ስለ አንተነህ አላምረው ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

እርሱ የአንድ ቡድን የልብ ምት ነው። ሜዳ ውስጥ ካለ ከኃላም ከፊትም ያሉት የቡድን ጓደኞቹ ምቾት ይሰማቸዋል። በዘጠናዎቹ ውስጥ ከታዩ ድንቅ የተካከላካይ አማካይ መካከል አንዱ የሆነው ግዙፉ ተጫዋች አንተነህ አላምረውአሳልፏል።

ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ በጦር ኃይሎች እና ልደታ መሀል በሚገኘው ቶሎሳ ሰፈር ነው። ለኳስ ተጫዋችነት መነሻ የሆኑት አባቱ ናቸው። እሱም በልጅነቱ እንደ ዓለም ዋንጫ ያሉ ውድድሮችን እየተመለከተ አድጓል። በተለይ በ1980 በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተካሄደውን የመካከለኛው እና የምስራቅ አፍሪካ ዋንጫ አይረሴውን ‹ዳኙ ገላግሌን› የድል ብስራት የፍፃሜ ጨዋታ በልጅነቱ አዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት በኳስ አቀባይነት ተከታትሏል። በዚህ ጊዜ ነው አንድ ነገር ለራሱ ቃል የገባው ‹‹እኔም አንድ ቀን ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ይህን ዋንጫ አንስቼ ታሪክ ሰራለሁ›› በማለት። በዚህ ያልቆመው ህልሙን እውን ለማድረግ ስታዲየም አካባቢ በምተገኘው ትንሿ ሜዳ በአስር ዓመቱ አቶ ታዴ እና ጌታቸው ጨቡዴ ፕሮጀክት ውስጥ በመግባት ይሰራ ጀመር። በመቀጠል ምድር ጦር ‘ሲ’ ቡድን ከዚያ ደግሞ ኪራይ ቤቶች ተጫውቶ ወደ ኢትዮጵያ ቡና አመራ። በኢትዮጵያ ቡና ከዕድሜውም አንፃር የመሰለፍ ዕድል ባለማግኘቱ በ1988 ቀጣይ ማረፊያውን በቅዱስ ጊዮርጊስ አደረገ።

በፈረሰኞቹ ቤት በነበረው የዓመታት ቆይታ በመሐል በሱዳን ሊግ ለመጫወት በሄደበት ጊዜ ካልሆነ በቀር በርከት ያሉ የዋንጫ ድሎችን አሳክቷል።

በቁመቱ ረዘም ያለው እና በመሐል አማካይነት ሜዳውን በግርማ ሞገስ ሲጫወት የምናውቀው አንተነህ ከሱዳን የአንድ ዓመት ውጤታማ ቆይታ በኃላ ወደ ሀገሩ በመመለስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ዳግመኛ ቆይታን አድርጎ 1995 ላይ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ይሰለጥን ወደነበረው ኢትዮጵያ ቡና አምርቷል። በቡናዎቹ ቤት የአሸናፊዎች አሸናፊ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫን አሳክቶ በመጨረሻም ለመከላከያ ተጫውቶ አሳልፏል።


በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አብሮት የተጫወተው እና በስም ሞክሼው የሆነው አንተነህ ፈለቀ ስለ አንተነህ ይህን ምስክርነት ይሰጣል። “አንተነህ በጣም ጎበዝ የሆነ በቦታው ሁሉን ነገር አሟልቶ ያየዘ ተጫዋች ነው። አብረኸው ሜዳ ውስጥ ስትጫወት ግዝፈቱ እና ብቃቱን አውጥቶ እንደሚጫወት የምታውቀው እርሱ ሜዳ ውስጥ ከሌለ ጉድለቱን በግልፅ የሚታይ በመሆኑ ነው። አንተነህ ለአንድ ቡድን በጣም ከሚያስፈልጉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረ ነው፡፡ እኔ በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔ በቦታው እንደ እርሱ ያለ ተጫዋች አላየሁም። አንተነህ ከሜዳ ውጪ የተለየ ፣ የሚሰማውን ፊት ለፊት የሚናገር ፣ የዋህ እና ቅን ሰው ነው።” በማለት ገልፆታል።
ከኢትዮጵያ ቡና በኃላ የመጨረሻ ክለቡ ወደሆነው መከላከያ በማምራት ለሁለት ዓመት ተጫውቷል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ1988 ጀምሮ ከሀገር እስከወጣበት 1998 ድረስ ሀገሩን በስኬት ያገለገለው አንተነህ ለመጀመርያ ጊዜ ከሀገር ውጪ ኢትዮጵያ ሩዋንዳ ላይ በ1994 የሴካፋ ዋንጫን ስታነሳ በስብስቡ ውስጥ አንተነህ ነበር። በተለይ ደግሞ የ1997 በሀገራችን በተስተናገደው እና ኢትዮጵያ ዋንጫውን ባነሳችበት የሴካፋ ውድድር ላይ በፍፃሜው ጨዋታ ቡሩንዲ ላይ ጎል አስቆጥሮ በወታደራዊ ሰላምታ ደስታውን የገለፀበት መንገድ በብዙሀኑ የስፖርት ቤተሰብ ውስጥ የቀረ ትውስታ ነው፡፡

ሌላኛው በቅዱስ ጊዮርጊስ አብሮት የተጫወተው እና የቅርብ ጓደኛው እንደሆነ የሚነገረው ዮሴፍ ሰለሞን ስለ አንተነህ ይህን ይናገራል “አንተነህ ከኃላ ለምንገኘው ተከላካዮች እና ከጎኑ ለሚጫወቱ አማካዮች ከለላ የሚሰጥ ፣ እንደ ልባችን ከኃላ ኳሱን መስርተን እንድንወጣ ትልቅ እገዛ የሚያደርግልን ምርጥ ተጫዋች ነው። ለእኔ የልብ ጓደኛዬ የነበረ ፣ ብዙ ነገሮችን አብረን ያሳለፍን ፣ በባህሪውም በጣም የዋህ ሰው ነው። ምንም እንኳን በየቦታው ተበታትነን ብንኖርም አሁንም ድረስ የምንጠያየቅ ጓደኛዬ ነው፡፡”

አንተነህ እየበሰለ በመምጣት ባገኘው ልምድ የሚጫወትበትን ክለብም ሆነ ሀገሩን እየጠቀመ ባለበት ሰዓት ሳይታሰብ ብዙ መጫወት እየቻለ በ1998 ከሀገሩ በመውጣት ኑሮውን በካናዳ ካደረገ 14 ዓመት ሆኖታል። ከረጅም ዓመታት በኃላ በዘጠናዎቹ ከታዩ ምረጥ የመሀል አማካዮች ውስጥ አንዱ የነበረው አንተነህ አላምረውን ከሶከር ኢትዮጵያ ካለበት ሀገር አግኝታው ቀጣዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡

“በእግርኳስ ተጫዋችነቴ በሀገር ውስጥ በሚገኙት ትላልቅ ቡድኖች በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በኢትዮጵያ ቡና ተጫውቼ አሳልፊያለሁ። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ወደ ሱዳን በሄድኩበት አጋጣሚ ካልሆነ በቀር በርከት ያሉ ዋንጫዎችን አንስቻለሁ። በኢትዮጵያ ቡናም ሆነ በመከላከያ የነበረኝ ቆይታ በጣም አሪፍ ነበር። በአጠቃላይ በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔ በክለብም በብሔራዊ ቡድንም ስኬታማ ነበርኩ ማለት እችላለሁ፡፡

“ከቅዱስ ጊዮርጊስ የወጣሁት በራሴ ምክንያት ነው። በአስተዳደር አካባቢ በነበሩ ችግሮች የተወሰኑ ሰዎች በሚያደርጉት ነገር ደስተኛ አልነበርኩም። እንዲሁም የካሣዬ አጨዋወት ይመቸኝ ስለነበር እዛ ሄጄ ጥሩ ነገር እሰራለሁ በሚል ወጥቻለው። እንጂ ለጊዮርጊስ ፍቅር ሳይኖረኝ ቀርቶ አልነበረም ፤ ጊዮርጊስን በጣም እወደው ነበር። ቡና ሄጄ የጥሎ ማለፍ እንዲሁም የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ከመብራት ኃይል ጋር ተጫውተን ወስደናል። በጣም ጥሩ ቡድን ነው የነበረን። እንደውም በዚያ ዓመት የሊጉን ዋንጫ መውሰድ እንችል ነበር። አንዳንድ የእኛ ስህተቶች ፣ ቡድኑ ውስጥ በነበሩ ቀላል ችግሮች እና በዳኞች ውሳኔም ዋንጫ ሳናገኝ ቀርተናል። በዛው ዓመት ደግሞ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ማንም አድርጎት የማያውቀውን ቡና አንድ ሚሊየን ብር የሜዳ ገቢ አግኝቷል።

