አዳማ ከተማ የእግድ ውሳኔ ተላለፈበት

ከዚህ ቀደም ከፌዴሬሽኑ ግልጋሎት እንዳያገኝ እግድ ተጥሎበት የነበረው አዳማ ከተማ በተመሳሳይ ክስ ዳግም የእግድ ውሳኔ ተላልፎበታል።

የቀድሞው የአውሥኮድ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ አጥቂ የነበረው አብዱልሀኪም ሱልጣን አዳማ ከተማን ለሁለት ዓመታት ለማገልገል 2009 ላይ ተቀላቅሎ ነበር። ይህ የአጥቂ እና የመስመር ተጫዋች በወቅቱ በገባበት አመት እየተጫወተ እያለ ጉዳትን በማስተናገዱ ለስምንት ወራት ያህል ከሜዳ ለመራቅ ይገደዳል። ይሁን እና ተጫዋቹ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እያለ አዳማ ከተማዎች ቀሪ የውል ኮንትራት እያለው ከክለቡ እንዲሰናበት አድርገውታል። ከዛም ተጫዋቹ “ኮንትራት አለኝ። በተጨማሪም አሁን ጤናማ ነኝ።” በማለት ወደ ክለቡ ልመለስ ቢልም ክለቡ የተጫዋቹን ጥያቄ ወደ ጎን በማለት ውሳኔውን ያፀናል፡፡

ይህንን የክለቡን ውሳኔ ተከትሎ ተጫዋቹ “ያለፉትን ሁለት ዓመታት ውል እያለኝ በመሰናበቴ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፍረደኝ” በሚል በተደጋጋሚ ወደ ፌዴሬሽኑ ቀርቦ ጥያቄውን ሲያቀርብ ነበር። ፌዴሬሽኑም ከወራቶች በፊት ‘ወደ ስራ ገበታው መልሱት፣ ካለበለዚያ የራሴን ውሳኔ እወስናለሁ።’ የሚል ትዕዛዝ ለክለቡ ያስተላልፋል። አዳማ ከተማም ጉዳዩን ተፈፃሚ አደርጋለሁ በሚል ከተጫዋቹ ጋር ከነበረው የውል ጊዜ ጥቂት ወራት በመቀነስ እንክፈልህ በማለት እንዲሁም ተጫዋቹ ከክለቡ የመጣውን ጥያቄ በመቀበል ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ከስምምነት የዘለለ ድርጊት አሁንም ክለቡ ባለመፈፀሙ ተጫዋቹ ከሰሞኑ ወደ ፌዴሬሽኑ በድጋሜ በመሄድ ጉዳዩ አለመፈፀሙን ገልጿል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ከዚህ ቀደም ለተጫዋቾቹ የደመወዝ ክፍያን ሳይፈፅሙ እግድ አስተላልፎባቸው የነበረውን አዳማ ከተማዎችን በድጋሜ በቀድሞ ተጫዋቻቸው ክስ ማገዱን አስታውቋል።

የእግድ ደብዳቤው ሙሉ ሀሳብ 👇

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!