“ጠንክረን ከሰራን ያሰብንበት እንደርሳለን” ተስፈኛው አጥቂ አቤል ነጋሽ

በመከላከያ ከታዳጊ ቡድን አንስቶ በየዓመቱ በሚያሳየው ተከታታይ እድገት አቅሙን በማሳየት ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለው ተስፋኛው አጥቂ አቤል ነጋሽ የዛሬው ተስፈኞች አምዳችን እንግዳ ነው።

በ2009 በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ውድድር ወቅት በኢትዮጵያ ቡናው ተመስገን ዘውዴ በጥቂት ጎሎች ተቀድሞ ሁለተኛ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል። ከ17 እና 20 ዓመት በታች የዕድሜ እርከን ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ለአራት ዓመት መጫወት ችሏል። በ2011 ዩጋንዳ ላይ በተካሄደው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባደረገው በሦስት የምድብ ጨዋታ ላይ በመሳተፍ ሀገሩን አገልግሏል። በ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ በትልቅ ደረጃ መከላከያ ከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ቡድኑን አቻ ያደረገበትን የመጀመርያ ጎሉን አስቆጥሯል። እልህኛ መሆኑ፣ ተከላካዮችን እንዳያስቡ እረፍት በመንሳት፣ ከኳስ እና ከኳስም ውጭ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ እንዲሁም በጎል አጨራረስ ብቃቱ ይታወቃል። የዛሬው የተስፈኛ አምዳችን እንግዳ የሆነው ወጣቱ አጥቂ አቤል ነጋሽ…

በቢሸፍቱ ከተማ ቀበሌ 13 የተወለደው አቤል በሞዴል ትምህርት ቤት ውስጥ በአሰልጣኝ ኤልያስ የሚሰለጥኑ የታዳጊ ቡድኖች ውስጥ ታቅፎ እየሰለጠነ አድጓል። በኃላም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት መከላከያ ያወጣውን ከ17 ዓመት በታች ታዳጊ ቡድን የምልመላ ፈተናውን በሚገባ በማለፍ በ2008 የቡድኑ አባል በመሆን የእግርኳስ ህይወቱን በክለብ ታቅፎ መምራት ጀምሯል። ለሁለት ዓመት ከ17 ዓመት በታች ቡድን ከተጫወተ በኃላ በ2010 ከ20 ዓመት በታች (ተስፋ ቡድን) አድጎ ባሳለፍነው ዓመት በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ምርጫ ወደ ዋናው ቡድን በማደግ በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ለሆነው መከላከያ በጥሩ ሁኔታ እያገለገለ ይገኛል። አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታ፣ ወደፊት ራሱን በተሻለ ሁኔታ አሳድጎ ትልቅ ተጫዋች ስለማድረግ ህልሙ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ አጋርቷል።

“በኮሮና ምክንያት ውድድሮች ቢቋረጡም ከእንቅስቃሴ አልወጣሁም፤ ልምምዶችን እየሰራው እገኛለው። እንዲያውም የስፖርት ማዘውተርያ መከፈቱ አሁን በደንብ ተሰባስበን እየሰራን ነው። ለኛ ከታች ቡድን ላደግን ልጆች በከፍተኛ ሊግ የመጫወት እድል አግኝተን ጥሩ የውድድር ጊዜ እያሳለፍን ነበር። ሆኖም ኮሮና ብዙ ነገሮችን አበላሽቶብናል። ያም ቢሆን ዘንድሮ አሳዳጊ ክለቤን መከላከያን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ። ለዚህም ጠንክሬ እየሰራሁ ነው። አንድ አጥቂ አጥቂ ለመባል መለኪያው በዋናነት ጎል ማግባት አለበት። ይህንም ለማሟላት የምችለውን ያህል እየሰራሁ ነው። ከዚህ በተረፈ በብሔራዊ ቡድን እና ከኢትዮጵያ ውጭ ወጥቼ መጫወት እፈልጋለው። የመጫወት እድል እስክናገኝ ድረስ ብዙ ውጣ ውረዶች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን ቶሎ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም። የሚመጡትን ፈተናዎች መቋቋም ይገባል። ወጥረን በመስራት ያሰብንበት እንደርሳለን እላለሁ። እንዲያውም በአሁኑ ሰዓት ክለቦቻችን ለታዳጊዎች እድል እየሰጡ ነው። ይህን አጋጣሚ ደግሞ ሳንዘናጋ መጠቀም የኛ ፈንታ ነው። መከላከያ ደግሞ በታዳጊዎች የሚያምን እና ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ በጣም አመሰግናለሁ። እዚህ ደረጃ ለመድረሴ ፈጣሪን አመሰግናለሁ። በመቀጠል አሰልጣኝ ኤልያስን፣ ቤተሰቦቼን እና የሰፈር ጓደኞቼን ማመስገን እፈልጋለሁ። እነርሱ ናቸው እያበረታቱ፣ ትጥቆችን እያሟሉ እዚህ ያደረሱኝ። ከሀገር ውስጥ ተጫዋቾች የምንይሉ ወንድሙ አድናቂ ነኝ። የእርሱ የአጥቂ ባህሪን እኔም ተላብሼ መጫወት እፈልጋለሁ።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!