ሶከር መጻሕፍት | መሠረታዊው ሐሳብ (ምዕራፍ ሁለት – ክፍል አንድ)

THE PHILOSOPHY OF FOOTBALL፡ UNDER THE SHADOWS OF MARCELO BIELSA” ለአራት ዓመታት ያህል ከፍተኛ ጥናትና ምርምር የተደረገበት ሥራ ነው፡፡ በጠረጴዛ ዙረያ ቡና ፉት እየተባለ ከተደረጉ ምሁራዊ ውይይቶች አንስቶ ማርሴሎ ቢዬልሳን የተመለከቱ በርካታ ቃለ-መጠይቆችን መሥራት ጠይቋል፡፡ የእግርኳስ ሐሳባውያኑን ፍለጋ የተደረጉ የውጭ ጉዞዎችና አያሌ መጻሕፍትን መዳሰስም የዚህ መጽሐፍ ግብዓቶች ሆነዋል፡፡ ጸሃፊው በዚህኛው ምዕራፍ አርጀንቲናዊው የእግርኳስ ታክቲክ ባለሟል ከሌሎች በተለየ ኅልዮታዊ ልህቀት ያገኙበትን ምስጢራት ለማብራራት ይጥራል፡፡

“እግርኳስ በተጫዋቾች ቁጥር ብልጫ የሚወሰን ጨዋታ ነው፡፡ በሜዳ ላይ ሁለት ተጫዋቾች በአንድ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ላይ በሚያሳድሩት ጫና የሚካሄድ እንደማለት ይሆናል፡፡” – አይርተን ሳርጉሲንግ

አይርተን ሳርጉሲንግ በካናዳ <<ዌስት ኦታዋ እግርኳስ ክለብ>> በተባለ የኮሌጅ ሴቶች እግርኳስ ቡድን አመራር ሆኖ አገልግሏል፡፡ ቀደም ሲል በስልጠናው ዓለም ከተሰማሩ ጓደኞቼ አንዱ ከሆነው ሳርጉሲንግ ጋር ራት ለመመገብ በአንድ ሬስቶራንት ተቀጣጠርን፡፡ የተገናኘን ምሽት ስለ እግርኳስ ስናወራ “እግርኳስ በተጫዋቾች ቁጥር ብልጫ የሚወሰን ጨዋታ ነው፡፡” የሚል ሐሳብ አነሳ፡፡ በአባባሉ እጅጉን ተማረክሁ፡፡ በከባዱ የካናዳ ብርዳማ የአየር ሁኔታ በተመስጦ ሳርጉሲንግ የሚናገረውን ማዳመጤን ተያያዝኩ፡፡ በፊትም ቢሆን የዚህኛው ቀጠሯችን ዓላማ አጓጉቶኝ ቆይቷል፡፡ ውይይታችን ሲጀመር ሐሳባዊ ይዘቱ ከእኔ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም መሆኑ ተገለጠልኝ፡፡ ስለ እግርኳስ በጽንሰ-ሐሳቦች ዙሪያ ማውራት ከሚያስደስተው ሰው ጋር መቀመጤም ገባኝ፡፡ አይርተን ለታክቲካዊ የሐሳብ ሙግት ዝግጁ የሆነ ሰው ነው፡፡ መሳዬን አገኘሁ ማለት አይደል ታዲያ? በውይይታችን የተለያዩ ሐሳቦች ተነሱ፤ ክርክራችን ቀደም ብዬ በትክክለኝነት የልኬት ጥግ የምፈርጃቸውን ነባራዊ ሐቆች ዳግም እንድጠይቅ አስገደደኝ፡፡ አዕምሮዬ  እውነታዎችን ይሞግት ያዘ፤ በቀድሞው ግንዛቤዬ ላይ ጥርጣሬ ተሰማኝ፡፡ የአደጋ መከላከያ ባርኔጣ እና የበረዶ መቅዘፊያ ዘንግ ተይዞ የሚደረገው የበረዶ ሸርተቴ ውድድር በልክፍት ደረጃ በተጠናወታት ሃገር ውስጥ ሆኜ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤቴ ያለሁ  ተሰማኝ፡፡

