የሰማንያዎቹ… | የጨዋታ አቀጣጣዩ ቦጋለ ዘውዴ (ኢንተሎ)

አይደክሜ እና ታታሪው የመሐል ሜዳ ቴክኒሻን፣ በአንድ ቀን ሁለት ዘጠና ደቂቃ የተጫወተው፣ በወታደራዊ ማዕረግ ሃምሳ አለቃ የነበረው የሰማንያዎቹ ድንቅ ተጫዋች ቦጋለ ዘውዴ (ኢንተሎ) ማነው?

አባቱ አቶ ዘውዴ በአቅም ማነስ ኑሮን ለማሸነፍ ከወላይታ ወደ አዲስ አበባ የአምስት ዓመት ወንድ ልጃቸውን ይዘው ይመጣሉ። ታዲያ አቶ ዘውዴ ሁሉም ነገር እንዳሰቡት ሳይሆን ለከፋ ችግር ተዳርገው በአዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ ልጃቸውን ይዘው በጎዳና ላይ እያደሩ በኔብጤነት (ልመና) ሕይወትን መግፋት ጀመሩ። በወቅቱ የደርግ መንግሥት በጎዳና የሚኖሩ ህፃናትን በመውሰድ መጠለያ እየሰጠ ያሳድግ ስለነበረ በአሳዛኝ ሁኔታ አባትና ልጅ ዳግመኛ ላይገናኙ ትንሹ ህፃን ቦጋለ ዘውዴ ወደ ታጠቅ ጦር ሰፈር የህፃናት ማሳደግያ ገብቶ ህይወትን መኖር ጀምሯል።

በታጠቅ የህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ትምህርት እየተማረ ጎን ለጎን ደግሞ እግርኳስን እየተጫወተ አደገ። ከእርሱ በእድሜ ከሚበልጡ ወታደሮች ጋር እግርኳስን ሲጫወት የተመለከቱት የጦር ሹማምቶች ለተለያዩ የክፍለ ጦር ቡድኖች እንዲጫወት አድርገውታል። የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች አሰልጣኝ ቀፀላ ከበደ ራስ ሆቴልን እያሰለጠነ ጎን ለጎን ለክፍለጦር የሙዚቃ ቡድን ያሰለጠን ቦጋለ ዘውዴን ያውቀው ስለነበረ ሃምሳ ብር ደሞዝ እየተከፈለው ለራስ ሆሬል ይጫወት ነበር። ከዕለት ወደ ዕለት በሚያሳየው እድገት የተገረሙት የጦር መኮንኖች በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ትልቅ ስም እና ዝና ለነበረው ምድር ጦር (መቻል) በአስራ ሰባት ዓመቱ እንዲጫወቱ አደረጉት።

ሆኖም በጊዜው የነበሩት ታሪኩ መንጀታ፣ ሙሉዓለም እጅጉ፣ ዓለምሰገድ አሚቼ እና ማትያስ ኃብተማርያምን አስቀምጦ ቋሚ ለመሆን እጅግ ፈተና ነበር። ልጅ እና ሰውነቱም ገና ደቃቃ በሚል አሰልጣኝ መቶ አለቃ መሰለ ኢንተሎን ረጅም ጊዜ በተጠባባቂ ወንበር ላይ አንዳንዳንዴም ከጨዋታ ውጭ በመሆን አሳልፏል። በአንድ አጋጣሚ ሙሉዓለም እጅጉ ጉዳት ሲያስተናግድ የመሠለፍ እድል አግኝቶ ወደ ሜዳ የገባው ኢንተሎ አጋጣሚውን በአግባቡ ተጠቅሞበት በቀጣይነት ለመጫወት ችሏል። ታዲያ ምን ያደርጋል ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ግብፅ ሄደው አስራ አምስት ተጫዋቾች ጠፍረው ከ14 ቀን በግብፅ ቆይታ አድርገው የኢትዮጵያ መንግሥት ከግብፅ መንግስት ጋር ተደራድሮ ወደ ሀገራቸው እንደገቡ በዓለም ሚዲያ የሀገር ስም አጥፍታችዋል በሚል እንዲረሸኑ (እንዲገደሉ) ትዕዛዝ ተላልፎ ወደ ከርቸሌ ገብተዋል። የዚህ ሁሉ አስተባባሪ ደግሞ “አንተ ወታደር ሆነህ አገርህን ክደሀል” ተብሎ ኢንተሎ በልዩ ሁኔታ እርሱን ሊገሉት እንደሚችሉ ተነግሮት አስቸጋሪ የፈተና ህይወት አሳልፎ እንደ አጋጣሚ ሆኖ 1983 ግንቦት ወር የመንግስት ለውጥ መጥቶ ነፃ ሊወጣ ችሏል።

