ሶከር መጻሕፍት | የቢዬልሳ ኗሪ – ውርስ

THE PHILOSOPHY OF FOOTBALL፡ UNDER THE SHADOWS OF MARCELO BIELSA” ለአራት ዓመታት ያህል ከፍተኛ ጥናትና ምርምር የተደረገበት ሥራ ነው፡፡ በጠረጴዛ ዙረያ ቡና ፉት እየተባለ ከተደረጉ ምሁራዊ ውይይቶች አንስቶ ማርሴሎ ቢዬልሳን የተመለከቱ በርካታ ቃለ-መጠይቆችን መሥራት ጠይቋል፡፡ የእግርኳስ ሐሳባውያኑን ፍለጋ የተደረጉ የውጭ ጉዞዎችና አያሌ መጻሕፍትን መዳሰስም የዚህ መጽሐፍ ግብዓቶች ሆነዋል፡፡ ጸሃፊው በዚህኛው ምዕራፍ አርጀንቲናዊው የእግርኳስ ታክቲክ ባለሟል ከሌሎች በተለየ ኅልዮታዊ ልህቀት ያገኙበትን ምስጢራት ለማብራራት ይጥራል፡፡

ምዕራፍ አንድ – ክፍል አንድ

ሁሌም ቢሆን ቀዳሚው ሃሳብ ለተከታዩ ትርጉም አሻሚ ይሆናል፡፡” – ሆርሄ ሉዊስ ቦርሄስ

ስለ ማርሴሎ ቢዬልሳ አዘወትሬ አሰባለሁ። በእግርኳስ አጨዋወት ዘይቤ ላይ ስላሳረፉት አሻራ እና ስለ ተጽዕኖአቸው ዘላቂነት አሰላስላለሁ፡፡ ይህን ሳውጠነጥን ታላቁ አርጀንቲናዊ ገጣሚና ባለቅኔ ሆምዬሮ ማንዚ በአዕምሮዬ ድቅን ይልብኛል፡፡ ከእርሱ የጥበብ ሥራዎች መካከል በልቤ ያኖርኩትና “ሞቴን ህያው የሚያደርጉ ኹነቶች” የሚል ርዕስ ያለው ግጥም ትውስ ይለኛል፡፡ ቀጥሎ የቀረቡት ጥቂት ስንኞች ደግሞ ሃሳቤን የተሻለ ይገልጹልኛል፡፡

ሥሜ -መጠሪያዬ- በሰዎች አዕምሮ፤

ምሉዕ ምስል ፈጥሮ፤

ሲያስተጋባ አያለሁ በወዳጆች ጆሮ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደ’ሞ ይኸው መጠሪያዬ-ስም-መሆኑ ቀርቶ፤

የቃላት ጋጋታ-የቃላት ድሪቶ፤

ሊሆን እንደሚችል አይጠፋኝም ከቶ፡፡

የግጥሙ ፍሬ-ሐሳብ በውስጤ የተለየ ቦታ ያገኘው በበቂ ምክንያት ነው፡፡ በእግርኳስ ታሪክ እጅግ ብዙ ተጽእኖ ፈጣሪዎች በጨዋታው ዙሪያ የለውጥ አራማጆች ሆነው አልፈዋል፡፡ እግርኳሳዊ ሐሳቦች ወጥ በሆነ የለውጥና የእድገት ሒደት ውስጥ ቅቡልነት በማግኘትና በማጣት ምልልስ ኖረዋል፡፡

ቺሊያዊው ጸሃፊ ሮቤርቶ ቦላኖ በለውጥ እና እድገት ዙሪያ የግል አስተያየቱን በዚህ መልኩ ይሰጣል፡፡ “እንደ ተፈጥሮ መመሪያ ተወስዶ የሰው ልጅ በህይወቱ የሚገጥሙትን ትልልቅ ተመክሮዎች ወይ ይላመዳቸዋል-አልያም ጭራሹኑ ይጥላቸዋል፡፡ በአንጻሩ ትንንሽ ሆነው የማይታዩ የሚመስሉ ታሪካዊ ዋጋ ያላቸው እሴቶቹን ደግሞ ከቁብ አይቆጥራቸውም፡፡”

