ስለ ኃይሉ አድማሱ (ቻይና) ሊያውቋቸው የሚገቡ ዕውነታዎች

ከዘጠናዎቹ ወርቃማ ትውልድ አባላት መካከል ነው። ጥበበኛ እና ባለ አዕምሮ ተጫዋች ነው። በኢትዮጵያ እግርኳስ የችሎታውን ያህል ያልተዘመረለት ድንቁ አማካይ ኃይሉ አድማሱ (ቻይና) ማነው ?

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባልተጠበቀ ሁኔታ የለውጥ ዐብዮት ላይ ነው። የቀድሞ ድንቅ ተጫዋቾቹን እየቀነሰ ቡድኑን በወጣት ተጫዋቾች የመቀየር እንቅስቃሴ ላይ ተጠምዷል። በቀነሳቸው አስራ ሁለት ነባር ተጫዋቾች ምትክ ከታዳጊ ቡድኑ ወደ ዋናው ቡድን የማሳደግ ሽግግር ውስጥ ደግሞ የወቅቱ አሰልጣኞች ዓይን ውስጥ የገቡ በርከት ያሉ ታዳጊዎች ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል ደግሞ ልባም፣ ጠንካራ፣ ፈጣን፣ መሸነፍን የማይወድ እና በእግርኳስ ክህሎቱ ወደፊት የተሻለ ደረጃ መድረስ የሚችል ተጫዋች ነበር። በቁመቱ ዘለግ ያለ ቢሆንም በጣም ቀጫጫ ከመሆኑ የተነሳ ብዙዎች ፍርሀት አድሮባቸዋል። “ይሄ ልጅ በቅጥነቱ የተነሳ ወደ ዋናው ቡድን አያድግ ይሆን ?” የሚል። በዚህም የተነሳ የሚሳሱለት አንዳንድ ጓደኞቹ ምክርም ይመክሩት ነበር። “በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ እንዲህ ያለ ሰውነት ይዘህ የትም አትደርስም። ብትችል የሰውነትህን ክብደት ለመጨምር እንዲረዳህ መድኃኒት ብትወስድ መልካም ነው” ይሉት ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ በነበረው የጨዋታ ዘይቤ አንድ ተጫዋች በተክለ ሰውነቱ ገዘፍ ያለ፣ ሰውነቱም ደንደን ያለ ቅድሚያ የመመረጡ ዕድል የሰፋ በመሆኑ ይመስላል። ይህ ቀጭን ጥበበኛ ተጫዋች አቅሙን ቀድመው የተረዱት እና በትክክል የቀድሞ ኮከብ ተጫዋቾች አልጋ ወራሽ እንደሚሆን እምነት የጣሉበት አንድ ታላቅ የእግርኳስ ሰው ነበሩ። ነፍሳቸውን ይማርና ማስተር ቴክኒሻን ሐጎስ ደስታ ናቸው። በታዳጊ ቡድን ያሳየውን መልካም እንቅስቃሴ ተመልክተው ወደ ዋናው ቡድን ያሳደጉት እግርኳሰኛ ደግሞ ኃይሉ አድማሱ (ቻይና) ይባላል።

ኃይሉ አድማሱ የተወለደው አዲስ አበባ ግንፍሌ ቀበሌ 10 ሜዳ አካባቢ ነው። በዚህ ሜዳ ከእርሱ በፊትም በእርሱም ጊዜ አሁንም ድረስ ብዙ ድንቅ ተጫዋቾች የፈሩበት ሜዳ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ እግርኳስ ብቻ ህይወቱ እንዲሆን ይመኝ የነበረው ኃይሉ ተመኝቶ አልቀረ በወቅቱ ለነበሩ በሠፈር ውስጥ “ሀኒ መዋለ ህፃናት” እና “ዩሮፓ ኮሚኒቲ” በሚባሉ ድርጅቶች ውስጥ የአካባቢው ልጆችን ሠብስቦ የሚያሰለጥኑ ወንድማማቾች (ኤርሚያስ ሙላቱ እና አስፋው ሙላቱ) እንዲሁም ቸርነት ተክሉ የሚባሉ አሰልጣኞች ስር እየሰሩ በተለያዩ ውድድሮች ይካፈሉ ነበር። በዚህ መሐል ነው በ1990 ኤልፓ ለመከራ በመሄድ በወቅቱ በአንድ ቀን ከተፈተኑ በርካታ ታዳጊዎች መካከል ኃይሉ አድማሱ ብቸኛ ተመራጭ ተጫዋች በመሆን የ “ሲ” ቡድኑን ተቀላቅሎ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኃላ ወደ ዋናው ቡድን በፍጥነት ያደገው። ባልተጠበቀ ሁኔታ በክለቡ ውስጥ በነበረው የሽግግር ጊዜ ወደ 12 ልጆች ወደ ዋናው ቡድን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ ለስድስት ዓመታት ጥሩ የሚባል ስኬታማ ዘመንን አሳልፏል። በመብራት ኃይል በቆየበት ዓመታት ውስጥ አይረሴው የ1993 ድል ውስጥ ጎል በማስቆጠር እና ለጎል የሚሆኑ ዕድሎችን በመፍጠር የነበረው ሚና ከፍተኛ ነበር። በኤልፓ ለተጨማሪ ዓመታት በመቆየት የሚወደውን ክለብ ለማገልገል ፍላጎት ቢኖረውም ከአሁኗ የትዳር አጋሩ ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ ጫና የተነሳ ከኤልፓ በመልቀቅ በ1997 ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርቶ ብዙም እንዳሰበው ሳይሆን ያላሰበው ሁኔታ ገጥሞት ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት እያለው በስምምነት ከቡና ጋር ተለያይቶ ወደ ሀዋሳ ከተማ አምርቷል።

ከታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በሚገርም ጥምረት አብሮት የተሳካ ጊዜያት ያሳለፈው ድንቁ ተጫዋች ዓለማየሁ ዲሳሳ (ዴልፒዬሮ) ስለ ኃይሉ አድማሱ ይሄን ይናገራል። “ቻይና ከታች ከ ሲ ቡድን ጀምሮ አብሮኝ የተጫወተ በሜዳም፣ ከሜዳ ውጭ በጣም የምንግባባ ወንድማማቾች ነን። አብረውኝ ከተጫወቱት በጣም ጎበዝ ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ እርሱ ነው። ከእርሱ ጋር በመጫወቴ ራሴን እንደ እድለኛ አድርጌ እቆጥራለው። በጣም ተግባብተን እስከፈለግነው ድረስ ተቀባብለን የምንጫወት፣ በጣም ቴክኒሻን የሆነ ተጫዋች ነው። ጎል ያስቆጥራል፣ ለጎል የሚሆን ኳስ ያቀብላል፣ ሜዳውን ሙሉ አካሎ የሚጫወት የማይደክመው፣ ጠንካራ የሆነ ኳስ ላይ የሚቀልድ ምርጥ ተጫዋች ነው።” ብሏል።

በሀዋሳ ከተማ ከ1998 –2002 ድረስ የተጫወተው ኃይሉ በቆይታው የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አሳክቶ ወደ ኢትዮጵያ ውሀ ሥራ በ2003 በማቅናት በታችኛው ዲቪዚዮን ከተጫወተ በኃላ ለሁለት ዓመት ራሱን ከእግርኳስ ዓለም አግልሎ በድጋሚ በ2007 ወደ እግርኳሱ በመመለስ ለአዲስ ከተማ እና የካ ክፍለ ከተማ ከተጫወተ በኃላ በመጨረሻ ዋዜማ የሚባል ቡድን እስከ 2008 መጨረሻ ድረስ እግርኳስን ሲጫወት ቆይቶ ጫማውን ሰቅሏል።

የኢትዮጵያ እግርኳስን በቅርብ ርቀት ከሚያውቁ እና ከሚከታተሉ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያር ስለ ኃይሉ አድማሱ እንዲህ ይናገራል። ” በዮርዳኖስ ጎሎች ከተክሌ ቀጥሎ የእርሱ ኳሶች አስተዋፆአቸው የጎላ ነበር። በግሉም ጎሎችን ያስቆጥር የነበረ ሲበዛ ኳስ የሚችል፣ በዛ ቅጥነቱ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን የሚወክል ስንቱን እያንከራተተ፣ እያስተኛ የሚያልፍ በጣም ኳስን የበላ ምርጥ ተጫዋች ነው። እንዲያውም የችሎታውን፣ የብቃቱን ያህል በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ያልገነነ፣ ያልተወራለት ተጫዋች ነው።”ይለዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ሥዩም አባተ ምርጫ በ1992 ሲሸልስ በተካሄደው ከ17 ዓመት የአፍሪካ ታዳጊዎች ቡድን ጀምሮ ጥሪ ቀርቦለት እስከ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ደረስ ተጫውቶ አሳልፏል። በአርጀንቲና ዓለም ዋንጫ በተሳተፈው የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካቶ አብሮ ቢጓዝም ምንም ዓይነት ጨዋታ ላይ ሳይሳተፍ ልምድ አግኝቶ እንደተመለሰ ይነገራል።

