የኢትዮጵያ ቡና እና የሐበሻ ቢራ ስምምነት ዝርዝር ጉዳዮች

ሐበሻ ቢራ ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብን ለተጨማሪ ዓመት ስፖንሰር ለማድረግ የሚያስቸለውን ስምምነት ዛሬ ፈፀመ።
ያለፉትን ስምንት ዓመታት በስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ከኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ጋር አጋር ሆኖ የዘለቀው ሐበሻ ቢራ ከክለቡ ጋር ያለውን ውል ለአንድ ዓመት አራዝሟል። ዛሬ ከሰዓት በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል በተዘጋጀው የፊርማ እና ጋዜጣዊ መግለጫ መርሐ-ግብር ላይ ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብን ወክለው አቶ ሚኒሊክ እና አቶ ገዛኸኝ ሲገኙ በሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማኀበር በኩል ደግሞ ወ/ሮ አፌን እና አቶ ክንፈ ተገኝተዋል። በቅድሚያም ሁለቱን አካላት ወክለው የተገኙት አቶ ገዛኸኝ እና ወ/ሮ አፌን ስምምነቱን በይፋ በመፈራረም ፈፅመዋል።

የፊርማ ስምምነቱ ከተከናወነ በኋላ ስምምነቱ በውስጡ የያዙት ዝርዝሮች ጉዳዮች አቶ ገዛኸኝ ገለፃ ማድረግ ጀምረዋል። በስምንት አንቀፆች በተዘረዘረው ውል ላይ የሚከተሉት ክፍያዎች በሀበሻ ቢራ እንደሚፈፀሙም ተገልጿል።

– ከሐምሌ 1 2012 – ሰኔ 30 2013 በሚቆየው ውል ላይ ሀበሻ ቢራ 18 ሚሊዮን ብር ለክለቡ በቀጥታ ይከፍላል።

– በተጨማሪ ሀበሻ ቢራ ቡና በተጠቀሰው አንድ ዓመት ውስጥ ለሚያከናውናቸው የተለያዩ አራት ዝግጅቶች ለእያንዳንዳቸው 500 ሺህ ብር በድምሩ 2 ሚሊዮን ብር ይከፍላል።

– ክለቡ ለ2013 ለደጋፊዎች ለሚያሰራው ደረጃውን የጠበቀ መለያ 4 ሚሊዮን 500 ሺህ ይሰጣል ( ይህ ክለቡ መለያዎችን ሸጦ ከሚያገኘው ገንዘብ ውጪ ነው)።

– ተቋሙ ለ2013 የቡና ቤተሰብ የሩጫ ውድድር 3 ሚሊየን 750 ሺህ ብር ይሰጣል።

በአጠቃላይ 28.25 ሚሊየን ብር ሀበሻ ቢራ በተጠቀሰው የአንድ ዓመት ቆይታ ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ስፖርት ክለብ ይሰጣል። በተጨማሪም

– ቡድኑ የሊጉ ቻምፒዮን ከሆነ ለተጫዋቾች 2.7 ሚሊየን ብር በሁለተኝነት ካጠናቀቀ ደግሞ 900 ሺህ ብር በሽልማት መልክ ያበረክታል።

– በሊጉ በሚደረጉ ጨዋታዎች ቡድኑ ሲያሸንፍ ለተጫዋቾች ተነሳሽነትን ለመፍጠር በሜዳው ሲጫወት በተጫዋች ከ6000-8000 እንዲሁም ከሜዳው ውጪ ከሆነ ደግሞ 7000-8000 ክፍያ ይፈፅማል። ከዚህ በተጨማሪም የማበረታቻ ሽልማቱ በጨዋታው በተቆጠሩ ግቦች ጭምር የተዘረዘረ ነው።

የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ከውሉ ጋር የተገናኙትን ዋና ዋና ነጥቦች ካብራሩ በኋላ ተከታዮን ሀሳብ አጋርተዋል።

“የውሉ ስምምነት በፊትም የተጠናቀቀ ነው ፤ የሊጉ ጉዳይ ዕልባት ያግኝ ብለን ነው ይፋ ለማድረግ የዘገየነው። ከሐበሻ ቢራ፣ ከክለቡ እና ከደጋፊው የተውጣጣ የሦስትዮሽ ኮሚቴም አዋቅረናል። ኮሚቴው በሒደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን እያየ መፍትሄ የሚሰጠን ይሆናል።

“በቀጣይ ውሉን ለአምስት ዓመታት ለማድረግ አስበናል። ይህንንም በመጪዎቹ ስድስት ወራት ተወያይተን የምናሳውቅ ይሆናል።

“በዋናነት የሀበሻ ቢራን አርማ በቡድኑ መለያ ላይ የምናስተዋውቅ ይሆናል። በተጨማሪም ክለቡ ራሱን ለማጠናከር በሚያዘጋጃቸው መርሐ-ግብሮች ላይም የሐበሻን የንግድ ምልክት በስፋት እናስተዋውቃለን።

