ከፍተኛ ሊግ | ኢኮሥኮ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ

በቅርቡ አሰልጣኝ የሾመው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢኮሥኮ) አስራ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የሦስት ነባሮችን ውልም አራዝሟል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን የሚታወቀው ኢኮሥኮ በቅርቡ ዳንኤል ገብረማርያምን መሾሙ ይታወሳል፡፡ ክለቡም በአሰልጣኙ እየተመራ ለዘንድሮው የውድድር ዓመት ጠንክሮ ለመቅረብ ይረዳው ዘንድ አስራ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከየክለቡ ሲያስፈርም ሦስት ነባር ተጫዋቾቹን ለማቆየት ውላቸውን አድሶላቸዋል፡፡ ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ መካከል ከሀዋሳ ከተማ ታዳጊ ቡድን ከተገኘ በኃላ ያለፉትን አራት ዓመታት በዋና የሀዋሳ ቡድን ሲጫወት የቆየው ወጣቱ ግብ ጠባቂው አላዛር መርኔ እና ከመከላከያ ወጣት ቡድን ተገኝቶ ያለፈውን ዓመት ለአንደኛ ሊጉ ዳሞት ከተማ እየተጫወተ የነበረውና በአሁኑ ሰዓት በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሪ የቀረበለት አማካዩ ቤዛ መድህን ሲገኙበት ፈጣኑ አጥቂ የኃላሸት ሰለሞን ከደቡብ ፖሊስ፣ ቃልፍቅር መስፍን (አጥቂ ከወሎ ኮምቦልቻ)፣ አብዱልቃድር ናስር (የመስመር ተከላካይ ከአቃቂ ቃሊቲ)፣ ቴዲ አጋ (አማካይ ከአቃቂ ቃሊቲ)፣ ኤርሚያስ ኃይሌ (አጥቂ ከገላን ከተማ)፣ አቤኔዘር ኦቴ (የግራ ተከላካይ ከወልቂጤ)፣ አቡበከር ጀማል (ተከላካይ ከሶሎዳ አድዋ)፣ ምትኩ ማመጫ (አማካይ ደቡብ ፖሊስ)፣ ዝናው (ተከላካይ ከሶሎዳ አድዋ)፣ ተፈራ አንለይ (አማካይ ከመከላከያ)፣ ዘሪሁን ዐቢይ (ተከላካይ ከገላን ከተማ)፣ አብዱላዚዝ አማን (አጥቂ ከቡታጅራ ከተማ) የአሰልጣኝ ዳንኤልን ቡድን የተቀላቀሉ አዲሶቹ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ክለቡም የሶስት ነባሮችንም ውል አራዝሟል፡፡ መስፍን ቡዜ (ግብ ጠባቂ)፣ ኢሳያስ ታደሰ (አጥቂ) እና እስማኤል ነጋሽ (ተከላካይ) ውላቸው የተራዘመላቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!