ሪፖርት | ዋልያዎቹ በአቋም መለኪያ ጨዋታ ተረተዋል

ከዛምቢያ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያደረጉት ዋልያዎቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠረባቸው ሁለት ጎሎች 3-2 ተሸንፈዋል።

በኮቪድ-19 ምክንያት ለተራዘመው የ2021 (ወደ 2022 የተሸጋገረው) የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎች እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኒጀር ጋር ላለበት የምድቡ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታ በዛሬው ዕለት የአቋም መለኪያ ጨዋታ ከዛምቢያ አቻው ጋር አከናውኗል። ከሳምንታት በፊት ብሔራዊ ቡድኑን ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ለማሰልጠን የተስማሙት አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ጀማል ጣሰው፣ ረመዳን ተስፋዬ፣ ያሬድ ባዬ፣ አስቻለው ታመነ፣ ሱሌማን ሀሚድ፣ ይሁን እንዳሻው፣ መሱዕድ መሐመድ፣ ታፈሰ ሰለሞን፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ጌታነህ ከበደ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤልን በመጀመርያ ተሰላፊነት በመጠቀም ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

ምንም እንኳን በባዶ ስታዲየም ይደረጋል ቢባልም በርካታ እንግዶች በክቡር ትሪቡን ሆነው በታደሙበት እና የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር በክብር እንግድነት በተገኙበት ጨዋታ ላይ ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያዎቹን ደቂቃዎች መጠናናት በሚመስል የጨዋታ እንቅስቃሴ ሲጫወቱ ተስተውሏል። በአንፃራዊነት ዋልያዎቹ ኳስን በመቆጣጠር የጨዋታውን ሚዛን ወደ ራሳቸው ለማድረግ ጥረዋል። በተቃራኒው በራሳቸው ሜዳ አብዛኛውን የጨዋታ ጅማሮ ያሳለፉት ዛምቢያዎች በበኩላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በዘጠነኛው ደቂቃ ያገኙትን እድል ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክረዋል። በዚህ ደቂቃም ከልቨርት ካምፓምባ በረጅሙ የተላከውን ኳስ ተከላካዮች ሲመልሱት የተገኘ ኳስ ከመስመር በድጋሚ ሲሻማለት በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ የግቡ አግዳሚ መልሶበተል።

በእርጋታ ጨዋታውን የቀጠሉት ዋሊያዎቹ አስደንጋጩን ሙከራ ካስተናገዱ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በማምራት የመጀመሪያ ሙከራቸውን ወደ ግብነት ቀይረዋል። በዚህም ከግራ መስመር የተገኘውን ኳስ ረመዳን በጥሩ ሁኔታ ራሱን ነፃ እያደረገ ለነበረው የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ አቀበሎት ጌታነህ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ለተቆጠረባቸው ግብ በቶሎ ምላሽ ለመስጠት የፈለጉት ዛምቢያዎች ግብ ክልላቸውን ለቀው በወጡበት ቅፅበት የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረው ጌታነህ በድጋሜ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። በዚህ እንቅስቃሴም በጥሩ የማጥቃት ሽግግር የተገኘውን ኳስ ሱራፌል ለጌታነህ ከተከላካይ ጀርባ አቀብሎት ኳሱ ወደ ግብነት ሳይቀይር ቀርቷል።

አሁንም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረታቸውን የቀጠሉት ተጋባዦቹ በ19ኛው ደቂቃ የተገኘን የመዓዘን ምት በኢማኑኤል ቻቡላ አማካኝነት ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክረው ሳይሳካላች ቀርቷል። በ29ኛው ደቂቃም በጥሩ የኳስ ፍሰት ወደ ግብ የደረሱ ሲሆን ቻቡላ ከካምፓምባ ያገኘውን ጥሩ ኳስ በድጋሜ ወደ ግብነት ሳይቀይረው አልፏል። በእነዚህ ሁለት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች ብቻ ወደ ዋሊያዎቹ የግብ ክልል መድረስ ያላቆሙት የአሠልጣኝ ሚቾ ተጫዋቾች በ31ኛው ደቂቃ ተጭነው በመጫወታቸው ያገኙትን ጥሩ ኳስ በኮሊንስ ሲኮምቤ አማካኝነት ወደ ጎል መትተው ጀማል አምክኖባቸዋል።

ከፍተኛ እርጋታ የሚታይበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ መሪነቱን ካገኘ በኋላ በድጋሚ የላሜክ ሲያሜን መረብ ለመፈተሽ እስከ 37ኛው ደቂቃ መጠበቅ ግድ ብሎታል። በዚህ ደቂቃም በቀኝ የአጥቂ መስመር ላይ የተሰለፈው ሱራፌል የግብ ጠባቂውን አቋቋም ተመልክቶ ወደ ጎል የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ይህ ሙከራ በተደረገ በሁለት ደቂቃዎች ውስጥ ጀማል ወደ ኋላ የተመለሰለትን ኳስ አፀዳለው ብሎ ተመቻችቶ ለቆመው ካምፓምባ አቀብሎት ካምፓምባ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