እግርኳስን ካቆመ በኃላ ወዲያው ወደ አሰልጣኝነቱ የገባ ሲሆን በአሴጋ ፕሮጀክት በማሰልጠን ወደ ሲዊድን በማቅናት ሀገሩን በመልካም ስም አስጠርቶ ተመልሷል። በመቀጠል ሀሌታ አካደሚው ውስጥ እስካሁን እየሰራ ሲገኝ ከ2010 ጀምሮ ወደ አሳዳጊ ክለቡ በመመለስ ያለውን ልምድ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በዋና አሰልጣኝነት እየሰራ ይገኛል።

ሌላኛው ከወርቃማዎቹ ትውልዶች መካከል አብሮት ከታችኛው ቡድን አንስቶ አብሮ የተጫወተው ዳንኤል (የሻው) ስለ ኃይሉ ይሄን ይናገራል። ” ኃይሉ እኛ ቻይና ነው የምንለው በጣም ጎበዝ፣ አስተዋይ፣ መፍጠን ሲፈልግ የሚፈጥን ተረጋግቶ መጫወት ሲፈልግ በጣም የሚረጋጋ፣ አጭርም ረጅም ኳስ የመጠቀም ችሎታ የነበረው። ከሜዳ ውጭ ብዙ አብረን ባንውልም ምክንያቱም ሮጦ ሄዶ ከቤተሰቡ እና ከፍቅረኛው ጋር ጊዜውን የሚያሳልፍ ጥሩ ስነ ምግባር ያለው ተጫዋች ነው” በማለት ይገልፀዋል።

በቤተሰብ ህይወቱ ለብዙዎች ምሳሌ በሚሆን መልኩ በኢትዮጵያ ተጫዋቾች እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ ከመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ አብራው ከነበረችው የያኔው ፍቅረኛው የአሁኗ የትዳር አጋሩ ጋር ሃያ ሁለት ዓመት በቆየው አብሮነታቸው ሦስት ልጆች አፍርተው በአዲስ አበባ መልካም የሚባል ህይወት እየኖረ ይገኛል። በዛሬው ድንቅ የዘጠናዎቹ ኮከብ አምዳችን እንግዳ ኃይሉ አድማሱ(ቻይና) ጋር ያደረግነው ቆይታ ይሄን ይመስላል።

“በእግርኳስ ተጫዋችነቴ ዘመን የምንም የሚፀፅተኝ ነገር የለም። እኔ በፍቅር የምወደው ነገር ኳስ ነው። ለእኔ እግርኳስ ጨዋታ ህይወት ነው። ልክ እንደምተነፍሰው አየር፣ እንደ ልጆቼ ፣ እንደ ባለቤቴ፣ እንደ ቤተሰቦቼ በዚህ ደረጃ የማየው ነው። ለእግርኳስ ሁሉ ነገሬን ነው የሰጠሁት ፈጣሪ ፈቅዶ ከልጅነቴ ጀምሮ ስወደው፣ ስመኘው የመጣሁበትን ነገር ነው ያገኘሁት። ተጫዋች በነበርኩበት አስራ ሰባት ዓመታት ውስጥ ኳስን እስክጠግበው ድረስ ተጫውቻለው። ቅር የሚለኝ፣ የሚፀፅተኝ ይህ ቀረ የምለው የሚቆጨኝ ነገር የለም። የሚቆጨኝ ነገር ቢኖር ኖሮ እግርኳስን መጫወትን እየወደድኩት፣ እየፈለኩት ተጫዋች ሳልሆን ብቀር ኖሮ እፀፀት ነበር። በዕድሜዬ ማድረግ የሚገባኝ ነገር ሁሉ ለኳስ ጨዋታ አድርጌአለው። እንደ ፈጣሪ ፍቃድ ከዚህም በኋላ ባለው እድሜዬም ከኳስ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ስራዬ ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም።

