“ዘንድሮ የተሻለ የመሰለፍ ዕድል ለማግኘት ጥረት አደርጋለሁ” የፋሲል ከነማው ተስፈኛ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ

በዛሬው የተስፈኞች አምዳችን ላይ ከፈጣኑ እና ሁለገቡ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ጋር ቆይታ አድርገናል።

በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ተወልዶ ያደገው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክት እግርኳስን የጀመረ ሲሆን በ2009 አማራ ክልልን ወክሎ ከተጫወተ በኋላ በዛው ዓመት ፋሲል ከነማ ተስፋ ተቀላቅሏል። ለሁለት ዓመት በተስፋ በቡድኑ ቆይታ ያደረገው ናትናኤል በውበቱ አባተ አማካኝነት ወደ ዋናው ቡድን የማደግ ዕድልን አግኝቷል። በ2012 ከቢጫ ወደ አረንጓዴ ቴሴራ የተሸጋገረ ሲሆን ውል ከማደሱ በፊት ከቀድሞ አሰልጣኙ ሰበታ ከተማ የውሰት ጥያቄ የቀረበለት ቢሆንም ፋሲል ከነማ ጥያቄውን ወድቅ አድርገው ተጨማሪ ዓመት በማስፈረም እንዲቆይ አድርገውታል።

በሁለቱም መስመሮች እንዲሁም በፊት አጥቂ ተሰልፎ መጫወት የሚችለው ተጫዋቹ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ሰብሮ ለመግባት ከበረከት ደስታ እና ሽመክት ጉግሳ ጋር ጥብቅ ፉክክር ይጠብቀዋል።

“ተወልጄ ያደኩት ጎንደር ሲሆን እግርኳስን በሠፈር እና ትምህርት ቤት መጫወት ጀምሬ 2008 ላይ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ውስጥ መኮንን ገብሬ የሚባል አሰልጣኝ ጋር ለአንድ ዓመት ሰራሁ። በመቀጠል ለጎንደር ከተማ እና ለክልል ቡድን ተጫውቼ በ2009 ወደ ፋሲል ከነማ ተስፋ አመራሁ። እዛም የተሳካ የሚባል ሁለት ዓመት ካሳለፍኩ በኋላ በ2010 ሀዋሳ ወድድር ላይ በውበቱ አባተ ተመርጠን ወደ ዋናው ቡድን አድገን። በቢጫ ቴሴራ ከተስፋ ቡድን እየተመላለስኩ ከዋናው ቡድን ጋር እሰራ ነበር። ያ ጊዜ ለኔ በጣም ጥሩ ጊዜ ነበር። በርካታ ልምዶችን አግኝቻለሁ። 2012 ላይ ዋናው ቡድን ላይ የተወሰኑ ደቂቃዎች ተጫውቻለሁ። ግማሽ ዓመት ላይም ከተመላላሽ ወደ አረንጓዴ በመፈረም የዋናው ቡድን ተጫዋች መሆን ችያለሁ። ክለቡም እኔ ላይ እምነት ስለጣለብን ያለኝን ሁሉ ሰጥቼ ራሴን አሳያለሁ የሚል እምነት አለኝ።

“በአሰልጣኞች ጥቆማ ለሀያ ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመርጭ ሄጄ ነበር። ሆኖም በኤርትራ፣ ኢትዮጵያ እና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል ሊካሄድ የነበረው ጨዋታ ተሰርዞ ሳልጫወት ቀርቻለሁ። ቢደረግ ጥሩ ነበር። ግን ወደፊት ማሳካት ስለምችል ብዙም አያስቆጨኝም።

” በኮሮና ምክንያት የነበረው ጊዜ በጣም ከባድ ነበር። በነዚህ ወቅቶች በግሌ እና ከሠፈር ልጆች ልምምድ እሰራ ነበር። እንዲሁም የተስፋ ቡድን አሰልጣኝ ግርማይ ኪሮስ አምስት አራት እያደረገ በሦስት በአራት ከፍሎ ጎንደር ያለን ልጆችን ያሰራን ነበር፤ ድጋፍ ያደርግልን ነበር። እና ከኳስ ጋርም ከኳስ ውጭም ልምምድ በመስራት ነበር ያሳለፍኩት።

” የቅርብ ጊዜ እቅዴ ዋናው ቡድን ላይ ሰብሬ በመግባት የተሻለ ነገር በማድረግ ከቡድኑ ጋር የተሻለ ነገር ማሳየት ነው። ባለፈው ዓመት የተወሰኑ ደቂቃዎች መግባት ችያለሁ። አሁን ደግሞ ይበልጥ ዕድሉን ለማግኘት ጥረት አደርጋለሁ። በዚህ አጋጣሚ የአሰልጣኝ አባላትን እንዲሁም አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን የእቅዳቸው አካል ስላደረጉኝ ማመስገን እፈልጋለሁ። የረዥም ጊዜ እቅዴ ከሀገር ወጥቼ መጫወት ነው። ብሔራዊ ቡድን ማገልገልም እፈልጋለሁ። የረዥም ጊዜ እቅድ ቢሆኑም እድሎች ከተፈጠሩ ግን ለየትኛውም ነገር ዝግጁ ነኝ ብዬ አምናለሁ።

“እህቴ ሰናይት ገብረጊዮርጊስ በጣም ነው ድጋፍ የምታደርግልኝ። የትጥቅ ድጋፍ እና ሜዳ ላይ በመገኘት ማበረታታትን ጨምሮ በርካታ ነገሮችን አድርጋልኛለች። እሷን በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ ።

“ከተጫዋቾች የአብዱራህማን ሙባረክ (ግሪዳው) አድናቂ ነኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ እሱን እያየሁ ነው ያደኩት እና እሱ ለእኔ ዕዓያዬ ነው። ከውጭ ሀገር የክሪስቲያኖ ሮናልዶ አድናቂ ነኝ። እሱ ሲጫወት መየት ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥርልኛል። ጠንክሮ መስራትን እማርበታለሁ።

“ከአሰልጣኞች ጠቅሼ አልጨርሳቸውም። ብዙ ናቸው መለያየት ይከብደኛል። ከፕሮጀክት ጀምሮ መኮንን ገብሬ፣ አሰልጣኝ ግርማይ ኪሮስ ከተስፋ ቡድን፣ አሰልጣኝ ታደሰ መኳንንት፣ አሰልጣኝ ዘመኑ ታፈረ፣ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ይታገሱ እንዳለ ለኔ ትልቅ ቦታ አላቸው።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!