“መከላከያ በጣም ጥሩ ስብስብ ነበረው። ቡድኑ ሲያድግ አልነበርኩም ፤ ካደገ በኋላ ነበር የገባሁት። እኔ ፣ ኩኩሻ ፣ ፋሲል ፣ አንዳርጋቸው ፣ ማሞዓለም ሻንቆ እና ወጣት ልጆችም ነበሩ ፤ ጥሩ ቡድን ነበር። እንደውም ጥሩ አቋም ላይ ሆኜ በብሔራዊ ቡድን የምስራቅ አፍሪካ ዋንጫን ያነሳነው መከላከያ እያለው ነበር። በመከላከያ ጥሩ ጊዜ አሳልፈን ነበር። ለዚህም ደግሞ ትልቁ ድርሻ የአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ነበር። ጥሩ ተጫዋቾች ሰብስቦ ጥሩ ቡድን ነበር የሰራው። ሁለት ዓመት ቆይቼ ነው የወጣሁት። እኔ ወደ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላም የጥሎ ማለፍ አሸናፊ ሆናዋል።

“ሱዳን የነበረኝ ቆይታ የአንድ ዓመት ነበር። ጊዜውም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 1999/2000 የውድድር ዓመት ነበር። ቆይታዬ በጣም ደስ የሚል ነበር። ሳውዲ ላይ ለሚደረገው ለአረብ ካፕ ውድድርም ስናልፍ እኔ ነበርኩ የማለፊያዋን ጎል ያስቆጠርኩት። ከእነርሱ ጋር እንድቆይ ሌላ አዲስ ኮንትራት አቅርበውልኝ ነበር። ነገር ግን አየሩንም ሆነ የሀገሩን ባህል ስላልለመድኩት ተመልሼ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውቻለሁ።

” እኔ እና ፍቅሩ ተፈራ ከምስራቅ አፍሪካው ውድድር በኋላ በውጪ ሀገራት የመጫወት ዕድል አግኝተን ነበር። በሚቾ አማካኝነት እሱ ደቡብ አፍሪካ እኔ ደግሞ ቦስኒያ ውስጥ ዕድሉን አግኝተን ነበር። ሚቾ ከፍቅሩ ጋር ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አውርቶን የኛን ቪዲዮ ሁሉ ልኮ እነሱም ወደውን ነበር። ነገር ግን በአንዳድ ጥቃቅን ነገሮች ሳንስማማ ቀርተን ወደ አሜሪካ የመምጣት ዕድሉ ስለነበረኝ ልመጣ ችያለሁ። ነገር ግን ትልቅ ስህተት ነው የሰራሁት። እግርኳስም በዛው አቆምኩኝ። ሆኖም አውሮፓ ተሻግሮ ለመጫወት የነበረው የሀገራችን የእግርኳስ አሰራር ምቹ አልነበረም ፤ የሱዳኑም በራሳችን ጥረት የተገኘ ነው። ሩዋንዳ ላይ ሥዩም አባተ ይዞት በነበረው እነኩኩሻ ፣ ሚካኤል ሽፈራው ፣ አሰግድ ተስፋዬ ፣ አፈወርቅ ኪሮስን በያዘው ስብስብ ላይ የውድድሩ በነበረኝ ነገር ነው ያንን ዕድል ያገኘሁት እንጂ የነበረው አሰራር እዛው ታፍነን እንድንቀር የሚያደርግ ነበር። ህይወታችንን ቀጭቶታል ማለት እችላለሁ። እንደዛም ሆኖ በራሴ ጥረት መድረስ የሚገባኝ ድረስ ደርሻለሁ።