“ነፍሱን ይማረው ጋሽ ሐጎስ ደስታ ለእኔ በእግርኳስ ህይወቴ ትልቅ ባለሙያ ነው። የሰውነቴ መቅጠን (ቀጭን) ሳይሆን ኳስ እና ኳስን ብቻ መሠረት አድርጎ የሚያሰለጥን ሰው በማግኘቴ እድለኛ ነኝ። እኔ ያየውን የቴክኒካል አቅም ብቻ እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። አቅሜን አውቆ ተረድቶኝ በመንከባከብ እና በጣም በማበረታታት ትልቅ ኃላፊነቶችን በመስጠት እንድጫወት ያደረገኝ ጋሽ ሀጎስ ነው። እርሱ ባይኖር ኖሮ ማንም አይረዳኝም፣ አሁንም ላለሁበት ቦታ ላልገኝ እችላለው። የትም ክለብ መጫወት አይደለም መብራት ኃይል እራሱ ቢሆን ጋሽ ሀጎስ ባይኖር አልጫወትም ነበር። ልበ ሙሉነቴን፣ የትኛውም ቦታ ገብቼ መጫወት እንደምችል፣ ሁሌ ማሸነፍ የሚለው ተነሳሽነት ውስጤ እንዳለ ያወቀው እርሱ በመሆኑ እና ያለኝን አቅም ባይረዳ ኖሮ እዚህ ደረጃ ለመድረስ እቸገር ነበር። እርሱን ካጣን በኃላ የሚረዳኝ አሰልጣኝ በማጣት አንዳንድ የእግርኳስ ህይወቴን አስቸጋሪ የሚያደርጉ ነገሮች አጋጥመውኝ ነበር። ጋሽ ሀጎስ ቀድሞ የኖረ፣ ያለ ጊዜው የነቃ ትልቅ አሰልጣኝ ነበር።

” የትላልቅ ተጫዋቾችን መተካቱ ቀላል የሚባል ኃላፊነት አልነበረም። መብራት ኃይል የራሱ የሆነ ባህሪ የነበረው ቡድን ነው። አቅም ኖሮህ ይህ ልጅ ወደ ላይ ይደግ ተብሎ ሲታሰብ ታድጋለህ ምንም ጥያቄ የለውም። በዋናው ቡድን የመጫወት እድል ብታጣ እንኳን ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለህ ልምድ የምታገኝነት መንግድ በጣም አሪፍ ነው። ከታች ወደ ላይ ያለው ፍሰት አሁን በአውሮፓ ያሉ የሊጉ ቡድኖች ያለው አደረጃጀት ነው እንጂ ብዙ በሀገራችን አልተለመደም። ክለቡ በአንዴ በርከት ያሉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ቀንሶ ወደ ዋናው ቡድን መጫወት አይደለም። እንዴት ብዬ ስታዲየም ገብቼ ሲጫወቱ ከማያቸው ድንቅ ተጫዋቾች ጋር አብሬ ልምምድ ልስራ፣ አብሬ በሰርቪስ ልሂድ ብዬ ፈርቼ እቀር ነበር። ጋሽ ሀጎስ ነው የቀረሁበትን ምክንያት አውቆ በአንዋር ያሲን፣ ኤልያስ ጁሀር እና አፈወርቅ ኪሮስ ባሉበት መሐል ባልገባ ተጫወት እያለ በውስጤ የነበረውን ፍርሀት ለማውጣት ሞክሯል። ይህን በማድረጉ ተሳክቶለት መጫወት ችያለው። በኃላም ክለቡ ኃላፊነት የሚወስድ መሆኑ ለምሳሌ እኔ ኤልያስ ጁሀር ተቀንሶ በእርሱ ቦታ የገባሁት እኔ ነኝ በጊዜው ይህን መወሰን በጣም ከባድ ቢሆንም ጋሽ ሀጎስ ለሚመጣው ማንኛውም ነገር እኛን በማምጣቱ ኃላፊነት ወስዶ አጫወተን እኛም አላሳፈርነውም። የተሰጠንን እድሎች ተጠቅመን በ1992 ላይ ለዋንጫ ተፎካክረን በተወሰ ነጥብ አንሰን ሁለተኛ ሆነን ጨረስን በመቀጠል በ1993 ግን በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም ዋንጫዎች ሰብስበን አነሳን። ይህ የሚያሳየው ጋሽ ሀጎስ ኃላፊነት ወሰዶ እኛም ቀላል የማይባል ጊዜ አሳልፈን በራስ መተማመናችን(የይቻላል)።መንፈስ አዳብረን ያንን ስኬት አሳክተናል። በዚህ ዘመን ኃላፊነት የሚወስድ አሰልጣኝ(ሰው) ስለሌለ ይመስለኛል። በሊጋችን አዳዲስ ልጆችን ማየት ያልቻልነው።