በወታደር ቤት ታንከኛ፣ የሙዚቃ ባለሙያ በመሆን ከማገልገሉ በተጨማሪ የሃምሳ አለቃ ማዕረግ አግኝቷል። ከመንግስት ለውጥ በኃላ መቻል በአሳዛኝ ሁኔታ ሲፈርስ ኳስ አቀጣጣዩ ባለ ግራ እግሩ ድንቅ ተጫዋች ወደ ንግድ ባንክ አምርቷል። በንግድ ባንክ የተሳኩ አምስት ዓመታትን ሲያሳልፍ በተለይ የ1987 ንግድ ባንክ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን የሚሆንበትን ሦስት እድል ይዞ በቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫ ባጣበት ዕለት ኮከብ ተጫዋች የመሆን እድሉ ከፍተኛ ቢሆነም ሳይሳካለት በቅረቱ እጅግ በጣም እንዳዘነ ይነገራል።

በመቻል እና በንግድ ባንክ ያጣውን የዋንጫ ረሀብ ለማርካት በ1988 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢያመራም በመታሰቢያ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 በሆነ ውጤት በረቱበት ጨዋታ ላይ የማሸነፊያ ብቸኛዋን ጎል በማስቆጠር ዋንጫ ከማንሳቱ ውጭ የሀገሪቱን ትልልቅ ዋንጫዎችን ሳያነሳ ከፈረሰኞቹ ጋር ከሁለት ዓመት ቆይታ በኃላ ጉዳት አጋጥሞት ወደ ኒያላ አምርቷል። ከኒያላም ጋር የጥሎ ማለፍ ዋንጫ የሚያነሳበት ሰፊ ዕድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም እርሱና ዋንጫ ፀብ ያለባቸው ይመሰል ለወላይታ ቱሳ ዋንጫውን አሳልፈው የሰጡበት አጋጣሚ መቼም የሚረሳ አይደለም። ወደ እግርኳስ ማብቂያው አካባቢ ጋሽ መንግሥቱ ወርቁ ለአየር መንገድ እንዲጫወት ጠርተውት ከተጫወተ በኃላ ዘጠናዎቹ መጀመርያ ላይ ጫማውን ሰቅሏል።

በብሔራዊ ቡድን ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን በመጫወት ስሙን መፃፍ የቻለው ኢንተሎ ኳስ ካቆመ ብዙም ሳይቆይ የአየር መንገድ ታዳጊ ቡድንን እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ ሲያሰለጥን ቆይቶ ከረጅም ዓመት በኃላ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክን በ2010 የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ምክትል በመሆን ሲሰራ ቆይቶ ኤሌክትሪክ በመውረዱ እስካሁን ክለብ ማሰልጠን አቁሞ በግል ሥራ እየተዳደረ ይገኛል። ይህ የሰማንያዎቹ ባለ ተስጥኦ ኮከብ ተጫዋች የዛሬው ተረኛ ዕንግዳችን በመሆን ከእኛ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አሰናድተነዋል። መልካም ንባብ!