ለበርካታ አሰልጣኞች ዘላቂ የፍልስፍና መዋቅር ያበጃጀ አሰልጣኝ ሥሙ “ሥም ብቻ!” ሆኖ ይቀራል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው፡፡ ከላይ በቀረበው ግጥም ውስጥ የ”ቃላት ድሪቶ” በሚለው ስንኝ የተገለጸው “የመጠሪያ-ሥም” ትርጓሜ ልኩ “የጥንድ ቃላት ትርጉም-የለሽ ስብስብ” ብቻ እንዳይሆን የባለ ሥሙ ገቢር ወይም አበርክቶት ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ዓለምአቀፋዊው የቢዬልሳ እግርኳሳዊ ተጽዕኖ በሒደት ወደ ከፍታው እየወጣ ይገኛል፡፡ አርጀንቲናዊው የታክቲክ ልሂቅ በአሰልጣኝነት ዘመናቸው ያሸበረቁ ገድሎች ባለቤት አልሆኑም፤ በበርካታ የዋንጫ ድሎችም አልታጀቡም፡፡ ይህኛው የቢዬልስ ማንነት ሰውየውን ከታላቅነት ማማ ላይ ስንዝር ዝቅ አለማድረጉ ለብዙዎች ግራ ያጋባል፡፡ በግዙፍ ስብዕናቸው እና በሚያስመዘግቧቸው “ተራ” ድሎች መካከል የቆሙ ሰዎች ነገሩ ተቃርኖ ይሆንባቸዋል፡፡ “እብዱ ሰው” በአስተሳሰብ ልህቀት እና በግዙፍ-ስኬት አልባ የአሰልጣኝነት ህይወት ተጻራሪ ጥጎች የተቀመጡ የእግርኳስ አጨዋወት ዘይቤ ባለሟል ናቸው፡፡ ቢዬልሳ በቅርብ ለሚያውቋቸው ጥቂቶችም ሆነ ለማያውቋቸው በቀላሉ የማይፈቱ ረቂቅ ቅኔ ናቸው፡፡ ለአንዳንዶች እርሳቸው እግርኳሱ ላይ ደማቅ አሻራቸውን ያሳረፉ ሲሆን ለሌሎች ደግሞ አይን የማይገባ አስተዋፅኦ ያላቸው መደበኛ አሰልጣኝ ይሆኑባቸዋል፡፡

ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በቢዬልሳ ፍልስፍና ዙሪያ ማብራሪያ ለመስጠት ነው፡፡ የእግርኳስ አጨዋወት የሚቃኝበት መነጽር ላይ ትልቁን ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ ሚና ከመጫወት አንጻር የመጽሃፉ አጠቃላይ ይዘት በአንባቢዎች ዘንድ በሁለት ጽንፍ የሚገኙ ዕጣዎች ይገጥሙታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ተቃውሞ ወይም ተቀባይነት፡፡ የአሰልጣኙ ሐሳብ መጨረሻ ቅቡልነት አልያም ሙሉ በመሉ ውድቅ መደረግ ሊሆን ይችላል እንጂ በፍጹም በቸልታ አይታለፍም፡፡ ፋይዳ ቢስ ሊሆን ከቶም አይችልም፡፡ በተለይ-በተለይ በተዓምር እንኳ “የማይረባ” አይሰኝም፡፡