“የ1993 የመብራት ኃይል ስኬት ሚስጢሩ አንደኛ አብዛኛው ልጆች በአንድ እድሜ ላይ መገኘታችን፣ ሁለተኛ ትልቁ አንዋር ወጥቶ ተክሌ ብርሀኔ የመጣበት ሽግግር ያ ማለት በአንዋር አቅም እና ችሎታ ተቀራራቢ የሆነ ሰው መተካቱ ሦስተኛው ከታች የመጣነው የሚነገረንን በመስማት ለመለወጥ የነበረን ተነሳሽነት፣ ለሙያው የነበረን ዲሰፒሊንድ፣ ለቡድን ስራ ትኩረት እንሰጥ የነበረ በመሆኑ እና በጣም መከባበራችን አንድ ላይ ማደጋችን እንዲሁም ከወገብ በላይ የነበርን ተጫዋቾች ሁላችንም ጎል እናስቆጥር ነበር። ለምሳሌ ዮርዳኖስ ዐባይ 24 ጎል፣ እኔ ከ10 በላይ ጎል፣ አለማየሁ ዲሳሳ(ዴልፔሮ) በተመሳሳይ፣ መስፍን ደምሴ(ድክሬ) ፣ ያሬድ፣ ተክሌ ብርሀኔ ሁላችንም ከተለያዮ አቅጣጫዎች ጎል የሚያስቆጥር እና ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ የምናቀብል የነበረ በመሆኑ ስኬታማ አድርጎናል። መብራት ኃይል ህልማችንን የኖርንበት ትልቅ ቤት ነው።

“እንደነበረኝ አቅም እና ችሎታ ብዙ አልተነገረልህም ላልከኝ እንደ ተመልካቹ ዕይታ ነው የሚወሰነው። የኔን እንቅስቃሴ የሚረዳ ሊያደንቅ የሚችል ሰው አለ ዮርዳኖስ የሚል ሰው አለ እኔን የሚል ሰው አለ ይሄን ለሰዉ መተው ነው የምንችለው።

“ከመብራት ኃይል ከወጣው በኃላ ቡና የነበረኝ ቆይታ ጥሩ አልነበረም። እንዳሰብኩት አልሆነም። ምክንያቱ ደግሞ ኤልፓ እያለው ትከበራለህ፣ ያደክበት ቤት ስለሆነ ኃላፊነት ይሰጥሀል፣ እፈለግ ነበር። ቡና ስትመጣ ገና አዲስ ቤት ነው እስክትላመድ፣ የቤቱን ባህሪ እስክትለምድ ድረስ ትንሽ ተቸግሬ ነበር። እንዲሁም እኔ ከፈረምኩ በኃላ ነው አብርሀም ተክለ ሀይማኖት የመጣው ከአብርሀም ጋር ልንግባባ አልቻልንም። በተለያዮ መድረኮች አሰልጣኝ አብርሀም እንደ ቻይና የምወደው ተጫዋች የለም ይላል ግን ልንግባባ አልቻልንም። አርሱ የሚፈልገው እና እኔ የማስበው ምንም ሊገናኝ አልቻልንም። ያለኝን ነገር ሊረዳ አልቻለም። ገና ከዝግጅት ጀምሮ በዝግጅት ወቅት በሁለታችን መሐል የተፈጠረው ግጭት የታሰበውን ያህል ጥሩ ጊዜ ሳላሳልፍ እንድቆይ አድርጎኛል። አብርሀም ቡናን ለቆ ሥዮም አባተ ለተወሰኑ ጨዋታ ሲመጣ የተወሰነ ጨዋታዎች ተጫውቼ በመጨረሻ ብዙም መቆየት ስላልፈለኩ ኮንትራቴ ሳያበቃ በሰሰምምነት ቡናን ለቅቄ ወደ ሀዋሳ ያመራሁት።

” ከለመድኩት ቤት ወጥቼ ወደ ቡና መሔዴ ብዙ ነገር ነው ያጣሁት ብዙ ደስተኛ አልነበርኩም። መብራት ኃይል ተፈላጊ ተጫዋች ነበርኩኝ ቡና ስመጣ ግን አልተመቸኝም ከአሰልጣኙ ጋር ልንግባባ አልቻልንም ቡና ጥሩ ቤት ነው።
ያጎደለብኝ ነገር የለም። ሆኖም ግን ለእኔ የሚሆን የሚያቀኝን ሰው አለማግኘቴ።ለጊዜው ችግር ፈጥሮብኛል። ኤልፓን ለቅቄ ቡና መግባቴ እድገቴን በተወሰነ መልኩ ጎድቶታል። ያው አንዳንዴ በወሰንከው ውሳኔ በኃላ አንዳንዴ ትተላለፋለህ በዚህም ተጫዋች ይጎዳል ምንም ጥያቄ የለውም። ሀዋሳ በነበረኝ አምስት ዓመት ቆይታዬ ግን በጣም ደስተኛ ነበርኩ ጋሽ ከማል፣ አዲሴ ካሴ፣ ከሌሎቹም የቡድን አጋሮቼ ጋር ጥሩ ጊዜ አሳሌፌያለው።