“በብሔራዊ ቡድን ቆይታዬ በጣም ውጤታማ ነበርኩኝ ዋንጫዎችንም አንስቻለሁ። በተለይ ግን ልዩ ትውስታ ያለኝ ሀገራችን ላይ በተደረገው የዓሊ አል ሙዲን ሲኒየር ቻሌንጅ ካፕ ከባድ ዝግጅት ነበር ያዳረግነው። በሀገራችን ዋንጫውን ለማስቀረት በጥሩ መንፈስ ፣ ፍቅር እና ከፍተኛ ትኩረት ሁላችንም በመተጋገዝ ነበር የምንሰራው። ውጤቱም እንደታየው ደስ የሚያሰኝ ነበር።

“በ1989 ወደ ሞሮኮ ስንሄድ በጠፋንበት ሁኔታ እኔ በዛው እንደምንወጣም አላውቅም ነበር። ኪሴ ውስጥም መቶ ዶላር ብቻ ነው የነበረው። ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። ብቻ ሁሉም ሲወጣ አብሬ ወጣሁ። የመጥፋት ሀሳብም ሳይኖረኝ ነው የጠፋሁት። በመሀል የተወሰኑ ልጆች ተመለሱ። እኔም ከአስር ቀን በኋላ ብቻዬን ነው የተመለስኩት። ልመለስ ስል እንደውም ኬኔዲ ደምሴ ተከትሎኝ መጣ። እኔም ‘ቤተሰብ መመለስ እንዳለብኝ ስለነገረኝ መመለስ አለብኝ አንተ ግን እዚሁ ሁን’ ብዬ መከርኩት እና ተቃቅፈን እኔ ተመለስኩ እሱ እዛው ቀረ። ኤርፖርት ላይ ኢህአዴግ’ዎች ይዘውኝ አንዳንድ ጥያቄዎች ጠየቁኝ። ታሪኩ በጣም ረጅም ነው። ‘እኔስ ከፋኝ ከፋኝ መውጪያ እና መግቢያው ከጠፋኝ ልሂድ እንግዲህ ከከፋኝ’ የሚለውን የሠለሞን ተካልኝን ዘፈን አንተ ዓሊ ረዲ እና ሌሎች ተሰብስባችሁ ትዘፍኑ ነበር አሉኝ። ሌሎች የተለያዩ ጥያቄዎችም ጠየቁኝ እና ለቀቁኝ። ከዚያ ለስድስት ወር በክለባችንም ኳስ እንዳንነካ ታገድን ከሀገር እንዳንወጣም የቁም እስረኛ ሆንን። ከዚያን በኋላ ነው ወደ ኳስ የተመለስነው።

“1980 ላይ እነ ነጋሽ ተክሊት፣ ሙሉዓለም እጅጉ ፣ ሙሉጌታ ወልደየስ ፣ ሙሉጌታ ከበደ የምስራቅ አፍሪካ ዋንጫን ሲያነሱ እኔ ህፃን ሆኜ ኳስ አቀባይ ነበርኩ። ያ ነገር ጭንቅላቴ ውስጥ ተቀርፆ ነበር።’እኔስ መቼ ነው እንዲህ የማደርገው ?’ የሚል ሀሳብ ውስጤ ነበር። እና ያ ዕድል ሲመጣ ለራሴ ‘ይሄ ነው ትክክለኛው ጊዜ! ‘ ብዬ ነው የነገርኩት። በዛም ምክንያት ተጫዋች ሆኜ ምስራቅ አፍሪካን ስናሸነፍ ለእኔ የተለየ ታሪክ ነበረው። ከኳስ አቀባይነት ተነስቼ ያንኑ ውድድር በድል በማሳካቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።