“በእግርኳስ ተጫዋችነት ባሳለፍኩት ህይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ብዙ ፈተናዎችን፣ ውጣ ውረዶችን አልፌያለው። ያም ቢሆን በትላልቅ ክለቦች በዋንጫ ባይታጀብም በግሌ ጥሩ ጊዜ የነበረኝ በመሆኑ በዚህ ደስተኛ ነኝ። ሆኖም ግን ከንግድ ባንክ ጋር በ1987 ሦስት እድል ይዘን ገብተን ያጣሁት ዋንጫ እስካሁን ድረስ የሚቆጨኝ ነው። ጊዮርጊስን በረጅም ርቀት እንበልጠው ነበር። ሆኖም በደጋፊው እና በዳኛ ታግዞ ለመጨረሻው ጨዋታ ደረሰ እንጂ በቀላሉ ዋንጫው የኛ ነበር። ብቻ ባንክ የዛን ጊዜ ዋንጫውን ቢያነሳ ኖሮ ደጋፊ ይበዛለት፣ ህዝባዊ ክለብ ሆኖ ቀጥ ያለ ቁመና ኖሮት መዝለቅ ይችል ነበር። አይፈርስም ሁሉ ነበር። ለመፍረሱ የእኛ አስተዋፆኦ አለው ብዬ እቆጫለው። ያኔ ያንን ዋንጫ አለማንሳታችን አሁንም ድረስ ይፀፅተኛል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ ገብቼ ብዙ ስኬትን አጣጥማለው ብልም አልተሳካልኝም። ከመታሰቢያ ዋንጫ በቀር ሌሎች ትልልቅ ዋንጫ አላነሳውም። አጋጣሚ ሆኖ ለዋንጫ አልታደልኩም። ባንክ የአንድ ዓመት ኮንትራት አለው እኔ ደግሞ የለኝም በሚል ክርክር ውስጥ የነበርኩ በመሆኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የኢትዮጵያ ሻምፒዮን አልሆንኩም። በእግርኳስ ተጫዋችነቴ በግሌ ጥሩ የውድድር ዓመት ባሳልፍም በተጫወትኩባቸው ክለቦች ሁሉ ከዋንጫ ጋር ብዙም አልተገናኘሁም፣ ዕድለኛም አይደለሁም።

” ኮከብ ተጫዋች እንደምሆን የፌዴሬሽን ሰዎች ነግረውኛል። ወደ ሜዳ ስገባ ዋንጫ እንደማነሳ እና እኔም በግሌ ኮከብ ተጫዋች እንደምሆን ነበር የማስበው። መጨረሻ የሆነው ግን ሌላ ነው። እየመራን ጨዋታውን ጥሩ እየተቆጣጠርን ባለንበት ሰዓት ምን እንደተፈጠረ አሁን ላይ ሆኜ ሳስብ ግርም ይለኛል። በቃ በጊዮርጊስ ተሸነፍን በጣም አዘንኩ። ሜዳ ውስጥ ተኝቼ አለቀስኩ። ለሦስት ቀን ከቤቴ ሳልወጣ በብስጭት ምግብ ሳልበላ ቆየሁ። አጋጣሚ ዋንጫ ከወሰደ ቡድን ተብሎ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመረጠ። አሁንም ድረስ በወቅቱ የነበረውን ነገር ሁሉ ለመቀበል የምቸገረው ውጤት ነው።

“በባህሪዬ በጣም እልኸኛ የሆንኩት ከልጅነቴ ጀምሮ ለብሔራዊ ቡድን መመረጥ፣ ሰው ሁሉ የሚያቀኝ ተጫዋች መሆን አለብኝ በማለት ዓላማ ነበረኝ። ልጅ ሆኜ ስታዲየም እየገባው ጨዋታ እከታተል ነበር። በጣም የማደንቃቸው ተስፋ ሚካኤል ዳኜ ፣ ሰለሞን ጋሜ፣ ንጉሴ ገብሬ እነዚህን በጣም ምርጥ ተጫዋቾችን እያየው ነው ያደጉት። እንዲሁም አብሬው አጠገቡ የተጫወትኩት ሙሉዓለም እጅጉ የሚተኛበት እየተኛው፣ የእርሱን ጫማ እያፀዳው፣ እያደረኩ የእርሱን ልብስ እየለበስኩ ነው እነርሱ መሆን አለብኝ በማለት ያደኩት። ወታደር ቤት ከሆንክ ደግሞ መሸነፍ የለም ከተሸነፍክ ወደ ሌላ ወደ ውትድርናው ቦታ ስለምትሄድ ይህ እንዳይሆን ሁሌም ላለመሸነፍ እልህኛ ሆነ ነው ወደ ሜዳ የምትገባው። ስለዚህ በጣም እልህኛ ነበርኩ። አንድ ተጫዋች ደግሞ ዓላማ ሊኖረው ይገባል። ለምድነው የምጫወተው ለማነው የምጫወተው? የት መድረስ አለብኝ ብሎ ካላወቀ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ ሁሌ ሽንፈት ካለ አንተን የሚያየህ፣ የሚያደንቅህ፣ ለብሔራዊ ቡድን የሚመርጥህ ሰው የለም። ስለሆነም ሁሌም በጣም ጠንክሬ እሰራ ነበር።