” እግርኳስን እንዳቆምኩ ከፍተኛ ፍላጎት ያለኝ በመሆኑ ወደ አሰልጣኝነቱ ወድያውኑ ነበር የገባሁት። ኮርሶችን ግን አልወሰድኩም። ይህ የሆነበት ምክንያት የ “ሲ” ላይሰንስ ስልጠናውን ልወስድ በተቃረብኩበት ሰዓት ላይሰንሱን መስጠት በፌዴሬሽኑ በመቆሙ ምክንያት ነው። ይህው አራት ዓመት ሆኖታል ላይሰንሱን መስጠት ፌዴሬሽኑ ከቆመ እኔ ግን እየሰራው ነው። የአሰግድ አሴጋ ፕሮጀክት በማሰልጠን ጀምሬ በኃላ በሀሌታ አካዳሚ በመግባት ሠርቻለው። ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ በኢትዮ ኤሌትሪክ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በዋና አሰልጣኝነት እየሰራው እገኛለው። ከዚህ በተረፈ እኔ አብይ፣ ራውዳ አሊ የከፈትነው ሀሌታ የሚባል አካዳሚ አለን አብረን የምንመራው ከሀሌታ ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩኝ እገኛለው። በአጠቃላይ በአሰልጣኝነት ህይወቴ ደስተኛ ነኝ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩኝ ነው። ከፊት ለፊቴ መልካም እና በጎ ነገሮች አሉ ብዬ አስባለው። ራሴን ብቁ አሰልጣኝ ለማድረግ እየተዘጋጀው ነው። መጫወት እንዳለ ሆኖ ስልጠና ምን ይፈልጋል የሚለውን ለማወቅ እየጣርኩ እገኛለው። ስለ ተጫወትክ ብቻ አሰልጣኝ አትሆንም መጫወቱ ጠቀሜታ ቢኖሮውም ትምህርቶችን መውሰድ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለው። ብዙ ነገሮቼን የማሳልፈው እራሴን ለማብቃት በመሞከር ነው። ከኤልፓ ጋር የታዳጊ ቡድኑን እየሰራው በጎን ደግሞ ሀሌታ እሰራለው። ከ7–14 ዓመት ታዳጊዎች የሚካፈሉበት በሀሌታ ጎጃ ካፕ የሚባል ዓመታዊ ውድድር አለ ሲዊዲን ድረስ በመሄድ እየተካፈልን እንገኛለን።

” ቻይና የሚለውን ቅፅል ስም ያወጡልኝ የኛ ጎረቤት የነበሩ አንድ እናት ናቸው። ስወለድ ዐይኔ ትናንሽ ስለነበረ ይሄ ልጅ ቻይና ነው አሉኝ። ቻይና ተብሎ ቅፅል ስሜ ቀርቷል። እኔ በተወለድኩበት ብዙ ቻይናዎች ሀገራችን ውስጥ እንደዛሬው በብዛት አልነበሩም። ሆኖም ወደፊት የሚሆነውን ቀድመው ተረድተው መስለኝ ቻይና ብለው ያወጡልኝ።

“የአርጄንቲና የወጣቶች ዓለም ዋንጫ ላይ ለብሔራዊ ቡድን በጨዋታ ተሳትፎ አለማድረጌ ምክንያቱ ምን መሰለህ አሰልጣኝ ጋርዚያቱ ከዚህ ገና ሳንሄድ ሁሌም ምን ይለኝ ነበር። “አንተን ወደ አርጄንቲና የምወስድህ ካሉኝ ስብስቦች በእድሜ ትንሹ ነህ። ወደፊት ብዙ ትጫወታለህ አርጄንቲና ይዤህ የምሄደው ልምድ እንድታገኝ ነው ይለኛል”። እውነትም በዛን ጊዜ ከነበረው ስብስብ በጠቅላላ ልጅም የነበርኩት እኔ ነኝ አብዛኛው በዚህ ብሔራዊ ቡድን የነበሩት ሲጫወቱ ቁጭ ብዬ ስመለከታቸው የነበሩ ናቸው። በአርጄንቲና በነበረው ቡድን ውስጥ መጫወት ባልችልም በመኖሬ ግን ብዙ ነገር አውቄ ተመልሼበታለው።