” ጎል አስቆጥሬ ደስታዬን የምገልፅበት መንገድ የተለየ ሆኖ የተወራው የምስራቅ አፍሪካ ዋንጫን ያነሳን ጊዜ ነው። በፍፃሜው ብሩንዲ ላይ ጎል አስቆጥሬ ነበር። ከዚያ በፊት ለደረጃ ሱዳን እና ኬኒያ እየተጫወቱ ሆቴል ቁጭ ብለን በቲቪ ስናይ የመከላከያ የበላይ ጠባቂ የነበሩት እና እንደ አባቴ የማያቸው ጀነራል ኃይሌን አየኋቸው። እናም ለራሴ ‘ ዛሬ ጎል ካገባው ለእሳቸው የክብር ሰላምታ እሰጣለሁ ‘ አልኩ። አጋጣሚ ተሳክቶልኝ አገባሁ እና ሆቴል ሆኜ ያየኋቸው ቦታ ላይ ቆመው ነበር ፤ እና ለእሳቸው ስለምታ ሰጠው። ውድድሩ ካለቀ ከስንት ጊዜ በኋላ ‘ሰላምታ የሰጠው ለሼህ መሀመድ ዓሊ አል አ ሙዲ ነው ወይ ?’ ተብዬ ተጠይቄ ነበር። ነገር ግን ለጀነራል ኃይሌ ለክለባችን የበላይ ጠባቂ ክብር ነበር።

“ከቤተሰቤ በእግርኳስ ያለፍኩት እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ወንዴም ኳስ ተጫዋች አይደለም ፤ ነገር ግን በጣም ታዋቂ ደራሲ ነበር። ድሮ ለእነአስቴር አወቀ ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ ፣ ኩኩ ሰብስቤ ግጥም የሰጠ ያየህይራድ አላምረው የተባለ ወንድም አለኝ።

“ልጅ ሆኜ እንደማልመው ሀገር ውስጥ ባሉት ትልልቅ በድኖች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ተጫውቻለሁ። ከሀገር ውጪ ወጥቼ ስጫወትም ያንን ለማድረግ የሚያስፈልጉ ነገሮችን አሟልቼ ክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስም ማግኘት የሚገባውን ጥቅም አግኝቶ እኔም የፊርማ ክፍያ አግኝቼ በጥሩ ውል ነው ወጥቼ የተጫወትኩት። ሌላው ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ውድድር ላይ ኮከብ የሆነ ሰው አትላንታ ለሚዘጋጀው የኢትዮጵያዊያን እግርኳስ ውድድር ላይ ወጪው ተችሎ ይሄዳል በተባለው መሰረት ያንን ዕድል አግኝቻለሁ።

“የሚቆጨኝ ነገር እኛ ኳስ ስንጀምር አብዛኛውን ነገር በራሳችን ጥረት ነበር። የሚረዳን ሰው አጠገባችን አልነበረም። አሁን ላይ ሳስበው የሀገሪቱ የእግርኳስ አሰራር አጥፊ ነው። ፌዴሬሽኑ የወደፊት ተስፋችንን አጥፍቶታል ፤ ያመቻቸልን ምንም ነገር አልነበረም። ይህ በጣም ይቆጨኛል። ሁለተኛ ሚቾ አግኝቶልኝ የነበረው የቦስኒያ ቡድን ቻምፒዮንስ ሊግ ውስጥ የማጣሪያ ማጣሪያ የሚጫወት ቡድን ነበር። እኔ ግን ሱዳን ስሄድ ያደረግኳቸው ስምምነቶች ስለነበሩ ሊያታልለኝ እንደፈለገ አውቂያለሁ። ቡድኔ መከላከያም እንዲያውቅ አልፈለገም ፤ በራሱ ጨርሶ ሊልከኝ ነበር የፈለገው። መሄድ እንደማልፈልግ ነገርኩት። ያንን ነገር አሁን ላይ ቁጭ ብዬ ሳስበው ትልቅ ስህተት ሰርቻለሁ። ማየት የነበረብኝ ከዚያ በኋላ የት እሄዳለው የሚለውን ነበር። ቦስኒያ ብሄድ ከዚያ ደግሞ የሌሎች ትልልቅ ክለቦች ዕድል አገኝ ነበር። ያን አለማድረጌ ይቆጨኛል። ዞሮ ዞሮ ሁሉም ነገር በአምላክ ፍቃድ ስለሚሆን በፀጋ እቀበለዋለሁ።