” እባክህ ቀጥል…” አልኩ በጉጉት፡፡ ይህን መሰል ግላዊ አስተያየት የሚቃረን ወይም እርሱ የደረሰበትን ድምዳሜ የሚቃወም ምንም አይነት ሐሳብ በአዕምሮዬ እንዲመላለስ አልፈለግሁም፡፡ ከዚያ ለሁለት ሰዓት ከግማሽ ያህል የተለያዩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያዊ ኹነቶችን በምስል መልክ እየሞነጫጨርን ስለ አጨዋወት መርሆች አወጣን አወረድን፡፡ ተጻራሪ ሐሳቦች ላይ ተከራከርን፤ አፍራሽ መሟገቻ አስተያየቶቻችንን አዥጎደጎድን፡፡ የሐሳብ ፍጭታችን ከውይይት፣ ክርክርና ሙገት አልፎ ጓደኛዬን ከተቀመጠበት እንዲነሳ አስገደደው፡፡ በበርካታ ሰዎች በተጨናነቀው ምግብ ቤት ውስጥ አይርተን ከመቀመጫው ብድግ ብሎ የተለያዩ ቴክኒካዊ እንቅስቃሴዎችን በአካላዊ ገለጻ ያሳየኝ ጀመር፡፡ ሁለታችንም በእግርኳስ የአጨዋወት ሥልት ሳቢያ በምናባዊ ሜዳ ላይ የተገኘን ያህል ሆነን አረፍነው፡፡ በአቅራቢያችን ተቀምጠው ስለመዋደዳቸው ለሚያወጉት ጥንዶች ግድ አልነበረንም፡፡ ምሽቷን ቀዳሚ የፍቅር ቀጠሯቸው ትሆን ዘንድ የተገናኙትን አዳዲስ ተጣማሪዎችንም ከቁብ አልቆጠርናቸውም፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በእኔ እና አይርተን የማያባራ ክርክር እንዲሁም ለመተማመን በምናደርገው በእንቅስቃሴ የተደገፈ ሙግት መረበሻቸውን አልክድም፡፡      

እንቅስቃሴ፦

“ለተጫዋቾቼ አዘወትሬ የምነግራቸው የአጨዋወት ዘይቤያችን በማያቋርጥ እንቅስቃሴ እንደሚቃኝ ነው፡፡” ይላሉ ማርሴሎ ቢዬልሳ፡፡ አሰልጣኙ የእግርኳስ ፍልስፍናቸው የሚጸኑባቸው አራቱ  መሰረታውያን እንቅስቃሴ፣ ዑደት (የቅይይር ሒደት)፣ ትኩረት (መደርጀት) እና የድንገቴ ዝግጅት ናቸው፡፡ ሁሌም ስለ እነዚህ ሐሳቦች በጥልቀት ከመዘርዘራቸው በፊት አንኳር ስለሆነው ጉዳይ ሲያነሱ ወደ ተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል ሰብሮ ለመግባት “የማያቋርጥ እንቅስቃሴ” ማድረግ ቀዳሚው ተግባር መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ 

እዚህ ጋር መሠረታዊ እሳቤ የምንለው አፍአዊ ያልሆነውን ተግባቦት ይሆናል፡፡ በምናብ መግባባት መቻልን ማለት ነው፡፡ በልምምድ ወቅት የሰራነውን እና በሜዳ ላይ ለመከወን የምንሻውን ተግባር የሚያዋድድልንን መላ ከመፍጠርም ጋር ይያያዛል፡፡ ማርቲ ፓራነው ስለ ፔፕ ጓርዲዮላ የባየር ሙኒክ የመጀመሪያ የውድድር ዘመን ቆይታ ዙሪያ ባዘጋጀው ድንቅ መጽሃፍ ስፔናዊው የታክቲክ ልሂቅ ለአጨዋወት ዘይቤ መነሻ የሚሆነው ዓቢይ ጉዳይ ” የአሰልጣኙ እና ቡድኑ የሁለትዮሽ ምርጫ መጣጣም እንዲሁም እምነት እና ተልዕኮን የማዋሃድ ሥራ” መሆኑን አስፍሯል፡፡ ይህን ውስብስብ ሐሳብ ግልጽ የሚያደርገው ጥሩ ምሳሌ ዮሃን ክሯይፍ በሚከተለው መልኩ በአጭሩ ያስቀመጠው ፍልስፍናው ነው፡፡ “…መሰረታዊው ዓላማ ተጋጣሚ ቡድን ላይ የኳስ ብልጫ መውሰድ ነው፡፡”  ይህን ገዳይ በመጀመሪያው <> የተሰኘ መጽሃፌ ውስጥ በሰፊው አንስቻለሁ፡፡