” ለኔ በአሰልጣኝነት ዘመኔ የምፈልገው የጨዋታ ፍልስፍናዬ መነሻ የሚሆኑት ልጆቼ ናቸው። ልጆቼ ደግሞ ሀገር ናቸው። እነርሱ ምን አላቸው ከሚለው አስባለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በየትኛውም አቅጣጫ በትሄድ መነሻ የሚሆነው ታለንት ነው። እነዚህ ልጆች ደግሞ ራሳቸውን የሚገልፁበት መንገድ ምድነው ብለህ ስትጠይቅ ኳስን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴዎች የተሻለ ነው ብዬ የማስበው። በዚህ ውስጥ ማደግ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አለ ብዬ አምናለው። እኔ የመጣሁበት መንገድ አለ ከአሰለጠኑኝ ሰዎች የወሰደድኩት ነገር አለ፣ በመጫወት ውስጥ ያተረፍኩት ነገር አለ፣ አሁን ደግሞ በጊዜ ሂደት የተማርኩት ነገር አለ። እነርሱን እየቀላቀልኩኝ በጣም ፈጠን ያለ ኳስን መሠረት ያደረገ፣ ቶሎ ቶሎ የሚያጠቃ ቡድን መስራት ነው የምፈልገው። ይህን ደግሞ በተወሰነ መልኩ ይሄን እያደረኩት እገኛለው።

” የቤተሰብ ህይወቴ በጣም ረጅም ታሪክ ያለው ነው። ከአሁኗ ባለቤቴ ጋር ኤልፓ ሲ እያለው በትምህርት ቤት ውስጥ ነው የተዋወቅነው ነው። አሁን ወደ ሀያ ሁለት ዓመት ሆኖናል ማለት ነው። እኔ በእግርኳስ ህይወቴ መደበቅ አልፈልግም። መደበቅ አልፈልግም ማለት የተለየ ሆኜ አይደለም። እኛ ሀገር ብዙ አልተለመደም ካፌም ፣ ቲያትርም ስሄድ ይዣት እሄዳለው። ከጨዋታ በኋላ ከልምምድም በኃላ ሮጬ የምሄደው እርሷ ጋር ነው። ስታዲየም መጥታ ኳስ ትመለከታለች። ከእርሷ ጋር በማሳልፈው አብዛኛው ጊዜ የተነሳ በእግርኳስ ተጫዋችነቴ ብዙ ፈተና መጥቶብኛል። ከመብራት ኃይል የወጣሁበትም ምክንያት ይሄ ነው። በእኔ እና በርሷ መካከል ያለው ግኑኝነት ሰው አይረዳም። ብዙ ሰው የሚያስበው ዱሩዬነት ብልግና ነው ብሎ የሚያስበው። እውነተው ግን ይሄ አይደለም። እኔ ደግሞ እንደማገባት በእርግጠኝነት አውቅ ነበር። በንፁሁነት ገና በልጅነት ነው የተገናኘነው። በጣም ትረዳኝ ነበር ኳስ እንድጫወት ትፈልግ ነበር። በጣም የማችስተር ዮናይትድ ደጋፊ ነበረች። የኤሪክ ካንቶና በጣም አድናቂው ነች እንዲያውም የእርሱ ፊርማ ያረፈበት የተላከላት ፎቶ አለ ለኔ በስጦታ የሰጠችኝ አለ። እርሷ ለኳሱ ቅርብ ስለነበረች ትልቅ ተጫዋች እንድሆን ትመኝ ስለነበረ በብዙ ደረጃ ታግዘኝ ነበር። በዚህ ረገድ ድብቅ ሳልሆን ቤተሰቦቼ እያወቁ ነበር አብሬት እሆን የነበረው። ሆኖም በእግርኳስ ህይወቴ ጫነው እየበረታ መጥቶብኛል። እንዲያውም የሆነ ቦታ ላይ ፀጋዘአብ በዘጠና መጀመርያ አካባቢ በሠርግ አግብቶ ፕሮግራሙ ላይ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው። “እኔ የፍቅር ጓደኛዬን ይዤ ለመዞር ሀምሳ አመት ነው የፈጀብኝ፣ አንተ ግን ዛሬ ይዘህ ትመጣለህ እኛንም ታስጨቀጭቀናለህ” ያለኝን አረሳም። ያው እኔ እውነተኛ ነገር ስለነበረኝ አልደበቅም ነበር። እንዲሁ አንድ ቀን የሆነውን ላጫውትህ ኤርሚያስ ተፈሪ መሰለኝ ሰብስቦን ስለ ቡድን እንቅስቃሴ ካወራን በኋላ እስቲ ከእናተ መሐል የፍቅር ጓደኛ ያለው ተብሎ ተጠየቀ ዳንኤል የሻው፣ ዮናስ ገ/ሚካኤል ሁሉም ሲጠየቁ የለኝም እያሉ መለሱ፣ እኔ ግን እንዳላቸው አውቃለው። እኔ ጋር ሲደርስ አለኝ አልኩኝ አለማየሁ (ዴልፒዬሮም) አለኝ አለ በቃ እናተ አስቸገራቹ ተብሎ ተቀወጠ ያው እኛ ሀገር ስላልተለመደ ነው። ሌላ ሀገር ከፍ ስትል ሀላፊነት እየተሰማህ እንዲመጣ ይደረጋል በወቅቱ የወሰንኩት ውሳኔ ተገቢ ነበር። የእግርኳስ ህይወት አጭር ነው። ያንን ውሳኔ አምኜ በመሄደ እነዚህን የመሰሉ ልጆች እና ይህን የመሰለ የትዳር ህይወት አላገኝም ነበር። በይሉታ ሰዎችን ለማስደሰት ትቼው ብሆን ኖሮ ለኔ ከባድ ነበር። ዘ ሬ ግን በጣም ደስተኛ ሙሉ ሰው ሆኛለው።