“የጂኬ አጨዋወት ተከታይ ነህ ላልከኝ የግድ GK ስለሆነ አይደለም። እኔ ኳስ መባከን የለበትም የሚል አመለካከት አለኝ። የሆላንድ ብሔራዊ ቡድን በቶታል ፉትቦል ይጫወት በነበረበት መንገድ ኳስ ከኋላ በጥንቃቄ ተመስርቶ ያለምክንያት ሳይባክን መሰራት አለበት ብዬ ነው የማምነው እንጂ የግድ GK ስለሆነ አይደለም። በዛን ወቅት ግን የካሳዬ ሀሳብ ከሌሎቹ አሰልጣኞች ስለተለየ ሀሳቡ እኔን ሊገዛኝ ችሏል። ሌላም አሰልጣኝ ያ አመለካከት ቢኖረው እደግፈዋለሁ። ዋናው ነገር ግን ኳስ አለመባከኑ ነው። ኳስ ይዞ በመጫወት አምናለሁ ፤ ረጅም ኳስ መሰጠት የለበትም ባልልም ግን ብዙ አላምንበትም።

“በእግርኳስ ገጠመኜ 1995 ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታ ለማድረግ ላይቤሪያ ሄደን ነበር ፤ ብናሸንፍ የምናልፍበት ነበር። ከዚህ ተነስተን ጋና ሄድን። ጋና እንደደረስን ‘ላይቤሪያ ከባድ ጦርነት ስላለ አትሂዱ’ የሚል መረጃ ደረሰን። እኛ ደግሞ መሄድ አለብን ብለን ሄድን። ተኩስ እየተተኮሰ ነው ጨዋታውን የጨረስነው። በጨዋታው ጥሩ እየተጫወትን እነሱ 1-0 እየመሩ ግብ ጠባቂው ሰዓት ይገድላል። ዳዊት ተጠባባቂ ነበር። እና ከዚያ ተነስቶ ግብ ጠባቂውን በጠረባ ይመታው እና በቀይ ይወጣል። እኔ ደግሞ በዚህ ተናድጄ ዳኛውን አነቅኩት ፤ በዛን ጊዜ ዳዊት ሁለት ዓመት እኔ ደግሞ አንድ ዓመት ከኢንተርናሽናል ውድድር ተቀጣን። ይሄ የማይረሳኝ አንዱ አጋጣሚ ነው። ሌላው ደግሞ ላይቤሪያ ሆቴላችን ውስጥ ሆነን የመንግሥት ተቃዋሚዎች እየተታኮሱ ከተማ ገቡ። ጠባቂዎቻችን ሆቴሉን ከውጪ ዘግተውብን ጥለውን ጠፉ። ሰዉም እየሸሸ ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ይሄዳል። እኛ በዛ ሰዓት ያሳላፍነውን ጊዜ በህይወቴ አልረሳውም፡፡ በህይወት የመቆየት ዕድላችን ሀምሳ ሀምሳ ሆኖ ነበር።

“ሌላው ደግሞ ሩዋንዳ ሄደን ስንመጣ ሁላችንም አውሮፕላን ውስጥ ገባን። ሌሎች መንገደኞችም ነበሩ ፤ ሁላችንም ገባን። እኔ መጀመሪያም ስገባ ቀፎኝ ነበር። አብራሪውን ሳየው በጣም አጭር ነው ፤ ዓይኑም ቀልቷል። ‘ይሄ ሰውዬ ሰክሮ ነው ወይስ ምንድነው ?’ ብዬ በመስታወት አይቼዋለሁ። በቃ ልቤ አልወደደውም ነበር። እና ልክ አውሮፕላኑ መንደርደር እንደጀመረ የሆነ ቀይ መብራት አሳየ ፤ ለካ በሩን አልዘጉትም። ልክ መኪና በፍጥነት ሄዶ ፍሬን ሲይዝ እንደሚሆነው ሆነን ቆምን። በራራውም በዛው ተሰረዘ። እኛም ባለማወቅ ምንም ክስም አላቀረብንም ፤ የኬኒያ አየርመንገድ ነበር። አጣድፈው በሌላ በረራ እንድንሄድ ኬንያ ኢንተር ኮንትናንታል ድሮ መንግሥቱ ኃይለማርያም ያርፍበት ነበር ባሉት ሆቴል ሦስት እና አራት ቀን ደብቀው እንዳስቀመጡን ትዝ ይለኛል።