ለሁለቱም መጽሃፎቼ ዝግጅት ይረዱኝ ዘንድ ጥናትና ምርምር ባደረግሁባቸው ያለፉት አምስት ዓመታት አዕምሮዬ ውስጥ በመሰረታዊነት የተፈረጁ ቀዳሚ ሐሳቦች ተከልሰዋል፤ ለውጥም ተደርጎባቸዋል፡፡ የጋራ በሆነው ወይም ብዙኃኑን በሚያስማማው መሰረታዊ ሐሳብ ዙሪያ ሶሥት ተጽዕኖ ፈጣሪ አሰልጣኞች ጥሩ አስተያየት አቅርበዋል፡፡ በርካታ አሰልጣኞች በፍላጎታቸው ላይ የተመሰረተ የአጨዋወት ሥልት ለመንደፍ የመጀመሪያውን መነሻ ሐሳብ ይቀበላሉ፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ ሁለተኛውን መነሻ ሐሳብ ይመርጣሉ፡፡ እነዚህኞቹ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት መውሰድን ከማጥቃት አላማ ጋር የሚያገናኙት ናቸው፡፡ በጣም አናሳ ቁጥር ያላቸው በሶስተኛ ጎራ የሚመደቡት አሰልጣኞችም አሉ፡፡ ከእነዚህ አሰልጣኞች ጎራ የሚመደቡት ሐሳባውያን ጨዋታው በኳሱ አልያም በሃያ ሁለት ተጫዋቾች እንቅስቃሴ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን መጫወቻ ሜዳ ላይ የሚፈጠሩ ክፍተቶች እና ሁኔታዎችም የራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው የሚያምኑ ናቸው፡፡

★ መነሻ ሐሳብ (1)

“…እኔ ሁሌም በቁጥራዊ መረጃዎች እየታገዝኩ ነው የምሰራው፡፡ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ይዞ ተጋጣሚ ላይ ጫና ማሳደር ከተቻለ ሰባ ዘጠኝ በመቶ የማሸነፍ ዕድል ይኖራል፡፡” – ብሬንዳን ሮጀርስ

★ መነሻ ሐሳብ (2)

” …ዋናው ዓላማችን ኳሱን ሳይሆን ተጋጣሚን መግፋት ነው፡፡” – ፔፕ ጓርዲዮላ

★ መነሻ ሐሳብ (3)

“… ዋናው ጉዳይ የተጋጣሚ ቡድን አልያም የኳሷ እንቅስቃሴ ብቻ አይደለም፡፡ ኳሷ የምትደርስበት የሜዳ ክፍል ወይም የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ኳሷን የሚያገኝበት ክፍት ቦታም ወሳኝ ነው፡፡” – ሉዊ ቫን ሃል

ከላይ የተጠቀሱትን መነሻ ሐሳቦች አንደምታ ለመረዳት ስንሞክር ስለጨዋታው የሚኖረን ግንዛቤ ይሰፋል፤ ቀደም ብሎ በእግርኳስ አጨዋወት ሥልት ዙሪያ የነበረን አተያይም ይሻሻላል፡፡ አለፍ ብሎም የራሳችን የሆነ ንድፈ-ሐሳባዊ ድምዳሜ እንዲኖን ያነሳሳናል፡፡