” ሁለት ዘጠና ደቂቃ የተጫወትኩበት አጋጣሚ በምን መሰለህ ለብሔራዊ ቡድን ምርጫ (ምልመላ) ሲደረግ ነው። የመጀመርያውን ዘጠና ደቂቃ ጨርሼ ልቀመጥ ስል ቆይ በደንብ እንይህ ብለው ድጋሚ ግባ ተብዬ ሌላ ዘጠና ደቂቃ ተጫውቻለው። ይህ ምንን ያሳያል ካልከኝ በውስጤ የነበረውን ጥንካሬ፣ ምን ያህል ትንፋሽ እንደነበረኝ እና ጥሩ ብቃት እንደነበረኝ ማሳያ ነው። በሳይንሱ የማይመከር ቢሆንም በዛ ሰውነቴ ባይገርምህ 65 ኪሎ ነበርኩኝ ግን ጠንክሬ ስለምሰራ ይሄን ማድረግ ችያለው። ድሮ በቀን ሦስት ጊዜ ነበር ልምምድ የምንሰራው እኔ ግን ቀድሜ ሌሊት ተነስቼ ብቻዬን እሰራ ነበር። ተከላካይ እንዲዘኝ አልፈልግም። ሁሌም የብሎን ጫማ አድርጌ ነበር ወደ ሜዳ የምገባው። ምክንያቱም ራሴን ለመጠበቅ። በድንብ እንድጫወት እንዲረዳኝ እና በሰው ዘንድ በደንብ ለመታወቅ ስለ ምፈልግ፣ ዓላማ ስለነበረኝ ነው። አንድ ቀን ተመትቼ(ጉዳት) አጋጥሞኝ በቃሬዛ ወጥቼ አላቅም። የምተማመንበት ቤተሰብ፣ ሰው የለኝም ብቸኛ ነኝ ወይም የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሆኜ ስራ በመስራት እራሴን ለመደጎም አልችልም። ስለዚህ ጎዳና ላይ እንዳልወድቅ የኔ ህይወት ኳስ ብቻ ስለሆነ ኳስ የምትፈልገውን ዲሲፕሊን አክብሬ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ጠንክሬ መስራቴ ነው ሁለት ዘጠና ደቂቃ የተጫወትኩት።

“ኢንተሎ ቃሉ የኦሮምኛ ነው። ሠፈር ውስጥ የሚኖሩ ቀልደኛ አራዳ የሆን ልጆች አሉ ስም ያወጡ፤ ያን ደግሞ በቃ ሰው ይቀበላቸዋል። ለኔም እንደዛ ነው አንድ ልጅ ስጫወት አይቶ አንቺ ልጅ ኢንተሎ ነሽ ብሎ ስም አወጣልኝ ይኸው እስከዛሬ መጠራዬ ሆኖ ቀርቷል።

“ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ግብፅ ላይ የጠፋነው ተጫዋቾች ጉዳይ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነበር። በተለይ እኔ ላይ የደርግ መንግስት ኃላፊዎች በጣም ተበሳጭተው ነበር። አንተ ወታደር ነክ እንዴት ሀገር ትከዳለህ በሚል እንደምገደል ነበር የማቀው በጣም ጭንቀት ፍርሀት ውስጥ ነበርኩ ለጥቂት የመንግስት ለውጥ መጥቶ ከሞት አመለጥኩኝ እንጂ ያጊዜ ከባድ ነበር።