መጽሐፉ እና ውስጡ የያዘው ሐሳብ የማርሴሎ ቢዬልሳን ውስብስብ እግርኳሳዊ አስተምህሮ ለእግርኳስ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ማስተማሪያነት ማዋል የሚያስችል የዋናው ፍልስፍና ቅጂ ነው፡፡ የአሰልጣኙ የአጨዋወት እሳቤዎች በቀጥታ ተወስደውም ይሁን ንድፈ-ሐሳቡ መነሻ ሆኗቸው ትልቅ ደረጃ የደረሱ አሰልጣኞች ከፍተኛ ተነሳሽነት ፈጥሮላቸዋል፡፡ ማውሪዚዮ ፖቼቲኖ፣ ጄራርዶ ማርቲኖ፣ ሆርሄ ሳምፓውሊ፣ ኤድዋርዶ ቤሪዞ፣ ፔፕ ጓርዲዮላ፣ ማሪያኖ ሶሶ፣ ዲዬጎ ሲሞኔ፣ ዳሪዮ ፍራንኮ፣ ሁዋን ማኑዌል ዮፕ፣ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ እና ሌሎች የቢዬልሳ ደቀ-መዛሙርት በብዙኃን መገናኛዎች “ቢዬልሲስታ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቢዬልሳ በቺሊ ብሄራዊ ቡድን እና በቀድሞው የአርጀንቲና ታላቅ ክለብ ኒዌልስ ኦልድ ቦይስ ለዘመናት የሚዘልቅ ኗሪ-ውርስ ትተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ የሃገራቸው ክለብ ስታዲየሙን “ማርሴሎ ቢዬልሳ ስታዲየም” ብሎ ሰይሞላቸዋል፡፡

የማርሴሎ ቢዬልሳ አበርክቶት በእግርኳስ ታክቲክ በፈጠረው ትልቅ ለውጥ ላይ ብቻ አይወሰንም፡፡ በዚህ ዘመን ከእርሱ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ልምምዶችን የሚያሰሩ አሰልጣኞች እንድናይ አድርጎናል፡፡ እኔ በዚህ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንደ ፖቼቲኖ፣ ሲሞኔ፣ ቤሪዞና የመሳሰሉት የእርሱ ፈለግ ተከታዮች ናቸው፡፡” – ኤሪክ ቴንያዶ፦ በኢስፓኞል የታዳጊ ቡድን አሰልጣኝ

ይህ ምዕራፍ ከስመ-ጥሩ አርጀንቲናዊ የአጫጭር ልቦለዶች ጸሃፊ ሆርሄ ሉዊስ ቦርሄስ በተወሰደና “ሁሌም ቢሆን ቀዳሚው ሃሳብ ለተከታዩ ትርጉም አሻሚ ይሆናል፡፡” በሚለው ዓረፍተ-ሐሳብ ይጀምራል፡፡ ይህ አባባል የምዕራፉ ንዑስ ርዕስ ሆኖ ተመርጧል፡፡ አባባሉ በ1782 በዊሊያም ብሬክፎርድ አማካኝነት የተደረሰውን አዲስ እና ወጥ “ቫቴክ” የተሰኘ ልቦለድ በ1986 ሳም ሄንሊ ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ አሻሽሎ ሲተረጉመው ቦርሄስ በትርጉም ሥራው ተደንቆ የተናገረው አስተያየት ነው፡፡ ማርሴሎ ቢዬልሳ እና ሐሳቦቹ ከሌሎች በርካታ ቀደምት ፍልስፍናዎች የተከለሱ፣ በስፋት የተጠኑ እና ጥልቅ ምርምር የተደረገባቸው እሳቤዎች ውጤት ናቸው፡፡

