​አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስለ ትናንቱ ድል ይናገራሉ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ከቀጥር በኋላ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የዝግጅት ጊዜ እና ትላንትና ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ አራተኛ የማጣሪያ ጨዋታውን ከኒጀር አቻው ጋር ያደረገውን ዋናውን ብሔራዊ ቡድን በተመለከተ በአሠልጣኞቻቸው አማካኝነት መግለጫ እንዲሰጥ አድርጓል። በዚህም የዋልያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ የትላንቱን ድል አስመልክቶ ሃሳባቸውን ለጋዜጠኞች አጋርተዋል። 

“እንደምታቁት ለምድቡ ሦስተኛ እና አራተኛ የማጣሪያ ጨዋታ አንድ ወር ከአስር ቀን ዝግጅት አድርገናል። የአርቡም ጨዋታ በተመለከተ ከዚህ በፊት ገለፃ ስላደረኩ አሁን ምንም አልልም። ግን ትላንት ጨዋታው በሜዳችን የተደረገ ስለነበር ከጨዋታው ማግኘት የሚገባንን ከፍተኛ ነጥብ ለማግኘት ወደ ሜዳ ገብተናል። ይህም ተሳክቶልን በጥሩ እንቅስቃሴ እና በተሻለ ወደ ተጋጣሚ ግብ የመድረስ እንቅስቃሴ ሦስት ግቦችን አስቆጥረን ወጥተናል። እንዳያችሁት ኒጀሮች ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ ለመመለስ ነበር አልመው የመጡት። ግን እኛ ያንን ሳንፈቅድላቸው ጨዋታውንም አቅልለን አሸንፈን ወጥተናል። 
“በጨዋታው እኔ ፈልጌ የነበረው ሁለት ነገር ነው። አንደኛው ሦስት ነጥብ ከጨዋታው ማግኘት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኒጀር ላይ የነበረውን ብልጫ መድገም የሚል ነው። ይህንንም በጥሩ ሁኔታ አሳክተናል። ሲጀምር በአርቡ ጨዋታ የተሸነፍነው ጎል ስላላገባን ብቻ ነው እንጂ በብዙ ነገሮች የተሻልን ነበርን።ለዛም ነው የአርቡን ቡድን ሳልቀይር ለጨዋታው የቀረብኩት። እንደውም እንዳደረግነው እንቅስቃሴ ቢሆን ሁለቱንም ጨዋታ ማሸነፍ ነበረብን። 
“አሁን ላይ በምድቡ የሚገኘው ይህ ቡድን 100% ያልፋል ብሎ መናገር አይቻልም። የቡድኖቹን ስም ትተን ሜዳ ላይ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ብንመለከት እንኳን ብዙ መቀራረቦች አሉ። ስለዚህ እኛም ከፉክክሩ ስላልወጣን በራሳችን የሚወሰን እድል አለን። ለሁሉም ክፍት የሆነ እድል ስለሆነ ያለው ቀሪዎቹን ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ላይ ጠንክረን እንቀርባለል። እርግጥ ከዚህ በኋላ ተጫዋቾቹ ወደየ ክለቦቻቸው ነው የሚሄዱት። እንደ ቀድሞዎቹ ጊዜም ሊግ እያቋረጡ ለብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ጊዜ ስለማይወሰድ ከሊጉ አሠልጣኞቻችን ጋር እንነጋገራለን። 
“እኔ ወደ ቡድኑ ስመጣ ከበፊቱ ቡድን ምንም የተሰጠኝ ቴክኒካዊ ግምገማ የለም። ግን ይህ መሆን የለበትም። እኔም ከሄድኩ በኋላ እንደዚህ አይነት ነገር እንዳይፈጠር ስራዎችን እሰራለሁ። በአጠቃላይ ግን ቡድኑ 38 ተጫዋቾችን ይዘን ልምምድ ከጀመርንበት ዕለት ጀምሮ በደንብ እየተሻሻለ እና እየተለወጠ የመጣ ቡድን ነው።” ብለዋል።
አሠልጣኙ ሰኞ ዕለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ “በስጨት” ብለው የታዩ ሲሆን በዛሬው ዕለት ግን በተረጋጋ መንፈስ አስተያየታቸውን ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል። ይህንን ተከትሎም በተፈጠረባቸው የስሜት ልውውጦች ዙሪያ ጥያቄ ቀርቦላቸው ይህንን ብለዋል።
“እኔን ከዚህ ቀደም ያበሳጨኝ ነገር ሀገራዊ ጉዳይ ነው። እንዳልኩት ሁላቸንም አንድ ሀገር ነው ያለን። ስለዚህ ለሀገራች ሁላችንም መተባበር አለብን። ግን ከአርቡ ጨዋታ በኋላ ይህ አልሆነም። እኔ በግሌ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በሚሰነዘሩት ነገር ምንም አልሆንም። ለተጫዋቾቹ እንደውም የምነግራችሁን ብቻ አድርጉ ነው የምላቸው። ከዛ ስትሸነፉ እኔ ሀላፊነቱን እወስዳለሁ ስሳሸንፉ ደግሞ እናንተ ትሞገሳላችሁ አልኳቸው። ስለዚህ ባለፈው ሀገራዊው ነገር ለምን እንዳልታሰበ ነው ያበሳጨኝ።” በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
በመጋቢት ወር የምድቡ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎችን የሚያከናውነው ቡድኑ ከጨዋታዎቹ በፊት ቢያንስ አንድ የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንዲዘጋጅ ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ ጥረቶች እንደሚጀመሩ ተገልጿል።
©ሶከር ኢትዮጵያ