ጫናዎችን የበዛባቸው ዋልያዎቹ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ተከላካዩ ሉካ ባንዳ በመሱዕድ ላይ በሰራው ጥፋት አማካኝነት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው አስቻለው ታመነ አጋጣሚውን ወደ ጎል ቀይረው ዳግም መሪ ሆነዋል። አጋማሹም ተጨማሪ ሙከራ እና ጎል ሳያስተናግድ በዋሊያዎቹ 2-1 መሪነት ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽም አሠልጣኝ ውበቱ ሙጂብ፣ ጋዲሳ፣ ሽመክት፣ ሀብታሙ ተ፣ ሀይደር፣ ይድነቃቸው እና ከነዓንን በጌታነህ፣ ሱራፌል፣ አማኑኤል፣ ይሁን፣ መሱዕድ፣ ጀማል እና ታፈሰን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። የኋላ አራት ተከላካዮቹን ብቻ ሳይቀይሩ ወደ ሜዳ የገቡት ዋሊያዎቹም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጅማሮ እርጋታ የታከለበት ከኳስ ጋር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር። በተቃራኒው እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል የገቡት ዛምቢባያዎች በበኩላቸው በርከት ያሉ ለውጦችው በማድረግ የተሻለ ለማጥቃት ጥረት አድርገዋል። በ58ኛው ደቂቃም ቻቡላ በመስመሮች መካከል ባገኘው እና ወደ ጎል በመታው ነገርግን ኢላማውን በሳተበት ሙከራ የይድነቃቸውን ግብ መፈታተን ጀምረዋል። በተጨማሪም በ62ኛው ደቂቃ ከጥሩ ቦታ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት ሲኮምቤ ወደ ግብ መትቶት ነበር። በጨዋታው ኳስን ቢቆጣጠሩም እንደ ልብ ወደ ጎል መድረስ የተሳናቸው ባለሜዳዎቹ በ66ኛው ደቂቃ የተገኘን የመልሶ ማጥቃት ጋዲሳ ለሙጂብ አመቻችቶለት ግብ ጠባቂው ሲያሜ ወጥቶ አድኖታል። ከደቂቃ በኋላም ሀይደር ለቀኝ መስመር ተከላካዩ ሱሌማን ምርጥ የአግድሞሽ ኳስ አቀብሎት ወደ ሳጥን የተሻማውን ኳስ ሙጂብ ሳይደርስ በድጋሚ ግብ ጠባቂው ቅልጥፍናውን ተጠቅሞ አምክኖታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ሀይደር በድጋሚ በ74ኛው ደቂቃ በተከላካዮች መካከል ጥሩ ኳስ ለሙጂብ አመቻችቶለት አጥቂው በአስቆጪ ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ፍጥነቱ በቀነሰው በዚህ አጋማሽ ላይ ቺፖሎፖሎዎቹ ተደጋጋሚ ጫናዎችን በተወሰኑ ደቂቃዎች ቢያስተናግዱም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሙሉ ሃይላቸውን ተጠቅመው ለማጥቃት ሲጥሩ ተስተውሏል። በዚህም በ86ኛው ደቂቃ በተጫዋቾች ተጨራርፎ የተገኘውን ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አልበርት ካዋንዳ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። በዚህች ጎል አቻ የሆኑት ዛምቢያዎቹ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ከቅጣት ምት በተሻማ ኳስ ወደ ጎል ደርሰው መሪ ለመሆን እጅግ ተቃርበው ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች መዘናጋቶች ሲታይባቸው የነበሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ሙሉ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ የተሸነፉበትን ግብ አስተናግደዋል። በዚህም የመሐል ዳኛው ጨዋታው መገባደዱን ሊያሳውቁ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩት በረጅሙ የተላከን ኳስ የአቻነቱን ጎል ያስቆጠረው አልበርት ካዋንዳ በግንባሩ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታውን ደምድመዋል። ይህቺ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከትኩረት ማነስ እና መዘናጋት የተገኘች መሆኗ ቢታይም ጎሉን ለቆ ያለ ሰዓት የወጣው ይድነቃቸው ኪዳኔ ለግቡ መቆጠር አስተዋፆ ጉልህ ነበር።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በሁለተኛው አጋማሸ ከያሬድ ባዬ ውጪ ሁሉንም የመጀመርያ ተሰላፊ ተጫዋቾች ቀያይረው የተጨዋቾችን አቅም የገመገሙ ሲሆን የተወሰኑ ተጫዋቾችም ያለ ተፈጥሮዋዊ ቦታቸው ሲያጫወቱ ተስተውሏል። ከካዋንዳ የግንባር ጎል በኋላ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ ጨዋታው መገባደዱን በፊሽካቸው አረጋግጠው ዋልያወቹ ከ10 ወራት በኋላ ያደረጉትን ጨዋታ በሽንፈት አጠናቀዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!