ይህን ያውቁ ኖሯል? (፯) | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ…

በዛሬው ይህንን ያውቁ ኖሯል? አምዳችን የነገውን የዋሊያዎቹ የኒጀር ጨዋታ እና አጠቃላይ የቡድኑን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች እውነታዎችን አጠናክረን ቀርበናል።

* የተጠቀሱት ጊዜያት በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ነው።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫው ማጣርያ በነገው ዕለት የኒጀር ብሔራዊ ቡድንን ይገጥማል። ይህም ጨዋታ ለዋልያዎቹ ከ360 ቀናት በኋላ የሚደረግ የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታ ይሆናል። ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ የነጥብ ጨዋታ ያደረገችው ኅዳር 9 ቀን 2012 አይቮሪኮስትን 2-1 የረታችበት ነው።

– ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዋልያዎቹ ነገ የሜዳ ውጪ የነጥብ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ከ363 ቀናት በኋላ ይሆናል። ለመጨረሻ ጊዜ ከሜዳቸው ውጪ የነጥብ ጨዋታ ያደረጉት በማዳጋስካር 1-0 የተሸነፉበት የኅዳር 6 ጨዋታ እንደነበር ይታወሳል።

– ዋልያዎቹ ከኒጀር ጋር ከዚህ ቀደም በሦስት አጋጣሚዎች ተገናኝተው ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ስታሸንፍ አንድ ጊዜ ኒጀር ረታለች።

– ሁለቱ ከዚህ ቀደም ለ2004 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በአንድ ምድብ ተገናኝተው የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ በሜዳዋ ያደረገችውን ጨዋታ በኤርሚያስ ኪዳኑ እና አብዱላሂ አዛድ (በራሱ ጎል ላይ) ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-0 ስታሸንፍ ኒያሜ ላይ በአንፃሩ ኒጀር 3-1 አሸንፋለች።

– ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በወዳጅነት ጨዋታ ሲሆን ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ባለፈችበት ወቅት ለውድድሩ ዝግጅት ካደረገቻቸው ጨዋታዎች መካከል ኒጀርን በአዲስ አበባ ስታዲየም የገጠመችበት ነበር። በጥር ወር 2005 በተደረገው በዚህ የወዳጅነት ጨዋታ ዋልያዎቹ በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸንፈዋል።

– ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ከሜዳዋ ውጪ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ድል ያስመዘገበችው በሰኔ ወር 2008 ሲሆን ማሴሩ ላይ የሌሶቶ ብሔራዊ ቡድንን በጌታነህ ከበደ ጎሎች 2-1 አሸንፋ ተመልሳለች። ከዚህ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ባደረገቻቸው ቀጣይ ሦስት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዳለች።

– ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በአጠቃላይ ከ31 የአፍሪካ ሀገራት ጋር ተጫውታለች። ከነዚህ መካከል ከ30 ሀገራት ጋር ሜዳ ገብታ ስትጫወት ከአንድ ሀገር (ቻድ) ጋር ለመጫወት መርሐ ግብር ወጥቶላት ኢትዮጵያ ከውድድሩ ራሷን በማግለሏ ለቻች ፎርፌ ተሰጥቷል። ሜዳ ገብታ ከገጠመቻቸው 30 ሀገራት መካከል ደግሞ ከሴራሊዮን ጋር ያደረችው ጨዋታ በሴራሊዮን መታገድ ምክንያት ውጤቱ ተሰርዟል።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከገጠመቻቸው 31 የአፍሪካ ሀገራት መካከል በተደጋጋሚ ያገኘቻት ሀገር ዩጋንዳ ስትሆን በ10 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ግብፅ እና ሱዳን ቀጣዩን ቦታ በ8 ሲይዙ ኬንያ፣ አልጄርያ፣ ጊኒ እና ታንዛንያ በ6 ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያን የገጠሙ ቡድኖች ናቸው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!