ፕሪሚየር ሊግ፡ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ ድል ሲቀናቸው ተጠባቂዎቹ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ 4 ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ድል ሲያስመዘግቡ ደደቢት እና ቡና ከሜዳቸው ውጪ ነጥብ ይዘው ወጥተዋል፡፡

ይርጋለም ላይ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ክለቦች ባገናኘው ጨዋታ ሲዳማ ቡና ደደቢትን አስተናግዶ መሪነቱን ማስጠበቅ ሳይችል አቻ ተለያይቷል፡፡ ሲዳማ ቡና ፍጹም ተፈሪ በ12 እና 17ኛ ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ግቦች 2-0 መምራት ቢችልም ደደቢቶች በ75ኛው ደቂቃ በሳምሶን ጥላሁን የፍጹም ቅጣት ምት እና በብርሃኑ ቦጋለ በተጨማሪው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ግቦች 1 ነጥብ ይዘው ወጥተዋል፡፡ የአቻ ውጤቱ ሁለቱ ቡድኖች መሪዎቹን ለመጠጋት የነበራቸውን እድል አበላሽቶባቸዋል፡፡

ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ድል አስመዝግቧል፡፡ የሀዋሳ ከተማ ሶስቱም ግቦች የተገኙት ጨዋታው ገና 25 ደቂቃዎችን ሳያልፍ ነበር፡፡ እስራኤል እሸቱ ፣ አስቻለው ግርማ እና ደስታ ዮሃንስ ለሰማያዊ ለባሾቹ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ታገል አበበ በ2ኛው አጋማሽ የአርባምንጭን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ሀዋሳ ከተማ በድሉ ታግዞ የወራጅ ቀጠናውን ለአርባምንጭ በማስረከብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

ወደ ሆሳዕና ያቀናው ኤሌክትሪክ ሁዲያ ሆሳዕናን 1-0 በማሸነፍ 3 ደረጃዎችን አሻሽሏል፡፡ የኤሌክትሪክ ብቸኛ የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው ናይጄርያዊ ግዙፍ አጥቂ ፒተር ኑዋድኬ ነው፡፡ ኤሌክትሪክ በድሉ ታግዞ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ተሸናፊው ሀዲያ ሆሳዕና የሊጉን ግርጌ በ5 ነጥቦች ይዟል፡፡

ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና አቻ ተለያተዋል፡፡ በጨዋታው መጀመርያ የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች በድሬዳዋ የሚዘወተረውን ሽርጥ ልብስ ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊወች በመስጠት መልካም አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በካሜሩናዊው ዊልያም ያቤውን የ34ኛ ደቂቃ ጎል 1-0 መምራት ቢችልም ፍቃዱ ወርቁ በ79ኛው ደቂቃ ብርቱካናማዎቹን አቻ ያደረገች ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ የአቻ ውጤቱ ድሬዳዋ ከተማን በ5ኛ ደረጃው እንዲቆይ ሲያደርገው ቡና 10ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡

የፕሪሚየር ሊጉ 11ኛ ሳምንት ቅዳሜ ሲቀጥል ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ አዳማ ከተማን ያስተናግዳል፡፡ ዳሽን ቢራ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ መከላከያ የሚያደርጉት ጨዋታ በአፍሪካ የክለቦች ውድድሮች ምክንያት ለየካቲት 27 ተሸጋግረዋል፡፡

የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ይህንን ይመስላል፡-

PL

የከፍተኛ ግብ አግቢዎች ደረጃ፡-

TS

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *