​ዐፄዎቹ ለአፍሪካ መድረክ ውድድራቸው ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ

በዘንድሮ ዓመት በኮፌዴሬሽን ካፕ ተሳታፊ የሆኑት ፋሲል ከነማዎች ዝግጅታቸውን በአዲስ አበባ አጠናክረው ቀጥለዋል። 

በካፍ ኮፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን የሚወክለው ፋሲል ከነማ ከቱኒዚያው ዩ ኤስ ሞናስቲር ጋር መደልደሉ ይታወቃል። የመጀመርያ ጨዋታውን ከኅዳር 18-20 ከሜዳው ውጪ፤ የመልሱን ጨዋታ ደግሞ በሳምንቱ ከ25-27 በሜዳው የሚያደርግ ይሆናል።

አስቀድሞ በጎንድር ከተማ ዝግጅቱን ሲያደርግ የከረመው ቡድኑ አሁን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ማረፊያውን ሆሊደይ ሆቴል በማድረግ በንግድ ባንክ ሜዳ ጠንካራ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል። በብሔራዊ ቡድን አገልግሎት ምክንያት ከቡድኑ ጋር አብረው ዝግጅት ያልነበሩት ያሬድ ባዬ፣ አምሳሉ ጥላሁን፣ ሽመክት ጉግሳ እና ሱራፌል ዳኛቸው ልምምድ ሲሰሩ ተመልክተናል። 

ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ሙጂብ ቃሲም አሁን በሙሉ ጤንነት ልምምድ ሲሰራ ተመልክተናል። ግብጠባቂው ቴዎድሮስ እና እንየው ካሣሁን ከፓስፖርት ጋር በተያያዘ በዛሬው ልምምድ ላይ ያልተሳተፉ መሆናቸውን ሲታወቅ የተቀሩት የቡድኑ አባላት መጠነኛ ጉዳት ካጋጠመው ሱራፌል ዳኛቸው በስተቀር ሁሉም በሙሉ ጤንነት ልምምዳቸውን ሲሰሩ ለማየት ችለናል። ለሁለት ተከፍለው በሙሉ ሜዳ ሲጫወቱ የቆዩት ዐፄዎቹ ምን አልባት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ለኤስ ሞናስቲር ጨዋታ 90% የሚጠቀሙበትን ተጫዋቾች ፍንጭ የሰጠ ቡድንም አስመልክተውናል። 

አንዳንድ ከቪዛና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በጉዟቸው ላይ እክል ቢያጋጥማቸውም ፌዴሬሽኑ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር አሁን ነገሮች ተስተካክለው የፊታችን ሰኞ ምሽት ወደ ሥፍራው ሊያቀኑ እንደሚችሉ ለማወቅ ችለናል።

©ሶከር ኢትዮጵያ