“ከሀገሬ ከወጣሁ 14 ዓመት አልፎኛል። ቅዱስ ጊዮርጊስ እያለው የወለድኩት ልዑል የሚባል አንድ ልጅ አለኝ። አሁን 21ኛ ዓመቱ ነው። እንደውም የተወለደው በጊዮርጊስ ቀን በ23 ነበር ፤ አሁን አድጓል ። እኔ እያለሁ ኳስ ጎበዝ ነበር። ከወጣሁ በኋላ ግን ቅርጫት ኳስ ስለሚወድ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች እና ጎበዝ ተማሪ ሆኗል። ከዚያ ውጪ ግን እስካሁን አላገባሁም። ከሀገር ከወጣው በኋላ እዚህ ኢትዮ ዋሊያ የሚባል ቡድን ስላለን እየተጫወትኩ አሰለጥናለሁ። እዚህ የተለያዩ ሀገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች የሚጫወቱባቸው ውድድሮች አሉ። እዛ ላይ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ላይ እየተጫወትን ነው። ባለፈው ዓመት የጀመርነው ውድድር ነው። በመሀል የተወሰኑ ዓመታት አሞኝ አቁሜ ነበር እንጂ አሁንም በደንብ እጫወትታለሁ።

“ስለኔ መናገር ከባድ ቢሆንም እኔ ኳስ ተመስርቶ ሲሄድ ደስ ይለኛል። ኳስ ከተከላካይ አላስፈላጊ በሆነ ሁኔታ እኔን አልፎ ሲሄድ በጣም ነው የምናደደው። ከእኔ ጎን ካለ አማካይ ጋር መስርተን ስንወጣ ደስ ይለኛል። ከዚያ ውጪ ያለአግባብ ወደፊት በረጅሙ ሲላክ አይመቸኝም። ሌላው ደግሞ መሸነፍ አልወድም። አይደለም መሸነፍ ስንመራ ራሱ ጎል እስክናገባ ድረስ በጣም ነው የምናደደው ፤ በጣም እልህ አለብኝ። ትልቅ ውድድር ላይ ብቻ ሳይሆን አሁን ራሱ ልምምድ ላይ መሸነፍ አልወድም።

“በአባቴ ስም አላምረው ብለው ነው ብዙዎች የሚጠሩኝ። ከዚያ ውጪ ልጅ እያለሁ ኃይሌ ካሴ ስታድየም አስፋልት ላይ ስጫወት ‘አንቶኔቭ’ ይለኝ ነበር። ለምን እንደዛ እንዳለኝ ግን አልጠየኩትም። ዳዊት ገዳዳው ደግሞ ‘ሙቾ ‘ ብሎ ይጠራኝ ነበር። የተለያዩ ሰዎች በተለያየ ስም ይጠሩኛል። ምክንያቱን ግን ጠይቄ አላውቅም።

“ብዙ መጫወት የምችልበት ጊዜ ላይ ነው የወጣሁት። ባልወጣ ኖሮ አምስት ስድስት ዓመት መጫወት እችል ነበር። አሁን ራሱ ስጫወት ሳየው አውቃለው እንደበፊቱ እንደማልሆን ግን አቅሙ እንዳለኝ እረዳለሁ። የወጣሁበት ምክንያት ሀገር ውስጥ የነበረው የኳሳችን ሁኔታ ፕሪምየር ሊግ ተብሎ ከተጀመረ በኋላ እየቀነሰ እየቀነሰ ሲሄድ ብዙም ደስተኛ አልነበርኩም። ወጥተህ ስትጫወት ሜዳዎቹ ፣ የደጋፊ ጭቅጭቁ ምኑ በየቦታው የነበረው ነገር ደስ የሚል ስላልነበር ወጥቻለው። ያም ቢሆን አልቆጭም። በህይወቴ በኳሱ ጥሩ ጊዜ አሳልፊያለሁ። በዚህም ደስተኛ ነኝ። ወደ ፊትም ወደ ሀገሬ እመጣለሁ። እናንተም ፈልጋችሁ እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!