“ሐበሻ ቢራ ዋነኛ ስፖንሰራችን ቢሆንም ራሳችንን ይበልጥ ለማጠናከር ሌሎች ድርጅቶችንም ለስፖንሰርሺፕነት እየጠየቅን ነው። ሀበሻ በመለያው ፊት ለፊት ባለው ቦታ መተዋወቁ እንዳለ ሆኖ እሱን በማይጋፋ መልኩ በመለያው እጅጌ እና ሌሎች ክፍት ቦታዎች ላይ ተጨማሪ ድርጅቶችን ለማስተዋወቅ እየሠራን ነው። ግን ድርጅቶቹ ከሐበሻ ዓይነት ምርት ውጪ መሆን አለባቸው።

“ስፖንሰርሺፑ ለፅድቅ አይደለም ፤ ለጋራ ተጠቃሚነት እንጂ። ስለዚህ ደጋፊዎቻችን የሐበሻን ምርት ከመጠቀም ጀምሮ በየሄዱበት የድርጅቱን ስም በማስተዋወቅ ረገድ ሊረዱን ይገባል።

የስምምነቱን ዝርዝር አቶ ገዛኸኝ በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች አስረድተው ሃሳባቸውን ከሰነዘሩ በኋላ የሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ማርኬቲንግ ማኔጀር የሆኑት ወ/ሮ አፌን ስለተቋማቸው እና ስለስምምነቱ በመቀጠል ገለፃ አድርገዋል።

“ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለን ግንኙነት ጠንከር ያለ ነው። እኛም እነሱን ለመደገፍ እንጥራለን እነሱም ተቋማችንን ወደፊት ለማሳደግ ይሠራሉ። ስለዚህ ስምምነቱ የጋራ ጥቅምን የሚያመጣ ነው።

“ሐበሻ ቢራ ከኢትዮጵያ ቡና ያገኘውን ነገር በቁጥር ማስቀመጥ ሊከብድ ይችላል። ግን በጣም ጠቅሞናል። እንደሚታወቀው ወደ ገበያው ከመግባታቸን በፊት ነበር ወደ ክለቡ የመጣነው። ወደ ምርት ከገባን በኋላም አሁን ድረስ ከክለቡ ጋር ነን። በዚህ ሒደት የክለቡ ደጋፊዎች ምርታችን እንዲተዋወቅ ትልቅ ስራ ሰርተዋል። ስለዚህ ወደ ገበያው በቶሎ እንድንገባ፣ ብራንዳችን እንዲተዋወቅ እንዲሁም የተሻለ ሽያጭ እንድናገኝ ደጋፊዎቹ ረድተውናል። ይህንን ብልም ግን የሁለታችንም ጥቅም ከዚህ በተሻለ ማደግ እና መሻሻል አለበት። ይህም እንዲሆን ወደፊት ከክለቡ ጋር የተለያዩ ውይይቶችን እያደረግን የተሻሉ ነገሮችን ለማምጣት እንሞክራለን። በተጨማሪም “ቅዳሜ ቢራ” የሚል ምርት እያቀረብን ነው። ይህንንም ምርት ለማስተዋወቅ ከክለቡ ጋር እንነጋገራለን።

“ከባስ ጋር በተገናኘ እኛ በይፋ ባስ እንገዛለን ብለን አልተናገርንም። ግን በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ይህ ነገር እየተሰራጨ ነው። በእኛ በኩል ምንም ችግር የለብንም። ቡና እና ሀበሻ ለህግ ሲሉ ዉል ይፈራረማሉ እንጂ ብዙ ነገሮችን በንግግር እና በመግባባት ነው የሚከውኑት። ይህም ነገር ለክለቡ አስፈላጊ ከሆነ ንግግሮችን አድርገን ወደፊት የምንገልፀው ነገር ይኖራል።”

የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ሚኒሊክ በበኩላቸው ስምምነቱን ተንተርሰው ተከታዩን ሃሳብ ሰንዝረዋል።

“የሀበሻ ቢራ እና የኢትዮጵያ ቡና ስምምነት የጋብቻ ያክል ነው። ሁለታችንም ለመጠቃቀም እንሰራለን። በተለይ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ክለቡን ለመጥቀም ሟች እንደሆነ ይታወቃል። ማሊያውን ለብሶ እራሱ ሰርግም ሆነ ሀዘን የሚሄድ ደጋፊ ነው። ይህ ደግሞ የስፖንሰራችን ምስል በደንብ እንዲታይ ያደርጋል። ስለዚህ ሀበሻ ቢራ በዚህ አካሄድ ይጠቀማል። እንደውም እውነት ለመናገር እኛ ያለንን የደጋፊ አቅም አሟጠን እየተጠቀምን አደለም።”

በመግለጫው ላይ የተጠቀሱት የገንዘብ መጠኖች በየሩብ ዓመቱ እንደሚፈፀሙ ተገልጿል። ስምምነቱን በተመለከተ ገለፃዎቸ በሚደረጉበት ሰዓትም ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በያዝነው ዓመት ለደጋፊዎች የሚሆኑ ቁሳቁሶችን መሸጫ ትልቅ ሱቅ ለመክፈት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ተጠቁሟል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!