“በእግርኳስ ተጫዋችነቴ ፈተኝ ጊዜዎችን አሳልፌያለው። በመጀመርያ አንድ ተጫዋች እግርኳስ ሲጫወት ቤተሰቡን ማወቅ አለበት። እኔ በዚህ አልታደልኩም። የቤተሰብ ጣዕም፣ ናፍቆት እና ፍቅር አላገኘሁም። በዓላቶች ሲደርሱ ሁሉም ወደ ቤተሰቡ ሲሄድ እኔ ግን ብቻዬን በካንፕ ውስጥ ብቻዬን ነበር የምቀረው። ብቻ ብዙ ነገሮች ፈተናዎችን አልፌለው። እስካሁንም ደረስ እናት እና አባቴን አላቅም። አንድ ሰው እናት እና አባት ሊኖረው ይገባል። ሁሌ እናፍቃለው። አላቃቸው የተወለድኩት ወላይታ እንደሆነ እሰማለው እንጂ የት እንዳሉ ቦታውን እንኳን አላቅም። ባቀው እንኳን ቦታው ሄጄ እፈልግ ነበር። ግን አላቀውም እንደዚህ ያሉ ነገሮች ፈተና ሆነውብኝ ብቸኝነት አሳልፌለው። እስካሁን ደረስ የምፈተንበት ነገር ነው።

“ኒያላ እያለው በጣም የሚገርም ገጠመኝ ነው። የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ለማለፍ እና በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን የሚወክለው ቡድን የሚለይበትን ወሳኝ ጨዋታ ጅማ ከተማ ላይ ከወላይታ ቱሳ ከሚባል ቡድን ጋር እንጫወታለን። ከእረፍት በፊት 3-0 እየመራን ነበር። አስብ እንግዲህ በሰፊ ጎል ልዮነተፍ እየመራን ነበር። በጊዜው አሰልጣኛችን ሰውነት ቢሻው ነበር። እረፍት ወጥተን እኔና አንድ ካሳሁን የሚባል ጎበዝ ልጅ ነበርን እናተ እረፉ በቃ አታስፈልጉም ብሎ ቀየረን። በዛን ሰዓት ዘላለም ምስክር (ማንዴላ) ነበር። እሺ ብለን የአሰልጣኝን ትዕዛዝ አክብረን ወጣሁኝ። በዚህ ጊዜ የወላይታ ቱሳ ተጫዋቾች በቃ፣ በቃ ኢንተሎ ወጥቷል። አሁን ነው መጫወት በማለት ተነጋገሩ። ከዛ እኔ ሻወር እየወሰድኩኝ አንድ አገቡ፣ ታጥቤ ስወጣ ሁለተኛ አገቡ ተመልከት ከዚህ በኃላ የኒያላ ተጫዋቾች መደናገጥ ጀመሩ። ሦስት ለዜሮ የምትመራ ከሆነ ኳሱን ይዘህ በብልጠት እየተጫወትክ አንድ ብትደግም ጫዋታው ያልቅ ነበር። መሐል ላይ ኳስ የሚይዝ ጠፋ ሦስተኛ ጎል አገቡ። ሰውነት ቢሻው ወይኔ ባላስወጣሁት ይላል። እኔ ደግሞ ተናድጄ ፈልገህ አይደለ ያስወጣህኝ በሚል በዛ መሐል ጭቅጭቅ ተፈጠረ በመጨረሻም በመለያ ምት ቱሳ አሸንፎ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ መድረክ ተሳታፊ ሆኗል። ባቃ እኔና ዋንጫ አንተዋወቅም (… እየሳቀ)።