ብሬንዳን ሮጀርስ ቁጥራዊ መረጃዎችን ተጠቅመው የደረሱበት ድምዳሜ “የጨዋታ ብልጫ መውሰድ” ወይም “ልቆ መገኘት” ብለው ያቀረቡትን ሐሳብ በስሌት የሚመዘን ልኬት በማድረግ ላይ ይመሰረታል፡፡ ምናልባት እርሳቸው ያነሱት ልቆ የመገኘት አጋጣሚ በተወሰነ የሜዳ ክፍል ላይ ብቻ ይሆን? ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሊሆን የሚችለው “ኳስ ይዞ ጨዋታን መቆጣጠር” የአንድ ቡድን እንዲሁም የቡድኑ ተጫዋቾች ሚና ይሆናል፡፡ አሰልጣኙ በስዋንሲ ክለብ ሳሉ ይህን ኃላፊነት የሚሰጡት ለሊዮን ብሪተን፣ ናታን ዳየርና ስኮት ሲንክሌር ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር በስዋንሲ ክለብ ተጋጣሚን በጨዋታ ልቆ መገኘት ማለት የተጠቀሱት ተጫዋቾች  ሜዳ ላይ የሚንቀሳቀሱባቸውን ቦታዎች በበላይነት ከመያዝ ጋር ይገናኛል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀጥተኛ ባለድርሻዎቹ እነዚሁ ቁልፍ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በሮጀርስ የተመራው ሊቨርፑል በወቅቱ ቁልፍ ተጫዋቾች የነበሩት ሱአሬዝ፣ ስተሪጅና ኩቲንሆ የበላይነት በሚወስዱባቸው የሜዳው ክፍሎች አማካኝነት ቡድኑ ልቆ ይገኝ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ “ተጋጣሚ ላይ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ” የተለያየ ይዘት ይኖረዋል፡፡ በአንድ ቡድን ዓይነተኛ ጥንካሬ ላይ ሊወሰንም ይችላል፡፡

” ኳስ ተቆጣጥሮ ተጋጣሚ ቡድን ላይ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ” አልያም በአጭሩ ” ተጋጣሚን በጨዋታ ልቆ መገኘት” የሚለውን የሮጀርስ ቀመር የሚከተል ቡድን በቀላሉ መጥቀስ ከባድ ነው፡፡ ከተሞክሮዬ ላስረዳ ብሞክር እንኳ የማገኘው በታክቲካዊ ዕቅዶች ዝግጅት ስሳተፍ የነበርኩበትን የኢስቶኒያ ብሄራዊ ቡድን ይሆናል፡፡ በማግኔስ ፌርሰን ይሰለጥን የነበረችው ኢስቶኒያ በስሎቬኒያ፣ ሳን ማሮኒ፣ ፊንላንድና አይስላንድ ላይ የምትወስዳቸው የበላይነቶች የተለያዩ ነበሩ፡፡

መነሻ ሐሳብ(3)ን በአግባቡ ለመረዳት እንችል ዘንድ በመጽሃፉ ቀጣይ ምዕራፎች  እንመለስበታለን፡፡ ያለ ሉዊ ቫን ሃል የጨዋታ መርሆች አውድ ዝርዝር ቃላቱ ትርጉም አልባ ይሆናሉ፡፡ (ከማርሴሎ ቢዬልሳ ጋር ተመሳስሎ ያላቸውን እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡) ይህ መነሻ የበለጠ ካልተተነተነ እና ካልተብራራም በቢዬልሳ ፍልስፍና ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች በሚፈለጉት መጠን ግልጽ አይሆኑም፡፡

ይቀጥላል…

የመጽሃፉ ደራሲ ጄድ ሳይናን ዴቪስ ይባላል፡፡ ዌልሳዊው በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በዋና አሰልጣኝነት፣ በኢስቶኒያ ብሄራዊ ቡድን ደግሞ በምክትል አሰልጣኝነት ሰርቷል፡፡ የሰላሳ ሁለት ዓመቱ ወጣት በአሁኑ ወቅት <ኦታዋ ፈሪ> በተባለው የካናዳ ክለብ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ ከ2019 ጀምሮ በኦታዋ ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ የእግርኳስ ፕሮፌሰር ሆኖ Strategy in Association Football ያስተምራል፡፡ ዴቪስ በ2013 ” Coaching the Tiki-Taka Style of Play” የተሰኘ መጽሃፍ አሳትሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