል። ከዚህም በተጓዳኝ በኃይል የሚኖር የውጫዊ ጉልበት ቀጥተኛ ስብራት (Overt Fracture) የሚመጣበት መንገድ ነው።

ውልቃቶች የሚከሰቱት የመገጣጠሚያዎች ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ላይ መዛባት በሚኖርበት ወቅት ነው ። በዚህን ወቅት መገጣጠሚያ ላይ ከተገናኙት አጥንቶች አንዱ ከእቅፉ (joint socket) ወጥቶ የሚገኝ ይሆናል። ውልቃት በአብዛኛው እግር ኳስ ላይ እንደ ስብራት በዝቶ አይታይም። የትከሻ ውልቃት በግብ ጠባቂዎች ላይ ተዘውትሮ የሚስተዋል ሲሆን የእግር አጥንቶች የሆኑት Fibilua እና Tibia ላይም ውልቃት መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።

 

በሜዳ ላይ ተገኝቶ ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳቶች የሚያክምና የሚመረምር ባለሙያ ጉዳቱ የተከሰተበትን መንገድ ማወቁ እና መመልከቱ ለስራው በጣም አስፈላጊ ነው።

የጫና ስብራት (Stress Fracture) በአብዛኛው መገለጫው ህመም ሲሆን ይህ በሚኖርበት ወቅት ተጫዋቹ ከሜዳ እንዲወገድ የሚመከር ሲሆን ድጋሚም ከጥቂት ጊዜ በኋላ መመርመር አስፈላጊ ነው።

በጨዋታ ወቅት የሚያጋጥሙ ስብራቶች የሚከተሉት መገለጫዎችን በስብራቱ ቦታ ላይ ያሳያሉ።

– ከፍተኛ የሆነ ህመም
– እብጠት
– የቅርፅ መዛባት (Deformity)
– መቁሰል (Bruising)
– በተጎዳው እግር በኩል ክብደትን መሸከም አለመቻል።

በጨዋታ ወቅት በሚኖሩ የአጥንት ውልቃቶች ወቅት የሚስተዋሉ የሚስተዋሉ የህመም ስሜቶች:

– መገጣጠሚያ ከቦታው ሲወጣ የሚያሳትውቅ ስሜት (popping out)

– በተጎዳው መገጣጠሚያ በኩል የሚኖር ህመም

– የተጎዳውን መገጣጠሚያ የማንቀሳቀስ ችግር

– የተጎዳው መገጣጠሚያ አካባቢ የሚኖር የስሜት መጥፋት (loss of sensation)

– ከተለመደው ወጣ ያለ ዕብጠት ወይንም የመገጣጠሚያው ቅርፅ እና መጠን መለወጥ ናቸው።

 

ምንም እንኳን አብዛኞቹ ስብራቶች ለህይወት አስጊ ባይሆንም የአተነፋፈስ እና የደም ዝውውር ሁኔታን ከምንም ነገር በፊት ቀድሞ መመልከት እና ማከም ወሳኝ ነው።

ህክምናው ከመጀመሩ በፊት መረጋገጥ ያለባቸው ነገሮች:

– ተጫዋቹ ንቁ መሆኑ

– የአንገት እና የህብረ ሰረሰር (spine) ጉዳት ካለ ማየት

– የአተነፋፈስ ሁኔታ

– መድማት መኖሩ እና ካለም መቆጣጠር

ስብራት በሚታከምበት ወቅት የሚኖሩ መሰረታ ጉዳዮች:

– ማንኛውም አይነት ውጫዊ ደም መቆጣጠር
– ከስብራት በታች ያሉ የነርቭ እና የደም ዝውውር ሁኔታን መመልከት
– ህመምን ማስታገስ
– የስብራቱን ቦታ ማሸግ እና አንድ ቦታ ላይ ማስቀመጥ። እንደ አስፈላጊነቱም ወደ ላይ ከፍ ማድረግ።

ሀገራችን ውስጥ ስብራትን እና ውልቃትን በተለምዶ ወጌሻዎች ጋር ሄዶ የመታከም ልማድ አለ። ነገር ግን ሁሉም እንደዚህ ያለው ጉዳት በማሸት ብቻ የሚስተካከል አይደለም። ይልቁንስ በአብዛኛው ጊዜ ሁኔታዎቹ ሲባባሱ ይስተዋላል። በመሆኑም በቂ ሳይንሳዊ ዕውቀት እና ትምህርት ባለው ባለሙያ መታከም የተጫዋቾች መብት ሲሆን ብቁ ባለሙያዎችን መቅጠር ደግሞ የክለቦች እና ብሄራዊ ቡድን ኃላፊነት ብሎም ግዴታ ነው።