” ባለቤቴ መዐዓዛ ምንዳዬ ትባላለች። በህይወቴ ደስተኛ ነኝ። እርሷ ሦስት ቆንጆ የሆኑ ልጆች አግኝቻለው። የመጀመርያ ልጄ ሀይከን ኃይሉ ትባላለች አስራ ሦስት ዓመት ሆኗቷል፣ ሁለተኛ ልጄ ክረስቲያን ኃይሉ ዘጠኝ ዓመቱ ሆኗል። የመጨረሻ ልጄ አትናሲያ ትባላለች አምስት አመቷ ነው። ወንዱ ልጄ በጣም እግርኳስ ይወዳል። ከእኔ ጋር ሀሌታ አካዳሚ እየሰራ ነው። እኔም ኳስ ተጫዋች ቢሆን ደስታዬ ነው። ምክንያቱም በኳስ ውስጥ ብዙ ነገሮችን አሳልፌያለው። ኳስ ስትጫወት የመጀመርያ የሚሆነው ጤነኝነት ነው። በመቀጠል ስሜቶችህን ፍላጎቶችህን ሳትናገር የምትጫወተው ነው ኳስ ጨዋታ ስለዚህ ስሜቱ አለው እየተጫወተ ነው።

“አሁን ያለው የኢትዮጵያ እግርኳስ በብዙ መልኩ ተቀይሯል። ጥሩ ጥሩ ነገሮች አሉ ተጫዋች ተከብሯል፣ ጥሩ ክፍያ ያገኛሉ። የዛኑ ያህል በእግርኳሱ ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች አሉ በአጠቃላይ በሁሉም በኩሉ ያሉ ባለድርሻ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና አመራሮች ሌሎችንም ጨምሮ በሙሉ እግርኳሱ ከፍ እንዲል ማድረግ እንዲቻል፣ ለእድገቱ ልንሰራ ይገባል።

“ለእኔ እዚህ መድረስ የማመሰግናቸው ሰዎች አሉ ወንድሜን ዓለማየሁ አድማሱ፣ እናቴን፣ ወንድሞቼን፣ ባለቤቴን ቤተሰቦቼን በጣም አመሰግናለሁ። አሁን በዙርያዬ እየሰሩ ያሉት ዐቢይ ካሣሁን፣ ራውዳ ዓሊ፣ ወደ ኤልፓ ስመጣ ደግሞ በጣም ትልቅ ሀሳብ ያለው፣ ለባለሙያ የሚመች ፣ ያለ ምንም ስበብ፣ መደናቀፍ በነፃነት እንዲሰራ ለባለሙያ መልካም የስራ መንገዶችን የሚፈጥር በጣም የማከብረው ትልቅ ሰው አቶ ኢሳይያስ ደንድርን ማመስገን እፈልጋለሁ። በአጠቃላይ የጠራኋቸው ያልጠራዋቸው ብዙ ሰዎች አሉ፤ ለኔ እዚህ መድረስ በጣም የማመሰግናቸው ሰዎች። እና አጠቃላይ አመሰግናለሁ።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!