ገነት ሁሌም ቤተ መጻሕፍት መስላ ትታየኛለች፡፡” – ሆርሄ ሉዊስ ቦርሄስ

ማርሴሎ ቢዬልሳ እጅግ ብዙ የእግርኳስ ጨዋታ ቪዲዮዎች፣ በእግርኳስ አጨዋወት ዙሪያ የተሰሩ በርካታ ጥናቶች፣ የእግርኳስ ጨዋታን በጥልቀት የሚመረምሩ ዝርዝር ትንተናዎችን የሚገኙባቸው ቁጥር-ሥፍር የማይገኝላቸው ሰነዶች የታጨቁበት ሰፊ ቤተ መጻህፍት መሳይ ክፍል እንዳላቸው ዘወትር ይነገራል፡፡ ጥልቀትና ስፋት ባለው ሃሳብ የተቃኘው እና የእግርኳስ አጨዋወት ሥልትን የሚዳስሰው ፍልስፍናቸውም በአግባቡ ተብራርቶና በንድፈ-ሐሳብ ደረጃ ተጠናቅሮ ተቀምጧል፡፡ በ1990ዎቹ የኮሎምቢያን ብሄራዊ ቡድን (ሎስ ካፌቴሮስ) ያሰለጠኑት ፍራንቼስኮ ማቹራና፣ በ1930ዎቹ የታላቁ የኦስትሪያ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ጂሚ ሆጋንና ሑጎ ሜይዝል፣ የ1950ዎቹ ሃንጋሪ ቡድን (ማይቲ ሜኸርስ) አሰልጣኝ ጉስታቭ ሴቤዝ፣ ዮሃን ክራይፍ፣ ሩኑስ ሚቼልስ፣ ቪክቶር ማስሎቭ፣ ቫለሪ ሎባኖቭስኪ፣ ሉዊስ ሴዛር ሜኖቲ፣… እነዚህ ሁሉ አሰልጣኞች ቢዬልሳ ላይ ትልቅ የአተያይ ተጽዕኖ ፈጥረዋል፡፡ ቢዬልሳ ሁሉንም ቀደምት የአዲስ አሰተሳሰብ አራማጆች አድርገው በመውሰድ ከእነርሱ ብዙ ተምረዋል፡፡

ቺሊያዊው አርቱሮ ሳላህ፣ በጥቂቶች ብቻ እውቅና ያለው ጣልያናዊው ኤዚዮ ግሌሪን፣ ዝድኔክ ዜማን እና ሪካርዶ ላቮልፔን የመሳሰሉት አሰልጣኞች ተገቢው ዕውቅና ባይቸራቸውም የታክቲካዊ ጽንሰ-ሐሳብ ባለሟሎች መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ቢዬልሳ በታክቲክ እውቀታቸው ይመነደጉ ዘንድ የእነዚህኞቹም አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ከእያንዳንዳቸው አሰልጣኞች አርጀንቲናዊው ለእግርኳስ አጨዋወት ጥናታቸው የወሰዷቸውም ሆኑ የጣሏቸውም ግብዓቶች አሏቸው፡፡ ሁሉም “የጥንት ታክቲሺያኖች” በእርሳቸው የጨዋታ ፍልስፍና ማዕቀፍ ውስጥ ቦታ አላቸው፡፡ ከብዙ ቀደምት ባለ ጥልቅ እሳቤ አሰልጣኞች የተማሩት ቢዬልሳ ራሳቸውን እጅጉን አሻሽለው ለሌሎች አያሌ የታክቲክ ልሂቃን ደግሞ መነሻ ሆነዋል፡፡

ይቀጥላል…

የመጽሃፉ ደራሲ ጄድ ሳይናን ዴቪስ ይባላል፡፡ ዌልሳዊው በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በዋና አሰልጣኝነት፣ በኢስቶኒያ ብሄራዊ ቡድን ደግሞ በምክትል አሰልጣኝነት ሰርቷል፡፡ የሰላሳ ሁለት ዓመቱ ወጣት በአሁኑ ወቅት “ኦታዋ ፈሪ” በተባለው የካናዳ ክለብ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ ከ2019 ጀምሮ በኦታዋ ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ የእግርኳስ ፕሮፌሰር ሆኖ Strategy in Association Football ያስተምራል፡፡ ዴቪስ በ2013 ” Coaching the Tiki-Taka Style of Play” የተሰኘ መጽሃፍ አሳትሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