የዋልያዎቹን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ገለፃ ተሰጥቷል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኒጀር ጋር ያለበትን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እና የነገውን የሱዳን የአቋም መለኪያ ግጥሚያ አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ ተሰጥቷል።

ወሎ ሠፈር በሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት አዳራሽ የተከናወነውና ለ45 ደቂቃዎች የቆየውን ጋዜጣዊ መግለጫ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እንዲሁም ረዳቶቻቸው አሥራት አባተ፣ አንዋር ያሲን እና ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ ሰጥተዋል። አሠልጣኞቹም ከቀናት በፊት ከነበረው የዛምቢያ የአቋም መለኪያ ጨዋታ በኋላ የታየውን የቡድኑን ወቅታዊ አቋም ከነገው የሱዳን እንዲሁም ከሳምንት በኋላ ከኒጀር ጋር የሚደረገውን ጨዋታ ተንተርሰው ገለፃዎችን አድርገዋል። በቅድሚያም የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በስፍራው ለተገኙ የብዙሐን መገናኛ አባላት የቡድኑን አሁናዊ ሁኔታ አስረድቷል።

“በአሁኑ ሰዓት ቡድኑ ለኒጀሩ ጨዋታ የመጨረሻ የዝግጅት ጊዜ ላይ ይገኛል። እንደምታቁት ዘግይተን ወደ ዝግጅት እንደመግባታችን ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን በማዘጋጀት የተጫዋቾችን ሁኔታ ለማየት ሞክረናል። የዛምቢያው የአቋም መለኪያ ጨዋታ ዝግጅት ከጀመርን ከ14 ቀናት በኋላ ስለሆነ የተደረገው ቡድኑ ብዙ ክፍተቶች ነበሩበት። ግን ጨዋታዎቹ ለእኛ እንደ ጨዋታ ሳይሆኑ እንደ ልምምድ ነበር የጠቀሙን። ምክንያቱም መርሐ-ግብሩን ተጫዋቾቻችን ያሉበትን ነገር ለማየት ስለሆነ የተጠቀምንበት። ለዛም ነው የዛምቢያውን ጨዋታ ተንተርሰን ብዙ ነገር ማለት የማንችለው። 7 ወር የት እንደነበሩ የማይታወቁ ተጫዋቾችን ሰብስቦ በ15 ቀን ይህንን አድርጉ ብሎ ማዘዝ ይከብዳል። በአጠቃላይ ግን ሁለቱ የወዳጅት ጨዋታዎች ጠቅመውናል። የዛምቢያውን ጨዋታ ካከናወንን በኋላም ተጫዋቾችን ቀንሰን ዝግጅታችንን ማከናወን ቀጥለናል። በዝግጅታችንም ሱራፌል ዳኛቸው የጉልበት ፣ አማኑኤል ዩሃንስ የብሽሽት፣ ሙጂብ ቃሲም የታፋ ጡንቻ እንዲሁም አቡበከር ናስር የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት አስተናግደው ነበር። ግን አማኑኤል እና አቡበከር ከጉዳታቸው አገግመው ከቡድኑ ጋር ልምምድ ጀምረዋል። የሱራፌል ጉዳት ቀላል ቢሆንም እሱ እና ሙጂብ ግን እስካሁን ቡድኑን ተቀላቅለው ልምምድ አልሰሩም።” ብለዋል።

ዋና አሠልጣኙ ጨምረውም የነገውን የሱዳን የአቋም መለኪያ ጨዋታ እና የኒጀርን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ግጥሚያ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

“እንዳልኩት የዛምቢያውን የአቋም መለኪያ ጨዋታ ተጫዋቾቻችንን ለማየት ነበር የተጠቀምንበት። የነገው ጨዋታ ግን የቡድናችንን 70 እና 80 በመቶ የምናይበት ነው። ለኒጀሩም ጨዋታ ያለንን ነገር በግልፅ እንደምናይበት አስባለሁ። በዛምቢያው ጨዋታ የታዩብንን ክፍተቶችም ለማስተካከልም ስለሰራን በነገው ጨዋታ ያንን መሻሻል ለመመልከት ጨዋታው ይጠቅመናል።”

እስካሁን ሦስት ጊዜ የኮቪድ-19 ምርመራ ያደረገው ቡድኑ የሜዳ ላይ ልምምዶችን በካፍ የልህቀት ማዕከል እና አዲስ አበባ ስታዲየም ከማከናወኑ በተጨማሪ የክፍል ውስጥ ትምህርቶችን ሲያገኝ እንደነበረ በመግለጫው ተብራርቷል። በተለይ ደግሞ የስነ ልቦና ስራዎችን በባለሙያዎች በመታገዝ ቡድኑ እንዲያገኝ ተደርጓል ተብሏል። በተጨማሪም ዘመናዊውን የእግርኳስ ዳኝነት ህግ እንዲሁም የአፍሪካ ዳኞችን ስነ-ልቦና ለተጫዋቾቹ ለማስረዳት በአህጉራዊ ውድድሮች ትልቅ ልምድ ያላቸውን ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በዓምላክ ተሰማ እና ሊዲያ ታፈሰ ቡድኑን የዳኝነት ትምህርት እንዲሰጡ እንደሚደረግ ተነግሯል (ከመግለጫው በኋላ 11 ሰዓት ትምህርቱ ተሰጥቷል)።

26 ተጫዋቾችን ይዞ ልምምዱን እያከናወነ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ በነገው ዕለት ሦስተኛ የአቋም መለኪያ ጨዋታውን 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ካከናወነ በኋላ ሰኞ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሦስተኛ የማጣሪያ ጨዋታውን ለማከናወን ወደ ኒጀር እንደሚበር ተነግሯል። ወደ ኒጀር በሚያቀናው ስብስብ ውስጥም 23 ተጫዋቾች እንዲካተቱ ተደርጎ ቀሪዎቹ ሦስት ተጫዋቾች ሳይቀነሱ ቡድኑ ከኒያሚ ሲመለስ እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግ አሠልጣኙ አብራርተዋል። በመጨረሻም ዋና አሠልጣኙ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ሽመልስ በቀለ ከግብፅ በመጣ ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ ቡድኑን መቀላቀሉ እና ልምምዶቸን በጥሩ ሁኔታ እየሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!