ወደ አሰልጣኝነት የገባሁት ወድያው ኳስ እንዳቆምኩ ነው። በጊዜው ኮርስ ይሰጡ የነበሩት ካሳሁን ተካ፣ ሰውነት ቢሻው ነበሩ። ከእነርሱ ስልጠናውን ወስጄ በታዳጊ ላይ እየሰራው አየርመንገድ ሲፈርስ ማሰልጠኑን አቁሜ ወደ ግል ሥራዬ ገባው ከረጅም ዓመት በኃላ አሸናፊ በቀለ ጠርቶኝ መብራት ሀይል እስኪወርድ ድረስ ምክትል አሰልጣኝ ሆንኩ። አሁን ምንም እያሰለጠንኩ አልገኝም።

” መብራት ኃይል መውረድ ምክንያት በወቅቱ የነበሩ ተጫዋቾች እኔ ካሳለፍኩት የተጫዋችነት ባህሪ ጋር ፍፁም የሚቃረን ነበር። እኔ እንዲህ ያለ የእግርኳስ በህይወቴ አላሳለፍኩም። ኳሱ በጣም ነው ግራ የሚያጋባህ። እውነት ኳስ ጨዋታ እንዲህ ነው ወይ አልኩ! እኔ የማቀው ለለበስከው ማልያ መሞት አለብህ ማንም ሊመራህ አይገባም። እኔን ሊያበላኝ፣ ሊያጠጣኝ፣ ሊያኖረኝ የሚችለው ክለቡ ነው እንጂ ግለሰቦች አይደሉም። ግለሰቦች ሲፈልጉ እንድጫወት፣ ሲፈልጉ እንዳድም ሊያደርጉኝ አይገባም። መብራት ኃይል ያየሁት ደጋፊ ለብቻ፣ ተጫዋቾች ለብቻ ተከፋፍለዋል። እንዲሁም ቀድሞ ኤልፓ ተጫውተው ያቆሙ ሠራተኞች የሆኑ ተጫዋቾች ቡድኑ ላይ ችግር ይፈጥሯሉ። በዚህ መሐል ነው የገባሁት የተረጋጋ ቡድን አልነበረም። ብቻ ተጫዋቾቹ ቢዝነስ ነው የሚሰሩት፣ ቢዝነስ ይስሩ እሺ ግን ያመጣቸውን ክለብስ፣ ማልያስ ፣ ከአንተ ጀርባ ክለቡ “ቢ “ሲ” ቡድን አለው እነዚህስ ከግምት አታስገባም። ክለቡ እኮ ሊወርድ ነው። ሦስት አራት ዓመት እንዴት አንድ ክለብ ላለመውረድ ትጫወታለህ? ስህተትህን አታርምም፣ ችግሩን አትፈታውም። እንዴት ከጨዋታ ውጭ የሚቀመጥ ጋናዊ ተጫዋች ክለቡ ውስጥ ታመጣለህ ብቻ በአሳዛኝ ሁኔታ ቡድኑ ሊወርድ ችሏል።

“የቤተስብ ህይወቴ ከባለቤቴ ያገኘሁት ሁሉን ነገር ያስረሳኝ የቤተሰቦቼ ምትክ ዳግማዊ ቦጋለ የሚባል የ17 ዓመት ወንድ ልጅ አለኝ። በጣም ጎበዝ ተጫዋች ነው። ቡና ሙከራ አድርጎ እንዳጋጣሚ ልጅ ስለነበረ መልሰውታል። እኔ ትልቅ ተጫዋች እንዲሆን በሚገባ አግዘዋለው እንጂ ስም እና የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ስለሆንኩ ይህን ተጠቅሜ ክለብ ላስገባው አልፈልግም። ሰው አይቶት ይህ የማን ልጅ ይበል እንጂ እኔ በራሱ ጥረት ችሎታውን አምነውበት፣ አቅሙን አሳይቶ እንዲገባ ነው የምፈልገው። ሆኖም በጣም ጎበዝ፣ ልነግርህ የማልችለው አቅም ያለው። ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ መመስከር እችላለው። እኔ እንደ ኮስትር ያለ ትልቅ መኪና አለኝ ተማሪዎችን እያመላለስኩ እየሰራው እገኛለው። ወደ ፊት አሰልጣኝ ሆኜ በጣም መምጣት እፈልጋለው። እኔ የተፈጠርኩት ለእግርኳስ ነው።


🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!